“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

የአንዲት ወፍን እምነት ለማግኘት

by | Oct 21, 2019 | Guest writer-እንግዳ ጸሃፍት | 2 comments

በሚስጥረ አደራው

ዛፍ መሆን እመኛለሁ ያለውን ባለቅኔ ዛሬ ነበር ማግኝት

“መጽሀፍ አንብቤ እፎይ ባልኩኝ ሰዓት

ምነው ዛፍ በሆንኩኝ፤እያልኩ እመኛለሁ

ወይ ፍሬ አፈራለሁ

ወይ ጥላ እሆናለሁ

ቢያንስ አንዲት ወፍ በግል

አምና ጎጆ ቤቷን፤ እንደምትሰጠኝ እተማመናለሁ

ያኔ በትክክል ለአደራ እበቃለሁ”- ነብይ መኮንን/ስውር ስፌት

ሰሞኑን በምኖርበት ከተማ ዛፎች ቅጠላቸውን የሚያጡበት ወቅት ነው። ላለፉት ወራቶች አረንጓዴ ለብሰው በኩራት ቆመው የነበሩት ዛፎች በነዚህ ወራቶች ቅጠላቸው ጠውልጎ ቀስ እያለ ከላያቸው ላይ ይረግፋል። በርግጥ ለተመልካች ይህ የሚረግፈው ቅጥል እራሱ ውብ መልክ አለው። ግን ደግሞ አረንጓዴ ለብሶ ያየነው ዛፍ እራቁቱን ቅርንጭፉን አንጭብርሮ ቆሞ ሲታይ ያሳዝናል። ተመልሶ ቅጠል የማያበቅል ይመስል ይራቆታል። እውነት ለመናገር እስከዛሬ ዛፎች በዚህ ወራት ለምን ቅጠሎቻቸው ይረግፋል ብዬ አጥብቄ ጠይቄ አላውቅም ነበር፤ሆኖም ዛሬ በዚህ ላይ የተጻፉ ጽሁፎችን ሳይ ዛፎች ቅጠላቸውን የሚያረግፉት መጭውን ቀዝቃዛ ወራቶች በህይወት ለማለፍ ሲሉ ነው።

እንደነዚህ አይነት ዛፎች አሁን ቅጠላቸውን ካረገፉ በቂ ውሃና በቂ ጉልበት ሰብስበው መጪውን እጅግ ቀዝቃዛ የሆነ ክረምት በጽናት ማለፍ ይችላሉ። ቅጠላቸው ስለረገፈ አይሞቱም፤ ቅርንጫፋቸውን ሰብረው አንገታቸውን አይደፉም። የወቅቱን መፈራረቅ ፤ በመፈረረቅ ውስጥም ያለውን የመጠለውግና የመለምለምን አይታለፌነት ያለምንም ማስተባበል ለሚመለከተው ሁሉ ያስተዋውቁታል። እኒህ ዛፎች በጋ መጥቶ ቅጥላቸው ሲለመልምም ሆነ፤ ክረምት መጥቶ ቅጠላቸው ሲረግፍ፤ በተመሳሳይ ጽናት ስራቸው ሳይላላ ሁለቱንም ወቅቶች ቀጥ ብለው በጽናት ይሳልፋሉ። ይህንን ሳይ ነበር እንደ ዛፍ መሆንን የተመኝሁት። ከዚህ የመፈራረቅ ስርዓት ማንም የአለም ፍጡር አያመልጥምና። ይህንን መፈራረቅ በጥበብ በማለፉ ረገድ ግን ሰው ያልሆኑት ፍጥረቶች ሳይሻሉ አይቀርም።

ማጣትን እንደዛፍ በጽናት ማለፍ ለሰው ይከብዳል። ሁሌም አረንጓዴ ለብሰን መኖር መብታችን ስለሚመስለን ክረምት መጥቶ ቅጥላችን መቅላት ሲምጀር አንገታችንን እንደፋለን። የሚያልፍ አይመስለንም። አሁን እየሆነው ያለው ነገር ሁሉ መጭውን ወቅት እንድናልፈው እያዘጋጀን መሆኑን መረዳት ይከብደናል። ሁሉም ነገር በቅጽበት እየሆነ በምናይበት አለም ውስጥ፤ትዕግስት ፈታኝ ባህሪ ነው። እንደዛፍ ቅጠል ከላያችን ላይ በቅለው ግርማ የሚሰጡን ብዙ አይነት ሰወኛ ቅጠሎች አሉ። ምናልባት ዛሬ ላይ አረንጓዴ ሆነው ይታዩ ይሆናል። ቁመናችንን አሳምረው፤ በሰው ፊትም አግዝፈውን ይሆናል። የአረንጓዴነትን ውበት ማንም አያጣውም። ነገር ግን ወቅት ሲቀየርስ? የነበረንን ስናጣስ?ያሳመረን ነገር ሲረግፍ፤ እራቁት የመሆን ጊዜ ሲመጣ፤ እንደ ዛፍ ግንድ የማይደነግጥና ሳይውድቅ ቀዝቃዛውን ወራት የሚያሳልፈን ማንነት አለን? ይህ ይመስለኛል እራሳችንን ልንጠይቅ የሚገባን ወሳኝ ጥያቄ።

አንድ ከስራችንን ጋር የሚያስተሳስረን፤በደስታ ብዛት የማይነቀል፤ በሀዘን ጊዜ የማይልፈሰፈስ፤በማግኝትም ሆነ በማጣት ወራቶች ቀጥ ብለን እንድንቆም የሚያስችለን ግንድ ሊኖረን ይገባል። የኑሮ ቅርንጫፎችን ተሸኽሞ መቆም የሚችል ግንድ። በዚህ የማንንነት ግንድ ላይ ነው፤ ቅርንጭፎች ተፈጥረው የረገፉት ቅጥሎች መልሰው የሚያቆጠቁጡት። በክረምት የሚራቆተው ዛፍ የራሱ የሆነ ውበት እንዳለው ሁሉ፤ በፈተና ወቅት የሚኖረን ማንነትም የራሱ ሆነ ውበት አለው። ይህ ውበታችን የሚወጣው ግን፤ ያለንበትን ወቅት አምነን መቀበል ስንችል ብቻ ነው። እላያችን ላይ ያሉት ቅጠሎች በረገፉ ቁጥር የሚደነግጥ ማንነት ሲኖረን ግን፤ የመለምለሚያው ወቅት ሳይደርስ ግንዱ እራሱ ይወድቃል። በወደቀ ግንድ ላይ ደግሞ ምሳር እንጂ ህይወትን የሚያስቀጥሉ ቅጠሎች አይበቅሉም።

ታዲያ ለምንድን ነው የነብዩ መኮንን ግጥም ሽው ያለኝ? እራስ ወዳድነቴን በትንሹ ስላሳየኝ። ባለቅኔው ዛፍ መሆንን ሲመኝ፤ ከራሱ አልፎ ለሌሎች ጥላ ለመሆን ነበር። ቢያንስ የአንዲትን ወፍ እምነት ሲጠይቅ፤የገዘፈ ሰብዓዊነቱን ያሳያል፤እኔ ዛሬ ላይ ሆኜ ዛፍነትን ስመኝ በፍጹም እራስ ወዳድነት ነው። እሱ ለሌሎች ማረፊያነት ህሊናውን ሲያሰናዳ፤ የእኔ ህሊና እስካውን እራሴን ለማዳን ነው የሚሮጥው። ይፈረድብኛል? ለሌሎች ጎጆ  መስሪያ ከመሆን በፊት ጸንቶ መቆም ይቀድማል! ጽኑ ዛፍ ብቻ ነው የወፊቱን እምነት ማግኘት የሚችለው::

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

2 Comments

  1. Shukran Maliso

    Long live Mistre i have no any other word to say than the best wishing i have for you. Nice stay!!!

    Reply
  2. TSEGAY

    Amazing

    Reply

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *