“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

የተጨናገፉ ጽንሶች

by | Mar 16, 2015 | Guest writer-እንግዳ ጸሃፍት | 0 comments

ምጥ ይመስለኛል….ህመሙ የማያቋርጥ ሆነብኝ ። የመጀመሪያ ልጄን ነው ያረገዝኩት። እርግዝና እንደሚከብድ ባውቅም እንዲህ ይከብዳል ብዬ እንኳን  አልጠበቅኩም ነበር። በዚህ አይነት ሶስት አራት የሚወልዱ ሰዎች እጅግ ይደነቃሉ። ጎኔን እየትጠዘጠዘኝ ነው…….ከሰዎች እንደሰማሁት ምጥ የሚባለው ከባዱ ህመም የሚመጣው ዘጠነኛው ወር ላይ ነው…ውጋት፤ ቁርጠት፤ ፍልጠት….ህመሞች ሁሉ የተደበላለቁበት ስቃይ ነው አሉ። አሁን  የሚሰማኝ ስሜት ምጥ ይሆን እንዴ?……ምጥ ባይሆን እንኳን፤ ያሁኑን ህመም አይቼ ምጥ ማለት ምን እንደሆነ መገመቱ እራሱ በጣም ከበደኝ:: በዛ ላይ አራሽ የለኝ፤ ባል የለኝ፤ ብቸኛ እርጉዝ። ስለ እርግዝና በቅጡ የሚያስረዳኝ የለም።ድንገት የሰፈራችን አዋላጅ አቶ “ተስፋ”  ትዝ አሉኝ፤ ምን አልባት ቢርዱኝ።

ያለልኩ ያፈጠጠውን ሆዴን አቀፍድዴ፤ ወደ አቶ “ተስፋ” ቤት አዘገምኩ። አቶ “ተስፋ” ጥሩ አዋላጅ ናቸው። አንዳንድ ሴቶች ግን ይጠሏቸዋል ሲባል ሰምቻለው። ማስወረድን ስለማይደግፉ ነው አሉ። እኔ የምኖርበት አካባቢ ፤ ማስወረድ ብርቅ አይደለም፤ ሲጀመር ማርገዝ የሚፈልግ የለም፤ ሲቀጥል …መውለድ የሚፈልግ የለም። ህጻናት እራሱ ከስንት አንዴ ነው የሚታዩት …..በቃ እርግዝና ይፈራል።

የአቶ “ተስፋ” ቤት ፈጽሞ ተዘግቶ አያውቅም፤ እንደ ቤተክርስትያን ማንም ሲመላለስበት ይውላል። እኔ ስገባ እንዳጋጣሚ ማንም አልነበረም፤ ደስ አለኝ። ምክንያቱም ሰው ሰማኝ አልሰማኝ ብዬ ሳልሳቀቅ እየተሰማኝ ያለውን ስሜት እነግራቸዋለው። አቶ “ተስፋ”፤ አካላቸው ሳይሆን አይኖቻቸው እድሚያቸውን ይናገራሉ። ነፍሳቸው ሺህ አመት እንደኖረች አይኖቻቸው  ያሳብቁባቸዋል…..እሳቸው ግን ከዘመነው ጋር ልዝመን …..ካረጀው ጋር ላርጅ፤ የሚሉ አይነት ቢጤ ናቸው።

“ደህና ዋልሽ ልጄ” አሉኝ…..አቶ “ተስፋ” ጽንስ ሲበዛ ይወዳሉ…..እጅግ በጣም ይወዳሉ

“ደህና ……ትንሽ ምጥ ቢጤ ሳይዘኝ አይቀርም.፤ ሌሊቱን ውጋት ሲያሰቃየኝ ነው ያደረው፤ እንደው ከቻሉ ቢያስወልዱኝ ብዬ ነው” አልኳቸው። ነገር ማብዛት እንደማይወዱ አውቃለውና

ሆዴን ገርመም በማድረግ “ስንት ወሩ ነው ጽንሱ?” ሲሉ ጠየቁኝ

“ኸረ ቆይቷል…….አምስት ወር ሆነው” አልኳቸው

“ቆይቷል…….(የምጸት ፈገግታ እያሳዩ) አምስት ወር ምን አላት ልጄ? ገና ልጁ መች ጠነከረና ነው የሚወለደው፤ እሱ የማይታሰብ ነገር ነው” እንዳሰቡኩት ተቆጡ

“አቶ ተስፋ …መጠንከሩ አያሳስብዎት፤ ከተወለደ በኋላ አጠነክረዋለው…..እኔ ፈጽሞ ይህንን ጽንስ ሆዴ ውስጥ ማቆየት አልችልም፤ ወይ ያስወልዱኝ ወይ ያስወርዱልኝ” አልኳቸው። ስቃዬን ፊቴ ላይ ቢያዩት ብዬ አይን አይናቸውን እያየሁኝ።

“ልጄ ማስወረድ……የኔ ጥበብ አይደለም። እኔ አቶ “ተስፋ” ጽንስን ማጨናገፍ ህሊናዬ የማይፈቅደው ነገር ነው። እንኳን እኔ ላደርገው አባቴ አቶ “መቁርጥ” ለሚያደረገው ሁሉ ይሰቀጥጠኛል። እኔ የአቶ “መቁረጥ” ልጅ “ተስፋ”፤ ያለአባት ስም……በእንጥልጥል  “ተስፋ” ተብዬ የምጠራው ለምን ይመስልሻል?….በአባቴ ስራ ስለማፍር። ማቁዋረጥ የሚለውን ሃሳብ አታስቢው……ይወለድ ያልሽውም አይሆንም፤ ጽንሱ ማደግ አለበት፤ ያለጊዜው ከተውለደ ሙሉ አይሆንም……ሙሉ ያልሆነ ልጅ ደግሞ ህይወቱ እረጅም አይደለም፤ ታዲያ ይህ ከማስወረድ በምን ተለየ፧”

“ስቃዩን እኮ አልቻልኩትም……”አልኳቸው እንባዬ ባፈጠጠው ሆዴ ላይ ጠብ ጠብ እያለ……..

“ትችይዋለሽ……ህመመሽ…..ወደፊት ከምታይው ደስታ ጋር ሲነጻጸር…ከምንም አይቆጠርም። ያሁኑን ህመም ፈርተሽ…ጽንሱን ብታስወርጂ…..እድሜሽን በሙሉ እንደ ነፍሰ ገዳይ እራስሽን፤ ህሊናሽን ስትሸሺ ትኖሪያለሽ። እርግዝና ድፍረት፤ መስዋትነት፤ ቆራጥነት፤ እራስን አሳልፎ መስጠት ይጠይቃል፤ ለዚህ ነው ብዙዎች የማያረግዙት፤ ቢያረግዙም በፍርሃት ጽንሱ ይጨናገፋል……አንቺንም የሚያምሽ  ጽንሱ ሳይሆን ፍርሃቱ ነው።…እናም ፍርሃትሽን ወይም ልጅችሽን ምረጭ” አሉኝ

“ብቻዬን ሆኜ እኮ ነው …..”አልኩኝ ሳላስበው አምልጦኝ

“አውቃለው…. እንደ ሌላው እርጉዝ  ያረገሽው ከ”ኑሮ” ነው። ኑሮሽ የራቀሽ የሚምስልሽ…..ጽንሱን እስክትገላገይ ነው። ያኔ ወዳንቺ ይመለሳል…..ልጁን ካጨናገፍሽ ግን…..መቼም አይመለስም” ብለውኝ መልስ ሳይጠብቁ ጥለውኝ ሄዱ….

ሁላችንም እርጉዝ ነን…….ከኑሮ ያረገዝን ነፍሰ ጥሮች።  አላማህን እንደጽንስ ቁጠረው…..ህመም ሲሰማህ፤ ተስፋ መቁረጥ ሲይዝህ፤ ሁሉ አልሳካም ሲልህ ያለጊዜው ለመውለድ አትሩጥ፤ ለማስወረድም አትጨክን። አላማህ ያለጊዜው ቢወለድ እንዳስብከው እርጀም እድሜ አይኖረውም…….ለሁሉም  ጊዜ አለው። ማን እናት ናት …..ልጇን ከወለደች በኋላ ጽንሷ የሚቆጫት?

ሁላችንም ውስጥ የኑሮ ጽንስ አለ፤ ልውለድ አልያም  ልውረድ የሚል ጽንስ። ነገሮች ሲከብዱን፤ ኑሮ ሲመሰቃቀልብን…..ስኬት እንደ ውልጃ ቀን ሲርቀን፤ ተስፋ መቁረጥ ጋር ሄደን አላማችንን እናጭናግፋለን……ትንሽ ብንታገስ እኮ…..በጊዜው ሙሉ ልጅ ፤ ሙሉ ስራ እንወልድ ነበር። ተፈጥሮ ትልቅ መምህር ነው። የወቅቶች መፈራረቅን እንይ፤ ክረምቱ ሲበርደን ቆይቶ፤ ደስ በሚለው ጸደይ ወራት ይተካል። እንዲያልቅ ባንፈልግም እንኳን ጸደይ ፤ በበጋ ይተካል። የሙቀቱ ጊዜ፤ እንደ ሞቀንም አንቅር፤ በጋው በመጽው ይተካል። ተመልከቱት….ክረምቱ ብርድ ሆኖ አይቀርም፤ ሙቁቱ ሙቀት ሆኖ አይቀርም። ጨለማው እና ብርሃኑም እንደዛው…..ሺህ ተጠራጣሪ ብንሆን ጨለማ  ሳይነጋ ጨለማ ሆኖ ይቀር ይሆን እንዴ? ብለህ ሳንተኛ አድረን እናውቃለን ? በፍጹም! ምክንያቱም አንጠራጠርም።

ታዲያ እኛ ለምን እራሳችንን ከተፈጥሮ እንገነጥላለን…..ችግራችን እና ደስታችን እንደ ተፈጥሮ መፈራሩቁ መች ይቀርና። ያቃተን ማመን ነው እንጂ……እምነት በማጣት…..በፍርሃት ስንት ጽንሶች ተጨናገፉ…..

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *