“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“As A Man Thinketh” – ክፍል ሰባት

by | Aug 4, 2015 | ትርጉሞች | 1 comment

“As A Man Thinketh” -By James Allen

ትርጉም- በሚስጥረ አደራው

ክፍል ሰባት

አስተሳሰብ እና አላማ

አስተሳሰባችን ከአላማ ጋር እስካልተዛመደ ድረስ ግቡን አይመታም። የብዙ ሰዎች አይምሮ በኑሮ ወጀብ ከወዲያ ወዲህ ይንገላታል። አላማቢስነት ከደካማ ማንነት የሚመነጭ ነው። ከወዲያ ወዲህ በሃሳብ በመዋዠቅ ሰው የኑሮውን ጸጥታ ያደፈረሳል።

በህይወታቸው አላማ እና ግብ የሌላቸው ሰዎች፤ በቀላሉ ለጭንቀት፤ ለፍርሃት፤ ለችግር እና እራስን ዝቅ ለማድረግ የተጋለጡ ናቸው። እኒህ ሁሉ የደከማ አስተሳሰብ እና ባህሪ መገለጫዎች ሲሆኑ ወደ ሃጥያት፤ ወደ ወድቀት እና ጥፋት የሚመሩ የጥፋት መንገዶችም በመሆን ያገለግላሉ።

ሰው በልቡ የሚኖርለትን አላማ መጸነስ መቻል አለበት። መጸነስ ብቻም ሳይሆን ለፍሬ ማብቃትም ጭምር። አላማውንም የአስተሳሰቡ ማገር አድርጎ ሊይዘው ይገባል። ምናልባት አላማው መንፈሳዊ አልያም ቁሳዊ ሊሆን ይችላል፤ ያም ሆነ ይህ ግን ትኩረቱን ሁሉ ከፊቱ ላኖረው አላማ ማዋል አለበት። አላማው ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር መሆን ነው፤ እራሱንም ለአላማው ተገዢ ማድረግ ይገባዋል። ያኔ አይምሮው ከወዲያ ውዲህ በምኞት አይዋዥቅም። አላማ እራስህ በቁጥጥር ስር ለማድረግ የሚረዳ ወርቃማ መንገድ ነው። አላማ ያለው ሰው፤ ደጋግሞ ቢወድቅም እንኳን (ሽንፈትን ድል እስኪነሳ መውደቁ አይቀርም) በወደቀ ቁጥር መነሳቱ፤ ጠንካራ ማንነቱን ስለሚመሰክር ስኬታማ ነው ሊባል ይችላል።

ደካማ ነፍስ ያለው ሰው ድክመቱን እንደ እውነት አድርጎ መቀበል ከቻለና፤ ጥንካሬ በትዕግስት እና በጥረት እንደሚገኝ ካመነ፤ እራሱንም አሳምኖ ለለውጥ ከተንሳ፤ በእርግጠኝነት ነፍሱን ጠንካራ ማድረግ ይቻለዋል። ልክ በአካል ደካማ የሆነ ሰው ሰውነቱን በእንቅስቃሴ ማጠንከር እንደሚችል ሁሉ።

ከአላማቢስነት ጎዳና አርቆ እራስን ለአላማ ማስገዛት፤ ውድቀትን እንደ መሸጋገሪያ ከሚቆጥሩ ስኬታማ ሰዎች ጎራ ይቀላቅላል። እኒህ ሰዎች ከስኬት ብቻም ሳይሆን ከውድቀትም ትርፍ ለማግኘት የሚጥሩ ብልሆች ናቸው። በትልቁ የሚያስቡ፤ ያለፍርሃት የሚተገብሩ፤ በስኬት የሚያጠናቅቁ ሰዎች ጭምር።

ሰው በልቡ አላማውን ከጸነሰ በኋላ ወደ ቀኝ ወደ ኋላ ሳይወላውል፤ ወደ ግቡ የሚያደርሰውን ቀጥተኛ መንገድ ሊያሰምር ይገባዋል። ወደ ስኬት መንገድ የጀመረ ሰው ፤ ጥርጣሬ እና ፍርሃትን ከመንገዱ ሊያርቃቸው ይገባል። ምክንያቱም ፍርሃት እና ጥርጣሬ ወደ አላማ የሚያደርሰውን ቀጥተኛ መንገድ የሚያጨናግፉ እንከኖች ናቸው። የቀናውን ያጎረብጣሉ። በፍርሃት እና በጥርጣሬ ምንም አይነት ስኬት አይታሰብም። ሁሌም ወደ ውድቀት የሚያደርሱ፤ ቁልቁል ጎዳናዎች ናቸው። የውደቀትን ጎዳና የሚያፈርሱት ፤ አላማ፤ ጠንካራ አስተሳሰብ እና ቁርጠኝነት ናቸው።

አላማን የማስፈጸም ፍላጎት፤ የሚበቅለው “ይቻላል” ከሚል ስሜት ነው። ፍርሃት እና ጥርጣሬ የእውቀት ጠላቶች ናቸው። ሰው የፍርሃትን እና ጥርጣሬን ዘር፤ ከማቆጥቆጣቸው በፊት ማስወገድ ካልቻለ፤ በእየአንዳንዱ እርምጃ የገዛ እራሱን እየጠለፈ ይጥላል። ፍርሃትን እና ጥርጣሬን ድል መንሳት የቻለ ሰው፤ ውድቀቱንም ድል ነሳ ማለት ነው። ሃሳቦቹ ሁሉ ያለፍርሃት ከሃይል ጋር ይጣመራሉ፤ እክሎቹን እና ውጣ ውረዶቹንም በብልሃት ያልፋቸዋል። አላማዎቹ ወቅታቸውን ጠብቀው ይዘራሉ፤ ፍሬም ያፈራሉ፤ ሃሳቡን ፍሬ በማያፈራ መጥፎ መሬትም አይዘራቸውም።

ከአላማ ጋር የተሳሰረ አስተሳሰብ እጅግ ግዙፍ ሃይል ነው። አሁን ካለበት ሁኔታ ለተሻለ ኑሮ እና አስተሳሰብ እራሱን ያዘጋጀ ሰው፤ አይምሮውን በብልሃት የሚያሰራ ለስኬት የተዘጋጀ ነው።

 

 

 

 

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

1 Comment

  1. kenyaa

    የምትፅፍያቸውን ፅህፈቶች አንብቤያለሁ በጣም የሚያስመስግንሽ መሆኑን ስገልፅልሽ በደስታ ነው ያንቺን ፔጅ ከጎበኘሁ ለት ጀምሮ ያንቺን አይነት አስተማሪ መልዕክት ያዘሉ ፔጆችን እንደጎበኝ ብርታት ያገኘውት ካንቺ ፔጅ ነው !!!!

    Reply

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *