“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

ጭንብሌ

by | Jul 2, 2015 | Guest writer-እንግዳ ጸሃፍት | 1 comment

ጭንብሌን የማወልቀው ገና ከቤቴ በራፍ ላይ ስደርስ ነው። ማውለቅ ባልፈልግም እንኳን እራሱ ከላዬ ላይ ለመውረድ ይታገላል። ጭንብሌን በፍጹም ቤቴ ውስጥ ማድረግ አልችልም…..ብፈልግም ስላለመድኩት ይከብደኛል። ሰዎች የሚወዱኝ በጭንብሌ ነው፤ ስለዚህ ከቤቴ ውጪ  ያለጭንብሌ መንቀሳቀስ አይሆንልኝም። በጭንብሌ ብዙ ወዳጆችን አፍርቻለው፤ ብዙ ዝና ተጎናጽፌአለው፤ ብዙ ምቾት አግኝቻለው። ለኔ ጭንብሌ አዲስ ህይወት ቀይሶልኛል፤ ከባድ የነበረው ጎርበጥባጣውን ጎዳና፤ ቀናም ባይሆን የተሻለ አድርጎልኛልና።

ጭንብሌ እውነተኛ መልክ ከመምሰሉ የተነሳ ይሁን ለምደውት ሰዎች እምብዛም አይጠረጥሩትም። በዛላይ እንደ እስስት የመቀየር ባህሪ ስላለው በየቦታው ቦታውን እየመሰለ ኑሮዬን አቅልሎታል። በእውነተኛ መልኬ የማላገኘውን ተቀባይነት ጭንብሌ በቀላሉ አስገኝቶልኛል። ግን ዘወትር እጅግ የሚረብሹኝ ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛው ዘወትር በጭንብል የሚሸፈነው ፊቴ ማታ ቤቴ ስገባ የሚያሳየኝ የተከፋ ገጽታ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሰዎች ሁሉ በእውነተኛ ፊታቸው እየተንቀሳቀሱ የኔ በጭንብል መዞር ከራሴ ጋር እንዳልግባባ አድርጎኛል። ግን ያለ ጭንብሌ እንዴት ልሁን?

ዛሬም ውሎዬን ጨርሼ ከቤቴ እንደደረስኩ ነበር ጭንብሌን ከላዬ ላይ ያወለቅኩት። በፈገግታ ተሞልቶ የነበረው የጭንብል ፊቴ ሃዘን በተሞላው እውነተኛ ፊቴ ተለውጦ ሳየው፤ እውነታው ተናነቀኝ። ሁሌም ቢሆን ከግርግሩ አለም ወጥቼ ከራሴ ጋር ወደምፋጠጥባት ትንሿ አለም ስገባ ግር ይለኛል። ግርታ ብቻም ሳይሆን ድብታም ጭምር። ጭንብሌ ከራሴ ሲወልቅ ፍርሃት ይይዘኛል፤ የሰው ፍርሃት ሳይሆን የገዛ እራሴን ሽሽት ፍርሃት። እራሴን ለማረጋጋት እሞክራለው…..ውስጤን ለማሳመን

በጭንብሌ- ከማንም ተስማምቼ እኖራለው፤ ሰዎች ስሜቴን ማንበብ ስለሚሳናቸው፤ ፊቴ ቢጨማደድ እንኳን ጭንብሌ በፈገግታ ይሸኛቸዋል። የጭንብሌን ፈገግታ የሚያዩ ሰዎች፤ሁሌም ደስተኛ እንደሆንኩኝ ስለሚያስቡ ከእውነተኛው ማንነቴ ሳይሆን ከጭንብሌ ጋር በደንብ ይግባባሉ። ስለዚህ ሁሌም ውስጤ ሊወቅሰኝ ሲነሳ እንዲህ ብዬ እመልስለታለው

“አንተ እንደጭንብሌ ታገለግለኛለህ? መስለህ መኖሩን ታውቅበታለህ? ከሁሉም ሰው ጋር እንደጭንብሌ መልክ እየቀየርክ መቀላቀል ትችላለህ? እውነተኛ ማንነቴን ይዤ አይቼዋለው፤ ሃቅን ይዞ መጋፈጥ ትልቅ ወኔ ይጠይቃል፤ የወደድኩትን ወደድኩ፤ የጠላሁትን ጠላው ማለት ቀላል ነው? ከልብህ እሺ ብሎ መፍቀድ፤ ካልተመቸኝ ደግሞ እምቢ ማለት አይከብድም? በጭንብል የተሸፈንኩት እኮ ወድጄ አይደለም፤ ኑሮዬን ለማቅለል ነው። የሚሰማቸውን የሚናገሩ ሰዎች፤ የፈለጉትን ኑሮ የሚመርጡ፤ እንደሰው ሳይሆን እንደራሳቸው የሚኖሩ ሰዎች ያላቸው ጥንካሬ አለህ?” እያልኩ እራሴን እወቅሰዋለው፤ ዛሬም ወቀስኩት። ከራሴ ጋር መጨቃጨቁን  ሲሰለቸኝ ከጎኔ ያለውን መጠጥ አንስቼ መጨለጡን ጀመርኩ ምናልባት ትንሽ ድፍረት ቢሰጠኝ…

በመስኮት ውጪውን እየተመለከትኩ ብዙ ቆየው፤ አልኮሉ የውስጤን ጩኸት ሲያስታግሰው ይታወቀኛል። ጩኸቱ ታግሶ በምትኩ በቀጭኑ የሚወጣ የወቀሳ ድምጽ ተሰማኝ። ከወቀሳው ጋር እልህ ተቀላቅሎበታል። ስካር የለኮሰው ወኔ የልብ ልብ ሰጠኝ፤ ወደ መስታወቱ ቀረብኩኝ፤ ያለጭንብሌ ሰዎች ቢያውቁኝ ምን ይሆናል? ጓጓሁኝ…ብርጭቆዬን ሞልቼ ጎሮሮዬን እየሰቀጠጠው ጨለጥኩት። እልህ ድፍረት፤ ወኔ፤ ጉጉት…..እየተግተለተሉ ወደጭንቅላቴ ሲዘምቱ ታወቀኝ። ጭንብሌን አንስቼ በመስኮት ቁልቁል ወረወርኩት አበቃ!!!

ሲነጋ መጠጥ ያናወዘው ጭንቅላቴ እየከበደኝ ተነሳው። የመጀመሪያው ስሜት ድንጋጤ ነበር፤ ማታ ምን አደረግኩኝ….ቀስ እያለ ሁሉም ነገር እንደህልም ትዝ አለኝ። ጭንብሌን ጥየዋለው….እውነተኛ ማንነቴን ይዤ፤ ማስመሰሉን ትቼ፤ ለእውነት ለመኖር ወሰኩኝ ማለት ነው?

ወደጎዳናው ስወጣ ትንሽ ግር አለኝ። ሰው እራሱን ሲሆን ብዙ ሃላፊነቶች አሉት፤ እውነት በብዙ ሰዎች ዘንድ ለመዋጥ የምትከብድ እንክብል ናት። ዛሬ ያለጭንብል ስዞር የሚገርም እውነት አየው፤ለካ አብዛኛው ሰው በጭንብል የተሸፈነ ነው? እኔ ደግሞ እኔ ብቻ ነኝ እያልኩኝ እራሴ ስወቅስ መክረሜ። በማስመሰል እርስ በርሳችን እየተሸነጋገልን የምንኖር….ግን ወደን  አይደለም፤ ከሰው ለመኖር ስንል ያጠለቅነው ጭንብል ነው። ግን በዛ ውስጥ የራሳችን ንጹህ ማንነት እየደበዘዘ ይሄዳል…..ያለ ጭንብል መኖር ድፍረት እና እራስን መሆን ይጠይቃል።ለዚህ ነው የማይጥመንን ሃሳብ በአደባባይ ተስማምተን፤ ቤታችን ጭንብላችንን ስናወልቅ የምናጉረመርመው፤ ሰውን በፊቱ አመስግነን ጭንብላችን ሲወልቅ ከአፈር የምንደባልቀው… ባደባባይ የሚመሰገኑ ጥንዶች በጓዳ ጭንብላቸው ሲወልቅ እሳት እና ጭንድ የሚሆኑት…..ምን ይደረግ። ግን ምንም ቢከብድ እንኳን ያለጭንብል መኖር እንዴት ነጻነት ይሰጣል?…..

 

 

 

 

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

1 Comment

  1. Tariku

    what an amazing title ”chinble’…. hv no comment..just likkker!!!!

    Reply

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *