“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

ያልተፈተሹ ባህሪያት

by | Jul 19, 2018 | Guest writer-እንግዳ ጸሃፍት | 1 comment

(በሚስጥረ አደራው) 

“ትዕግስት ስጠኝ ብለን ስንጠይቅ፤ የሚሰጠን እረጅም ሰልፍ ነው” ትላለች ጸሀፊ ትሬሲ ማክሚላን። ትዕግስትን ስንጠይቅ የሚሰጠን ትዕግስትን የምንለማመድበት መድረክና ትዕግስትን የምናዳብርባቸው ሁኔታዎች እንጂ ትዕግስት ልክ እንደተሰጥዎ ከላይ አይቸረንም። ለዛሬ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ ሀሳብ እንደሚከተለው ነው።

አንዳንዴ እራሳችንን ባላሰብነው ሁኔታ ውስጥ እናገኘውና ከራሳችን የማንጠብቀው ባህሪ ሲንጸባረቅብን እንደነግጣለን። ለወትሮ እኮ እንዲህ አልነበርኩም በማለት ግራ ይገባናል። ተሳድበን የማናውቅ ሰዎች በሆነ አጋጣሚ ሌላውን ሰው ስናጥረገርገው፤ ትዕግስተኛ ነን ብለን የምናስብ ሰዎች ቀጠሮዋችን እረፈደ ብለን የታክሲውን ሹፌር ስናመናጨቀው፤ ቂመኛ አይደለሁም ስንል የከረምን ሰዎች የወደድነው ሲከዳን ለበቀል ስናደባ፤ በደላችንን ይቅር በለን እያልን ጠዋት ማታ እየጸለይን የበደሉንን ሰዎች ይቅር ማለት ሲከብደን፤የሌሎች ሰዎች ማግኘት ያስደስተናል የምንል ሰዎች እኛ የተመኘነውን ሌላው ሰው ላይ ስናየውና ሲከፋን፤ ፈራጅ አይደለንም ስንል ከርመን የእኛ ህልውና ሲነካ የፍርድ ወንበር ላይ ቁጢጥ ስንል፤ ባህሪያችን ለገዛ እራሳችን እጅግ ግራ ያጋባል።

ማንነታችን የሚገለጸው እኛ ስለራሳችን ባለን አመለካከት ወይም ሌሎች ሰዎች ስለኛ ባላቸው አመለካከት ሳይሆን፤ እኛ ለሁኔታዎች በምንሰጠው ምላሽ ነው። ሰው እንቃለው የሚል ሰው ባያጋጥምም ፤ ሰው እጠላለሁ የሚል ሰው ስምተን ባናውቅም ሰው የሚንንቅና የምንጠላ ሰዎች ግን አንጠፋም። ከእኔ ከእራሴ ጭምር በውስጣችን መጥፎ ስሜት ያድራል ብለን ማሰቡ ይከብደናል፤ ይከብደናል ብቻም ሳይሆን ለማሰብም አንፈልግም። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። “እኔ” ብለን የምንጠራው ማንነት በአብዛኛው የተገነባው ባልተፈተሹ ባህሪያቶቻችን ነው። ስለራሳችን ስናወራ በአብዛኛው የምናወራው በሀሳብ ስለገነባነው ማንነት እንጂ፤ በተግባር ስለምነተገብረው ባህሪዎቻችን አይደለም።

እኔ እንዲህ ነኝ ብሎ በድፍረት መናገሩ ከባድ የሚሆነውም ለዚህ ነው፤ ሁላችንም ያልተፈተኑ ባህሪያቶችን አጭቀን ስለምንቀሳቀስ። አብዛኛው ባህሪያቶቻችንና አስተሳሰቦቻችን በቲዎሪ ደረጃ እንጂ በሙከራ የተረጋገጡ አይደሉም። መልካምነታችን፤ ትዕግስተኛነታችን፤ ፍትሃዊነታችን፤ ሰው አክባሪነታችን፤ እውነተኛነታችን ተገቢውን ፈተና አላለፉም። ፈተና ስል እውነተኛ ባህሪዎቻችንን እንድናጸባርቅ የሚያስገድዱን ሁኔታዎችን ነው። ጊዜ ስለተረፈን ከኋላችን ያለውን ተሰላፊ ከፊታችን ስላስቀደምነው ትዕግስተኛ ልንባል እንችላለን? በፍጹም!!! የማንኛችንም መልካምነትና ጥንካሬ በመልካም አጋጣሚዎች ሊረጋገጥልን አይችልም። በፈተናዎችና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የምናሳያቸው ባህሪያቶች ይበልጥ እኛን ይገልጹናል።

ለዚህ ነው አንዳንዴ ውሳኔዎቻችንና ድርጊቶቻችን የሚያስደነግጡን። ተፈትነን ያገኘናቸው ባህሪዋቻችን ስላልሆኑ ልንጠቀምባቸው በሚገባን ቦታ ይጠፉብናል። ይህንን ማወቁ ምን ይጠቅምናል? ለሁለት ነገር ይጠቅመናል ብዬ አስባለው። አንደኛው ከውሸተኛ ማንነት ቀስ እያለ ያላቅቀናል፤ ሙሉ በሙሉ መላቀቅ ለሰው ልጅ ቢከብድም። የሚሰማንን ስሜት በካድን ቁጥርና “እኔ እኮ እንዲህ አይደለሁም” በማለት እራሳችንን በተከላከልን ቁጥር ባህሪያችንን ማሻሻል አስቸጋሪ ይሆንብናል። ከእራሳችን ጋር እየተቆራረጥን በቅዠት አለም ውስጥ መኖሩን እንለምደዋለን።በሌላ በኩል ማንነትና ባህሪያችንን ለሁኔታዎች ከምንሰጠው ምላሽ ተነስተን መዳኘት ከቻልን፤ ከእውነተኛ ምንነታችን ጋር እንቀራረባለን። የትኛው ባህሪያችን ላይ ይበልጥ ማሻሻል እንዳለብን ግልጽ ይሆንልናል። ስለራሳችን ባህሪ እርግጠኛ ሆኖ መናገሩ የሚያስከፍለው ዋጋ አለ፤ እሱም ወደ እውነት የሚወስደውን ጎዳና ያጠብብናል።እውንተኛ ማንነታችንን ለማወቅ ከፈለግን ስለራሳችን የምናስበውን ሳይሆን፤ ለሁኔታዎችና ለአጋጣሚዎች የምንሰጠውን ምላሽ ልናስተውል ግድ ይለናል። ሁለተኛው ጥቅም “እኔ ብሆን ኖሮ” በሚለው የፍርድ ዱላ እርስ በራሳችን ከመፈነካከት ያድነናል።

“ የሰው ባህሪያት በሁኔታዎችና በአጋጣሚዎች አይፈጠርም፤ በሁኔታዎችና በአጋጣሚዎች ይጋለጣል እንጂ”- ዚግ ዚግለር

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

1 Comment

  1. Bruktya

    በጣም ድንቅ ነው ።እኛነታችን የሚገለጸው በምናልፍበት በሕይወት ውጣ ውረድ እንጂ እኔ ደግ ነኝ ቸር እናም ሌላ ተጨማሪ ማንነት እራሳችን እየሳልን ማቅረብ ትክክለኛ ማንነት እንዳልሆነ በሐሳብሽ ተስማምቻለሁ ። እንደ ነጠረ ወርቅ እኛም በፈተና የተፈተሸ ማንነት ሊኖረን ይገባል ።ያኔ ማንነት ብቅ ይላል ትእግስተኛ ነኝ አይደለሁም ከዛ በሖላ ነው ።

    Reply

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *