“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

ከባነንክ…ወደ መኝታ አትመለስ

by | Dec 22, 2020 | መነቃቂያ | 3 comments

እንደኔ ከሆናችሁ ሌሊት እንደ መንቃት የሚያናድደኝ ነገር የለም። ከተኛሁኝ ድብን ብዬ ሲነጋ መንቃት እንጂ፤ ሌሊት መባነን ደስ አይለኝም። ድንገት ከባነንኩኝና እንቅልፍ መልሶ ካልወሰደኝ እጨነቃለሁ።  እርግጠኛ ነኝ እንዲህ የሚሰማኝ እኔ ብቻ አይደለሁም። ሁላችንም ድንገት በሌሊት ከባንን ወዲያው ተመልሰን ለመተኛት እንታገላለን። በተለይ ከመንጋቱ ትንሽ ቀደም ብሎ የሆነ ነገር ካባነነን፤ ተመስን እንድንተኛ የሚጎተውተን ስሜት እጅግ ከባድ ነው።ይህንን ያነሳሁበት ምክንያት ስለ እንቅልፍ ወዳድነቴ ለማስረዳት አይደለም። ለመጻፍ ያነሳሳኝ ሃሳብ ጨርሶ ከእንቅልፍ ጋር ግንኙነት የለውም። የፐርሺያውን ገጣሚ “ወደ መኝታህ አትመለስ” የሚለውን አባባል መዋስ ስልፈለግኩኝ እንጂ።

“The breeze at dawn has secrets to tell you.

Don’ go back to sleep

You must ask what you really want.

Don’t go back to sleep.”- Rumi

“የንጋቱ ነፋስ የሚነግርህ ሚስጥር አለና ተመስህ አትተኛ፤

የምትፈልገውን  ሳትጠይቅ ተመልስህ አትተኛ”

ተመልሰን እንድንተኛ የሚጎተጉተን ስሜት፤ የንጋቱ ነፋስ ይዞልን የመጣውን ሚስጥር እንዳንሰማ ይከለክለናል። መባነን ደስ የማይል ስሜት ነው፤ በትዕግስት ካላለፍነው የመባነን ስሜት ይረብሻል። ሰው ድብን ብሎ ከተኛበት ሲባንን የድብርት፤ የመደናገር፤ የመቅበዝበዝ፤ ነገሮችን ጥርት ባለ መልኩ ያለማየት ስሜቶች ይንጸባረቁበታል።

አብዛኛዎቻችን የምንኖረው በእቅልፍ ልብ ውስጥ ነው ማለት ይቻላል። የምንወስናችው ውሳኔዎች፤ የምናደርጋቸው ድርጊቶች፤ ሀሳቦቻችን፤ ምኞቶቻችን ባጠቃላይ በቀን በቀን የምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ በአብዛኛው ድግግሞሽ ናቸው። አስበን ከምናደርጋቸው ድርጊቶች ፤አይምሮዋችን እንደለመደው የሚወስናቸው ውሳኔዎች ያመዝናሉ። አንዳንዴ ግን የሆኑ አጋጣሚዎች ካንቀላፋንበት ያባንኑናል፤ ያኔ ከእንቅልፍ እንደቀሰቀሱት ህጻን ድንግርግራችን ይወጣል። ይሄኔ ነው ተመልሰን የማንቀላፋቱ ፍላጎት የሚወተውተን። ደስ የማይለውን የመባንነን ስሜት ለመሸሽ፤ የሞቀው ኑሮዋችንን እንደብርድ ልብስ ተከናንበን ተመልሰን ለማሸለብ እንታገላለን። ሆኖም ግን የባነንነው፤ ሩሚ እንዳለው ልንሰማው የሚገባን ሚስጥር ስላለ እንዲሆም የእውነት የምንፈልገውን ነገር እንድንጠይቅ እድል ነውና፤ በፍጹም ተመልሰን መተኛት የለብንም።

መባነን ወይም መቀስቀስ ለጥቂት ደቂቃዎች ይጫጫናል፤ አይን ይሞጨሙጫል፤ ሰውነት ይደክማል፤ አይምሮ ይፈዛል። ሆኖም ግን ይህ ስሜት በጣም ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ደስ የማይል ስሜት ነው። ቀስ እያለ አይኖች ይበራሉ፤ ሰውነት ይሞቃል፤ አይምሮ ይነቃል። ያኔ ተመልሶ የማንቀላፋት ፈተናውን ያለፈ ሰው፤ የመንቃትን ዋጋ ያገኛል። እንደሚመስለኝ ሁላችንም በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የሆነ ያንቀላፋንበት የህይወት መስመር አለ። ታዲያ በተለያዩ አጋጣሚዎች ፈጣሪ ሊያባንነንና ሊያነቃን ሲፈልግ በፈተናዎች ውስጥ ያሳልፈናል። የእቅልፍ ጣዕም ሲበዛ ብርቱ ነውና አብዛኛዎቻችን ተመልሰን እናንቀላፋለን። የመንቃቱን ስሜት መቋቃም ስለሚያቅተን ብቻ።  የንጋቱ ነፋስ ያመጣልንን ሚስጥር ሳንሰማ፤ የምንመኘውን ሳንጠይቅ ተመልሰን ጥቅልል ብለን እንተኛለን። ማንቀላፋት ምቾት አለውና። አንዳንዶች ግን የሚታገላቸውን ተመልሶ የማንቀላፋት ስሜት ተቋቁመው ካንቀላፉበት እስከወዲያኛው ይነቃሉ።

እንደሚመስለኝ ፈተናዎች ሁሉ የማንቃያ ደውሎች ናቸው። በችግርና በፈተና ውስጥ የምናልፈው፤ ካንቀላፋንበት መንቃት ስላለንብን ነው። ለአብዛኛዎቻችን ግን ፈተናው ከባነን በኋላ ተመልሰን እንድንተኛ የሚታገለንን ስሜት ማሸነፍ ነው። ምናልባት እንደኔ አልፎ አልፎ  ከእቅልፍ እንደቀሰቀሱት ሰው የግርታ ስሜት የሚሰማችሁ ከሆነ፤ የሩሚን አባባል እንድታስታውሱ አደራ እላለው፤ በፈተና ውስጥ የመጣውን መልክዕክት፤ በመባነን ውስጥ የሚገለጠውን ሚስጥር ሳንሰማ ተመልሰን እንዳንተኛ!!

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

3 Comments

  1. eduna

    መልካም የሆኑ ስራዎች ሲገኙ በነበሩበት ሁኔታ የራስ የሆነ ማዳረሻ ቦታ ወስዶ ሌላው እንዲያገኘው ማድረጉ ክፋት ካለመሆኑ ባሻገር የበጎ ስራው ከሌላው እንዲደርስ የሚደረስ እገዛ ተደርጎ ይቆጠራል ብዬ አስባለሁ። ሌላው ደግሞ በጎ የመስራቱ አቅምና ብርታት ያላቸው ስራቸው ለንባብ ሲበቃ ወይም ሲዳረስ እንደዚሁ ይደሰታሉ ብዬ አስባለሁ።

    Reply
  2. Yohannes

    Good job !

    Reply
  3. Johni

    Wow Mis #mistre I thank you.
    ግጥሙ ተመችቶኛል ለተመልሶ መተኛት ሁነኛ ተግሳጥ ይመስለኛል ነገ እስከምሞክረው ጓጉቻለሁ። ይግረምሽና ፈተናውን ባለማለፌ(ተመልሶ መተኛትን) አንዳንዴ ሰዎች አስገድደዉኝ በተነሳሁ ቀን ይቆጨኛል። እና ለቀጣዩ ቀን እፎክርበታለው ግን ግነ… ለውጥ የለም።
    የ Muri ግጥም ከነገ ጀምሮ ለተመልሶ መተኛት ክፉ ተገዳዳሪ ሲሆን ማየት ተመኝቻለው ለህይዎት መተኛትና ለፈተናዎች ማለፍም እንዲሁ።
    ክበሪልኝ ሚስጥረ!

    Reply

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *