“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

ፍቅር ፍትህና መሪነት

by | Jun 14, 2020 | መነቃቂያ inspiring stories | 5 comments

(በሚስጥረ አደራው)

ፍቅር በፍትህ አፈር ላይ የምትበቅል ተክል ናት። የፍትህ አፈር ሚዛናዊ ነው፤ ያልተመጣጠነ ነገር ሁሉ ሚዛኑን ይደፋዋል። ከልክ በላይና በታች የሚሰጥ ነገር ሁሉ ተክሉን ይገለዋል። ሁሉንም ነገር በልኩና በመጠኑ፤ ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ ሲሆን፤ ፍቅር ታብባለች።

The Road less Traveled  በተሰኘው መጽሃፍ ላይ ጸሃፊው ፍቅርን እንዲህ ውብ አድርጎ ከፍትህና ከመሪነት ጋር ሽምኖ አቅርቦታል

“ፍቅር ዝም ብሎ መስጠት አይደለም

በፍትሃዊ መልኩ ቢሰጥም፤ በፍትሃዊ መልኩ ይከለክላል

በፍትሃዊ መልኩ ሲያሞግስ፤ በፍትሃዊ መልኩ ይገስጻል

በፍቅር ውስጥ ፍታሃዊ ጥል፤ ግብግብ፤ ፍጥጫ፤ ግፊት እንዲሁም ጉተታ፤ ባጠቃላይ ፍትሃዊ ትግል ይታያል

ከሁሉም በላይ ፍቅር ማለት መሪነት ነው”- M. Scott Peck- The road less Traveled

ከላይ የሰፈረው የፍቅርና የፍትህ ትስስር እጅግ በጣም ወሳኝ ነጥብ ይመስለኛል። ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ሰዎች በምንሰጠው ፍቅር ውስጥ የምንወስናቸው ውሳኔዎች ሚዛናቸውን የጠበቁ መሆን አለባቸው። ከጥላቻ በላይ በፍቅር ስም ብዙ ስህተቶች ይፈጸማሉ። ለእኛ ስህተቶቻችንን በጥላቻ ላይ ማሳበብ ቀላል ውሳኔ አይደለም፤ በአንጻሩ በፍቅር ላይ የራሳቻንን ሚዛን አልባነት ግን በቀላሉ እናላክክካለን። በመውደድ ውስጥ ሊኖር የሚገባውን ሚዛናዊነት ስለምንረሳ፤ ወይ አብዝተን እንሰጣለን አልያም አብዝተን እንከለክላለን።

ፍቅር የሚጀምረው ከራስ ነው። ሰው የሌለውን ነገር ለሌሎች ልስጥ ቢል ስጦታው በስጦታ የተጠቀለለ ባዶ ሳጥን ነው። እኔም ለዚህ ጽሁፌ ማተኮር የምፈልገው ለራሳችን በምንሰጠው ፍቅር ላይ ነው።ምክንያቱም ለሌሎች የምንሰጠው ፍቅር ለራሳችን የሰጠነው ፍቅር ነጸብራቅ ስለሆነ። ለራሳችን ምን ያህል ፍትሃዊ ነን? እራሳችንን በመውደድ ሰበብ አብዝተን ለራሳችን የምንሰጣቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? የምንከለክላቸውስ? ተገቢውን ምስጋናና ተግሳጽ ለራሳችን እናደርሳለን ወይ? ከህይወት ጋር ፍትሃዊ ትግል እናደርጋለን? ከምንም በላይ ኑሮዋችን በማን እየተመራ ነው?

ጽሀፊው ፍቅር ማለት መሪነት ወይም “leadership” ነው ያለበትን ምክንያት እኔ የተረዳሁት እንዲህ ነው። መሪነት ጥበብ ነው። አንድ ሰው መሪ ከሆነ ሌሎችን አይከተልም፤ የገዛ ልቦናውን ከአይምሮው ጋር አጣምሮ የራሱን መነገድ ቀዶ ይሄዳል። መሪ ቀድሞ የሚጓዘው ሌሎች በእምነትና በተስፋ እንዲከተሉት ሲል ነው። የደከሙ ነፍሶችን ለማንቃት ሲል መሪ ያልተሞከረውን ይሞክራል።ናፖሊዮን ሂል መሪ ማለት የተስፋ አከፍፋይ ነው ስል ይገልጸዋል። መሪ ተስፋ ሰጪ ስለሆነ፤ የሚኖረውም በትስፋ ነውና። የመሪነት ዋነኛ መለኪያዎቹ፤ ውሳኔ መስጠት መቻሉ፤ ሰዎች በራሳቸው እንዲያምኑ ማበረታታቱ፤ ሃላፊነት መውሰድ መቻሉ፤ ተጽዕኖ ማምጣቱ፤ በስተመጨረሻም ነገሮችን ጀምሮ መጨረስ እንዲሁም ውጤት ማሳየቱ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ባህሪያት እውነትም የፍቅር ምልክቶች ናቸው።

አንድ መሪ በአንድ ንግግሩ ላይ ይህንን ተናግሮ ነበር

“እንደ መሪ ለራሴ እውነተኛና ታማኝ መሆን ይገባኛል። አላማና እይታዬ ውስን ለሆነ አስተሳሰብና ማንነት እንዲሰግዱ መፍቀድ የለብኝም። ይልቁንም እኔ አላማና እይታዬ ወዳሉበት ከፍታ ከፍ ማለት አለብኝ እንጂ” ።

መሪነት እውነተኛነትን እና ታማኝነት በእጅጉ ይጠይቃል። እዚህ አለም ላይ ተሳክቶልን መኖር የምንችለው የራሳችን ህይወት መሪዎች መሆን ስንችል ብቻ ነው። መሪነት ብዙ ሃላፊነት ስለሚጠይቅ ለብዙዎቻችን ከባድ ነው። ምክንያቱም እኔ የህይወቴ መሪ ነኝ ብለን የተነሳን ቀን፤ እንደመሪ መኖር እና መስራት ስለሚጠበቅብን። እንደመሪ፤ ሰው ሳንጠብቅ ወደፈለግነው መንገድ መጓዝ፤ ሌሎች ባያምኑብንም እንኳን በራሳችን ማመን መቻል፤ መንገዱ ሲፈትነን አይዞህ/ሽ ባይ ሲጠፋ እራሳችንን ማበረታት፤ በምናደርጋቸው ጥቃቅን ነገሮች ሌሎች ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ማምጣት እንዲሁም የጀመርነውን መንገድ መጨረስ ሊኖርብን ነው። የመሪነት ሃላፊነቱና ስራው ከባድ ቢሆንም ትርፉ ከምንከፍለው ዋጋ በእጅጉ የላቀ ነው። ከምንም በላይ እርሳችንን በመምራት ሂደት ውስጥ ለራሳችን ያለን አመለካከት ይቀየራል። በራስችን ላይ ያለን እምነት ይጨምራል፤ የሚገጥሙንን ፈተናና ችግሮች ተደብቀን ሳይሆን ተጋፍጠን እናልፋቸዋለን። ሁሌም ማሸነፍ አይኖርም፤ ነገር ግን የሰው ልጅ በቻለው መጠን እስከሞከረ እና እስከጣረ ድረስ መሸነፍና ማሸነፍ ትርጉም አይኖራቸውም። የእኛ ሃላፉነት ለህይወት በቂ ትኩረት መስጠት ነው። አዎ በቂ ትኩሩት መስጠት።

ናትናዬል ብራንደን የተባለው ሳይኮሎጂስት በሽተኞችን በሚያይበት ክሊኒኩ ውስጥ አንድ አባባል ግድግዳው ላይ ለጥፎ ነበር “No one is Coming” የሚል፤ ማንም አይመጣም ማለቱ ነው። ከእለታት አንድ ቀን ሰዎችን ሰብስቦ ምክር በሚሰጥበት ወቅት አንዱ “ ዶ/ር ብራንደን  “ማንም አይመጣም” ብለህ ለጥፈሃል ነገር ግን ስንቸገር አንተ መጥተሃልና የለጠፍከው ውሸት ነው አለው። ዶክተሩም “እኔም የመጣሁት ማንም አይመጣም ብዬ ልነግራችሁ ነው” ስል መልሶላቸዋል።

ለህይወት፤ ለእራሳችን እና ለሎች ሰዎች ፍቅር ካለን የመሪነትንም ሃላፊነት መቀበል  ግድ ይለናል። መውደድ ከባድ ሃላፊነት ነው። ስራችንን እና አስተዋጽዎቻችንን በመገምገም፤ በልባችን ውስጥ ያለውን የፍቅር መጠን መለካት እንችላለን። የፍቅር መንገድ እረጅም፤ ፈታኝ፤ አድካሚ፤ ብቸኝነት የተሞላው መንገድ ነው። ቢሆንም ከተሻለው ስፍራ የምያደርሰን ትልቁ ሃይል ፍቅር ነው። ለፈጣሪያችን፤ ለራሳችን፤ ለህይወት እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች ያለን ፍቅር ወደፊት የሚያራምድ ጉልበት አለው። በስተመጨረሻ ለዚህ ሃሳብ መነሻ ከሆነኝ መጽሃፍ ውስጥ የሰፈረውን የፍቅር ትርጉም ላካፍላችሁና ጽሁፌን ልቋጭ።

” Love is defined as the will to extend oneself for the purpose of nurturing one’s own or another’s spiritual growth”- M Scott Beck

” ፍቅር ማለት እራስን ለራስና ለሌሎች ሰዎች የመንፈሳዊ እድገት ፈቃደኛ ማድረግ ነው” ይላል። በዚህ አባባል ውስጥ ሁለት ወሳኝ ቃላቶች አሉ “ፈቃድ” ወይም “will” እንዲሁም “መንፈሳዊ እድገት” ወይም “Spiritual Growth”። እኒህ ቃላቶች ከላይ ካነሳንቻው የፍትህና የመሪነት የፍቅር ሚና ጋር በጣም ይቆራኛሉ ብዬ አስባለው። ፍቅር በፈቃድ ላይ የተመሰረተ ስሜት ነው፤ ሰው ፍትሃዊ የሚሆነውም ሲፈቅድ ብቻ ነው። በሌላ መልኩ መንፈሳዊ እድገት ወደፊት መጓዝን፤ ሃላፊነትን ወስዶ መቆምን ፤ በሌሎች ሰዎች አዎንታ ሳይሆን በእራስ እውነታ ላይ ጸንቶ መቆምን ይጠይቃል። እኒህ ደግሞ የመሪ ባህሪያቶች ናቸው። ስለዚህ ለእራስችንም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ፍቅር አለን ካልን፤ የፍትህ፤ የእድገትና የመሪነት ባህሪያቶቻችንንም መፈተሽ  ይኖርብናል።

(ከእረጅም ግዜ በኋላ ወደዚህ ገጽ ስለመጣሁኝ ደስ ብሎኛል። ሳይጽፍ የከረመው ብዕሬና ብዕር ሳይጨብጡ የከረሙት እጣቶቼ እየፈተኑኝ የጻፍኩት ጽሁፍ ነው። ቢሆንም ሃሳብ መቆስቆሻ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለው።)

መልካም ሳምንት!

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

5 Comments

  1. hirsi bashir

    Long time,, tefash eko astemariye.

    Reply
  2. abreham

    meri yeseral enji ayeweledem lezehem new bezu meriwoch yemayesakalachew beteley Africans.yetesera meri gen ezebun yezo yewetal wed terara weyem wed kefeta lezehem new muse tesereto new lelam.

    Reply
    • Mistre

      Thank you so much Abreham!

      Reply
  3. Isaac Abraha

    እናቴ ነፍሷን ይማረውና “ፍቅርን እንዳዳምጥ ትነግረኝ ነበር
    በፍቅር ካመንክ መሆን ወደምትፈልገው ነገር ይመራሃል”
    ሌላው የሚገርመው ጥላቻ የሚመጣው ከፍቅር በኃላ መሆኑ ያሳዝናል

    Reply
    • Mistre

      በጣም አመሰግናለሁ! እውነት ነው በፍቅር ካመንን መሆን ወደምንፈልገው ይመራናል።

      Reply

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *