“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“የሴት ልጅ”

by | Jul 16, 2017 | Guest writer-እንግዳ ጸሃፍት | 0 comments

(በሚስጥረ አደራው) 
አገር ሰላም ብዬ ወደ ስራዬ ለመሄድ በጠዋቱ ጉዜዬን ጀምሬያለው። ከሰሞኑን አንድ ወዳጄ የሰጠኝን ብዙ ዘፈን ያለበት ማጫወቻ እያጫወትኩኝ ነበር። ድንገት ከዚህ ቀደም ልብ ብዬ አድምጬው የማላውቀው የተወዳጁ ዘፋኝ የአለማየው እሸቴ ዘፈን መስረቅረቅ ጀመረ። የመጀመሪያውን የዘፈኑን ስንኝ ስሰማ ግን የሆነ ስሜት ጭንቅላቴን መታኝ፤ ስንኙ እንዲህ ይላል
“ሴት ያሳደገው ልጅ ከመባል ዘወትር
ለማኝ ሆኖ አባቴ ባይጠቅመኝም ይኑር”

ለእኔ የተሰማኝ እንደ ሙዚቃ ሳይሆን እንደ ስድብ ነበር። “የሴት ልጅ” መባል እንደ ስድብ ተቆጥሮ በምንኖርበት ማህበረሰብ፤ ለአባባሉ ሙዚቃ ሲደረስለት፤ ህዝባዊ ስምምነት ላይ የተደረሰ አያስመስለውም? ይቀጥልና
“ስድ አደግ ባለጌ ቁንጥጫ ያላየው
የሚባለው ስድብ አባት ከሞተ ነው
ሌባ ወሮበላ ቀማኛ ዱርዬ
ስራ ፈት ወስላታ ዟሪ ነህ ተብዬ
ቁጥጥር ግልምጫ ፍጹም ያልጎበኘው
የሚባለው ስድብ አባት ከሞተ ነው”-ይላል

ሙዚቃ እጅግ በጣም ትልቅ ኃይል ያለው ጥበብ ነው። የግሪኩ ፈላስፋ ፕሌቶ ” ሙዚቃ የህሊና ህግ ነው፤ ለአለም ነፍስን ይሰጣል፤ ለአይምሮ ክንፍን ይቸራል፤ ለአይን ወደማይታየው ደስታ ወዳለበት ስፍራ ያከንፋል” ሲል ተናግሯል። ይህ ማለት እንግዲህ በሙዚቃ ውስጥ የሰው ልጅ፤ በህሊናው ከሚታሰበው በላይ መርቀቅ እንደሚችል ሲያስረዳ ነው። በተለያዩ ጊዜያት ሰዎች ሙዚቃን ለተለያዩ ነገሮች ተጠቅመውበታል፤ ሰው በሙዚቃ ተፋቅሯል፤ በሙዚቃ ነጻ ወጥቷል፤ በሙዚቃ ተደስቷል፤ በሙዚቃ አዝኖዋል፤ በሙዚቃ የወደፊቱን አስቧል፤ በሙዚቃ ያለፈውን እያሰበ ትናንትን በድጋሜ ኖሯል። ሙዚቃ ትልቅ ሃይል ያለው መሳሪያ ነው። የነጻነቱ ተፋላሚ ማሪቲን ሉተር ኪንግ “ከፋጣሪ ቃል በታች፤ አለም ያላት ትልቁ ሃብቷ እውነተኛው የሙዚቃ ጥበብ ነው” ብሏል። “Next to the word of God, the noble art of music is the greatest treasure in the world”- Martin Luther

ይህንን ያነሳሁበት ምክንያት፤ በሙዚቃ የምናስተላልፋቸው መልዕክቶች ምን ያህል አይምሮ ላይ ሊታተሙ እንደሚችሉ ለማስመር ነው። እንደውም ጥንታውያን ገጣሚያን (በእርግጠኝነት የፕርሺያ ገጣሚያን)፤ ህዝብ ሰብስበው ግጥም በሚያነብቡት ወቅት ሙዚቃ ያጅባቸው ነበር። ምክንያታቸውም የሙዚቃው ጉልበት፤ የሚነበበውን ግጥም በሰው ህሊና ውስጥ ይበልጥ ያሰርጸዋል፤ እንዳይረሳም ያደርገዋል ብለው ስለሚያምኑ ነው።

መነሻ ወደ ሆነኝ የአለማየው እሸቴ ዘፈን ልመልሳችሁ። “ሴት ያሳደገው ልጅ ከመባል ዘወትር” ሲል፤ ልጅ በእናት ብቻ ማደጉ እንደውርደት የሚቆጠርበት ማህበረሰብ እንዳለን የሚያመላክት ነው። ማንኛውም ልጅ የአባትና የእናትን ፍቅር አግኝቶ ማደግ እንዳለበት ይታመናል። ነገር ግን በአንድ ወላጅ ማደግ ክብር፤ በሌላ ወላጅ ማደግ ውርደት ሲሆን ግን የማህበረሰብ አድሎ ይመስለኛል። እርግጥ ነው እየተለወጠ የመጣ ነገር ነው። ቢሆንም ቅሉ “የሴት ልጅ”‘፤ “ሴታሴት” የመሳሰሉትን ስድቦች እስከአሁን የምንሰማቸው ናቸው። ኸረ እንደውም ከሳምንታት በፊት አንድ ሬድዮ ላይ፤ “ሴታሴት” ወንድ አንወድም የሚሉ ሴቶችን አድምጫለው። ጋዜጠኛው “ሴታሴትነትን” እንዲያስረዱ ሲጠይቃቸው፤ “ወሬ ማመላለስ” ብለው መልሰውለታል። ይህንን ቃል ብዙዎቻችን ሳናውቀው፤ በዘልማድ ተጠቅመንበታል፤ ግን እንዲህ ቀላል የሚመስሉ አባባሎች ናቸው፤ ተለምደው ተለምደው ኋላ ላይ ባህል፤ እምነት፤ ህግ፤ እውነታ ሆነው የሚቀሩት።ለምሳሌ ፈሪን ለመግለጽ “ሴት” ማለቱ፤ ወረኛነትን ለመግለጽ “ሴታሴት” ማለቱ፤ ጥቅመኛነትን ለማሳየት “ሴትና ገንዘብን” ማቆራኘቱ፤ በዘልማድ ውስጥ የሚስተዋሉ ትልቅ ጥፋቶች ናቸው።

ሴትነት ስድብ ሊሆን አይችልም። ስድብ እንዲሆን ግን ሴቶችም፤ ወንዶችም ይሁንታን ስንሰጠው ኖረናል። “ሴት ያሳደገው ልጅ ከመባል ዘወትር፤ ለማኝ ሆኖ አባቴ ባይጠቅመኝም ይኑር” ማለት እኮ፤ የማይጠቅም አባትነት፤ ከእውነተኛ እናትነት ምንም ግዜም ይሻላል ማለቱ ነው። ሙዚቃውን ደጋግሜ እየሰማው ፤ ብዙ የማውቃቸው ነጠላ እናቶች ታወሱኝ። ህጽን ሆኔ ሰፈራችን ውስጥ ብዙ ልጆችን ለብቻቸው ያሳድጉ የነበሩ እናትን አውቅ ነበር። እንደአንድ እናት ሳይሆን እንደ እናትም አባትም ሆነው ከአስር በላይ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ፤ ልጆቻቸው ብቻም ሳይሆን ሰፈሩ ሁሉ የሚፈራቸው እናት ነበሩ። የሚታወቁት በስርዓት አስከባሪነታቸውና በቁጣቸው ነበር። ታዲያ ይህ አይነቱ ሙዚቃ ለእንደዚህ አይነት እናት ህመም አይደለም?

ጽሁፉ ቢበቃኝና፤ ብተርክ በቅርብ የማውቃቸው፤ ያለ አባት ለልጆቻቸው አንድም ነገር ሳያጎድሉ በነጠላነት ልጆቻቸውን የሚያሳድጉ እናቶችን መጥቀስ እችል ነበር። “የሴት ልጅ” በፍጹም ስድብ አይደለም። ልጅ በሴት ብቻ ስላደገ፤ በዘፈኑ ላይ እንዳልው “ዘራፊ፤ ቀማኛ፤ ስራፈትና ወስላታ” አይሆንም። በጥበብ ሽፋን የሚቀርቡ መልዕክቶች ጉልበት አላቸው፤ የሬጌው አቀንቃኝ ቦብ ማርሌ፤ ብዙ ጥቁሮችን ስለ ነጻነትቻው በጥልቅ እንዲያስቡ አድርጎዋቸው ነበር።በንግግርና በስብሰባ ወይም በመጽሐፍ ሳይሆን በሙዚቃ ብቻ። ለዚህ ነው ሙዚቃው የረበሸኝ፤ ምናልባት ሴትነቴም አስቆጥቶኝ ይሆናል። ከምንም በላይ ግን በቅርብ የማውቃቸውን ነጠላ እናቶችን (ለብቻቸው ልጆችን የማሳደግ ሃላፊነት የተጣለባቸው እናቶች) ስላሰብኩኝ ነው። ሴትነት ስድብ መሆኑ እስካልቀረ ድረስ፤ ለሴት ልጅ ክበር መስጠት ከባድ ነው። ከምንም በላይ ግን በሙዚቃዎቻችን፤ በፊልሞቻችን፤ በግጥሞቻችንና በመጽሐፎቻችን ውስጥ ሴትን እንዴት ነው የምንስላት? የሚለው ጥያቄ መሰረታዊው ጥያቄ ይመስለኛል። ምክንያቱም ጥበብ አለምን ሁሉ የማስማማት ሃይል አላት። ሴቶች በጥበብ ውስጥ ያላቸው መልክና ስፍራ፤ የማህበረሰቡ እውነታና ስምምነት የመሆን እድሉ ሰፊ ስለሆነ።
ለማንኛውም ድምጽ ቢኖረኝና መዝፈን ብችል ፤ ለአለማየው እሸቴ የሚሆነው ዘፈኔ እንዲህ ይጀመር ነበር።
“ሴት ያሳደጋት ልጅ ልባል ስም ይውጣልኝ
የስም አባትነት ምንም ላይሰራልኝ
በሴት እጅ ማደጉ አያጎድልም ክብር
የሴት ልጅ በሉና ከፍ አርጉኝ ዘወትር”

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *