“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

As A Man Thinketh- ክፍል ስድስት

by | Aug 1, 2015 | ትርጉሞች | 0 comments

“As A Man Thinketh” -By James Allen

ትርጉም- በሚስጥረ አደራው

ክፍል ስድስት

አስተሳሰባችን በጤናችን እና አካላችን ላይ ያለው ተጽዕኖ

ሰውነታችን የአይምሮዋችን ባሪያ ነው። የምናስበውን አስፈጻሚ ክፍል ማለት ይቻላል። በብልህነት የመረጥናቸውንም ሆነ በደመነፍስ የምናስባቸውን ነገሮች ሰውነታችን ወደ እውነት ይቀይራቸዋል። ሰውነታችን ለበሽታ ሲጋለጥ እና ሲጠወልግ፤ ለጠወለገ አስተሳሰባችን ዋጋ እየከፈለ ነው ማለት ነው። አይምሮዋችን መልካም እና ብሩህ ሃሳቦችን ሲያስብ ደግሞ፤ ሰውነታችን ይፈካል፤ ከእድሜ ጋር እየተፎካከረ ልጅነትን ያላብሰናል።

በሽታ እና ጤና ልክ እንደሌሎች ሁኔታዎች ሁሉ ከአስተሳሰብ ጋር ጥብቅ ቁርኝነት አላቸው። ጤነኛ ያልሆኑ አስተሳሰቦች እራሳቸውን በበሽታ ይገልጻሉ። ፍርሃት ሰዎችን የጥይት ያህል ፈጥኖ ይገድላል። በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችም በፍርሃት ምክንያት እየሞቱ ነው። ለበሽታ የሚጋለጡ ሰዎችም አብዛኛዎቹ በሽታን የሚፈሩት ናቸው። ጭንቀት መላ ሰውነትን የማሟሸሽ አቅም አለው፤ ሰውነትንም ለበሽታ የተጋለጠ ደካማ እንዲሆን ያደርገዋል።

ሰዎች ደስ የሚሉ ሃሳቦችን ሲያስቡ፤ ሰውነታቸው በመልካም ሁኔታ ላይ እንዳለ ይናገራል፤ የውስጥ ደስታቸው ደስ የሚል ግርማን ያላብሳቸዋል። ሰውነታችን በቀላሉ እንደአስተሳሰባችን ይለዋወጣል። መልካም እና ክፉ አስተሳሰቦች የየራሳቸውን ተጽዕኖ ያሳድሩበታል።

ከንጹህ ልብ፤ ንጹህ ሰውነት ይገኛል፤ ከጤነኛ አስተሳሰብ ጤነኛ ሰውነት ይወለዳል። አንድ ሰው መጥፎ አስተሳሰቦችን በአይምሮው እስከያዘ ድረስ፤ ውስጡን እየመረዘ ይኖራል። የተበላሸ ህይወት፤ ከተበላሸ አስተሳሰብ የመጣ ነው። የሰው ልጅ አስተሳሰብ፤ ህይወት፤ ተግባር እና እውነታ የሚፈልቁበት ምንጭ ነው። ይህ ምንጭ ንጹህ ካልሆነ፤ ከስሩ የሚቀዱት ነገሮች ሁሉ ንጹህ አይሆኑም።

አስተሳሰብ እስካልተለወጠ ፤ ሰው አመጋገቡን ቢለውጥ በሰውነቱ ላይ ለውጥ ለማምጣት ይከብደዋል። ለራሱ የሚጠቅመውን አስተሳሰብ ሲይዝ፤ ለሰውነቱ የማይጠቅሙትን ምግቦች መመኘቱን ይተዋል። ምክንያቱም የጸዳ አስተሳሰብ፤ የጸዳ ባህሪህን ያጎናጽፋልና። ሰውነቱን መንከባከብ የሚፈልግ ሰው፤ መጀመሪያ አይምሮውን መፈተሽ እና መጋረድ ይጠበቅበታል። ውጪው ከማማሩ በፊት፤ ውስጡ ማማር ስላለበት።

ቅናት፤ ተንኮል፤ ጥላቻ እና ቂም የሰውነትን ውበት እና ግርማ የሚሰርቁ ቀማኞች ናቸው። ፈገግታ የራቀው ኮስማና ፊት እንደው ዝም ብሎ የሚመጣ ነገር አይደለም፤ ኮስማና ሃሳቦችን ከማሰብ የሚመጣ እንጂ። ለምሳሌ ዘጠና ስድስት አመት የሞላትን ነገር ግን የልጃገረድ ፊት የሚመስል ደስ የሚል ገጽታ ያላትን ሴትዮ አውቃለው። በሌላ በኩል ከመካከለኛ እድሜ በታች የሆነ ነገር ግን የሽማግሌ ገጽታ ያለው ሰውም አውቃለው። አንደኛው የጣፋጭ ህይወት ነጸብራቅ ሲሆን፤ ሌላኛው ደክሞ ያልተደሰች ነፍስ ውጤት ነው።

አንድ ክፍል የጸሃይ ብርሃን እና ንጹህ አየር ካልገባበት፤ እንደሚጨልምና እንደሚጨንቅ ሁሉ፤ ሰውነታችም የደስታ ብራሃን እና የነጻነት አየር ካልገባበት አይደምቅም። ህይወቱን በስነስርዓት እና በትክክለኛ መንገድ ለኖረ ሰው፤ እርጅና እረጋ  ያለ ሰላማዊ ሽግግር ነው፤ ልክ ጸሃይ ስትጠልቅ እንደሚታየው ድንቅ  ትዕይንት ። በቅርቡ ከዚህ አለም በሞት የተሰናበት ፈላስፋን ተመልክቼ ነበር፤ በእድሜ ብቻ ነው ያረጀው። እንደኖረው ጣፋጭ ኑሮ፤ ሞቱም ጣፋጭ ነበረች።

የታመመ ሰውነትን የሚፈውስ ድንቅ ሃኪም ቢኖር ደስ የሚያሰኙ ሃሳቦችን የሚያስብ አይምሮ ነው። የሃዘንን ጥላ መልካም ሃሳብ እና ድርጊት ያርቀዋል። ቀና ያልሆኑ ሃሳቦችን ማስብ ልምድ የሆነበት ሰው፤እራሱን በገዛ እስርቤት ውስጥ ይቆልፈዋል። በተቃራኒው፤ ደስ የሚያሰኙ ሃሳቦችን አዘውትሮ የሚያስብ ፤ ከሁሉም ነገር ውስጥ መልካሙን ለመመልከት የሚጥር ሰው እራሱን ከገነት ደጃፍ ያደረሳል። በቀን በቀን በሰላም ውስጥ የሚመላለስ ሰው ለሌላውም ሰላምን የሚሰጥ የሰላም መልዕክተኛ ነው።

 

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *