“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

As A Man Thinketh- ክፍል አንድ

by | Jul 18, 2015 | ትርጉሞች | 2 comments

“As A Man Thinketh” -By James Allen

ትርጉም- በሚስጥረ አደራው

ክፍል አንድ

“Thought and Character”

“አስተሳሰብ እና ባህሪ”

“ሰው በልቡ የሚያስበውን ሃሳብ ነው” የሚለው አባባል የሰውን ልጅ ማንነት የሚያንጸባርቅ አባባል ብቻም ሳይሆን፤ የህይወቱን መስመር እና ጉዞም የሚዳስስ  ነው። እርግጥም ሰው የሚያስበውን ሃሳብ ነው። ባህሪው እና ጸባዩ የአስተሳሰቦቹ ሁሉ ድምር ናቸው።  አንድ እጽዋት ከውስጡ ይፈካል እንጂ ፤ ከውጪ ሊፈካ አይቻለውም። የሰው ልጅ ድርጊትም በውስጡ ካለው ከድብቁ የአስተሳስብ ዘር የሚፈጠር ፍሬ ነው። ድርጊቶቻችን ሁሉ የአስተሳሰቦቻችን ውጤቶች ናቸው፤ ሃዘን እና ደስታም ፍሬዎቹ። ስለዚህ የሰው ልጅ ከራሱ የአስተሳሰብ እርሻ፤ ጣፋጩን እና መራራ የኑሮ ፍሬዎቹን ይለቅማል።

“በአይምሮዋችን ወስጥ ያሉት አስተሳሰቦች እኛ እኛን እንድንሆን አድርገውናል

በሃሳብ ብዙ ነገሮች ተሞረደዋል ተገንብተዋል

የሰው አይምሮ ክፉ አስተሳሰብ ከተዘራበት፤ ስቃይ መምጣቱ አይቀርም። መልካሙን የሚያስብ ሰው ደግሞ ደስታ እንደጥላ ትከተለዋለች”

መልካም ባህሪ እና ሰናይ ጸባይ በአጋጣሚ የሚገኙ ትሩፋቶች አይደሉም። ይልቁንም አይምሮን ትክክለኛውን ነገር እንዲያስብ በተደጋጋሚ በመግራት የሚገኝ ውጤት እንጂ። መልካም ያልሆነ ማንነት ወይም ለአውሬ የተጠጋ ባህሪ ደግሞ ከቀናነት የራቁ እና ክፉ አስተሳሰቦችን ደጋግሞ በማሰብ የሚመጣ ልክፍት ነው።

ሰው እራሱን መገንባትም ማፍረስም ይቻለዋል። በሃሳቦቹ እራሱን የሚያወድምበትን መሳሪያ ይፈጥራል፤ ወይም ደግሞ ሰላም እና ደስታን የሚያገኝበትን የኑሮ ቤተመንግስት ይገነባል። የሚያስበውን የሚመርጥ እና በእውነት ሀሳቡን የሚተገብር ሰው እራሱን ወደ ንጹህ ወደማንነት ማቅረብ ይችላል። ሃሳቦቹን እና እምነቶቹን መምረጥ ሲሳነው ግን ከእንስሳ በታች የሚያስብ ፍጡር ይሆናል። በነዚህ ሁለት የማንነት ጥጎች መካከል ሌሎች በመሃል የሚወድቁ ብዙ ማንነቶች አሉ። የሁሉም ማንነቶች ፈጣሪ ግን እርሱ ሰው ነው።

በዚህ አሁን ባለንበት ዘመን ነፍስን ከሚነኩ፤ ብርሃንን ከሚፈነጥቁ እውነታዎች መካከል፤ ይህንን እውነታ ማወቅ መታደል ብቻም ሳይሆን ፍሬያማ እና በራስ መተማመን ጭምር የሚያሳድግ ነው። ታላቁ እውነታ ይህ ነው ” ሰው የሃሳቦቹ ፈጣሪ፤ የባህሪው ቀራጭ፤ የአጋጣሚዎቹ አመልካች፤ የአካባቢው እና የእጣፋንታው ጌታ ነው” የሚል ነው።

የአስተሳሰቡ ጌታ፤ የፍቅር እና የእውቀት ባለቤት የሆነው የሰው ልጅ ለእያንዳንዱ የህይወቱ አጋጣሚ ቁልፍ አለው። ያለውን ሃይል ማወቅ ከቻለም እራሱን መሆን ወደሚመኘው ማንነት መቀየር ይቻለዋል። ሰው ሁሌም የራሱ ጌታ ነው፤ ሌላው ይቅር በደከመበት ሰዓት እራሱ ጌታ ነው። ነገር ግን በአስተሳሰብ ደካማ በሆነበት ጊዜ ሞኝ ጌታ ነው፤ ቤቱን በስርዓት ማስተዳደር እንደሚሳነው ሰነፍ ጌታ።  ህይወቱ የተመሰረተበትን  ህግ መርምሮ ሲያውቅ እና ሲረዳ ግን ብልህ ጌታ ይሆናል።

ወርቅ እና አልማዝ በብዙ ፍለጋ እና ቁፋሮ እንደሚገኙ ሁሉ፤ የሰው ልጅም ከራሱ ማንነቶች ጋር የሚቆራኙ ማንኛቸውንም አይነት እውነታዎችን ወደ ውስጥ ነፍሱን ቢቆፍር ያገኛል። የማንነቱ ፈጣሪ፤ የእጣፋንታው ገንቢ፤ የህይወቱ ጠራቢ መሆኑን ያረጋግጣል። አስተሳስቦቹን  በቅጡ ካጤነ፤ ከተቆጣጠረ፤ እና በህይወቱ ላይ የሚኖራቸውን ተጽዕኖ ማወቅ ከተቻልው፤ በትዕግስት ህይወቱን ካስተዋለ፤ የመንስኤ እና የውጤትን ሂደት ከተረዳ፤ እራስን ማውቅ ጥበብ ብቻም ሳይሆን ሃይልም ነውና፤ የእራሱ እጣፋንታ ባለቤት መሆኑን በጊዜ ሂደት ያረጋግጣል። በዚህ መንገድ ሲጓዝ ብቻ ነው “እሹ ታገኙማላችሁ፤ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል” የሚለው ህግ ፍጹም እውነት መሆኑን የሚረዳው።

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

2 Comments

  1. Geletesa Negeri

    thank you very much for sharing such golden documents

    Reply
    • Mistre

      Thank you so much! Glad you enjoyed reading it.

      Reply

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *