“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

ዘለቄታዊ ለውጥን እንዴት ማምጣት እንችላለን?

by | Jun 9, 2015 | መነቃቂያ inspiring stories | 0 comments

ብዙ ጊዜ በህይወታችን ለውጥ ለማምጣት እንፋልግና መንገዱ ቀላል አይሆንልንም። ዛሬ የሚያነቃቃ ነገር ሰምተን እንደሆነ ወዲያው በስሜታዊነት ለለውጥ እንነሳሳለን፤ ጥቂት ቆይተን  የሰማነውን ስንረሳ ደግሞ መልሰን ወደነበርንበት ስሜት እንወርዳለን። ይህ የብዙ ሰዎች ችግር ነው። የስሜት መዋዠቅ፤ በራስ መተማመናችን ከማሳነሱ ባሻገር ከራሳችን ጋር ያለን ግኑኝነት ላይም ተጽዕኖ አለው። ለውጥ ለሁላችንም እንደየግላችን የራሱ የሆነ ትርጉም አለው። ሁላችንንም የሚያጋራን ትርጉሙ ግን፤ ለመለወጥ ስናስብ፤ አሁን ደስተኛ እንዳንሆን የሚያደርጉንን ባህሪዎች እና አስተሳሰቦች፤ ገንቢ በሆኑ ባህሪዎች እና አስተሳሰቦች መተካት ነው።

ታዲያ ዘለቄታዊ በሆነ መንገድ እንዴት በህይወታች የምንፈልገውን ለውጥ እናምጣ? የሚከተሉት ነጥቦች ሁላችንም ማስተካከል ለምንፈልገው የህይወታችን ክፍል ዘለቄታዊ ለውጥ ለማጣት ይረዱናልና እነሆ….

  •  በመጀመሪያ ለራሳችን ግልጽ እንሁን- እራስህ ላይ ሃይለኛ አትሁን። በሰራኸው ስራ ወይም በያዝከው መጥፎ አመል እራስህን በጸጸት አትግደል። ይልቁንም  አሁን ያለህ ባህሪ የምትፈልገውን ኑሮ ከማግኘት እንዳገደህና ልታስወግደው እንደምትፈልግ፤ ለራስህ ንገረው። መንገር ብቻም ሳይሆን አሳምነው።
  • ምን ሳይሆን ማንን መሆን እንደምትፈልግ ወስን- ምን ለመሆን አታስብ ማለት፤ ሰዎች ብዙ ነገርን ለመሆን ያስቡ ይሆናል ለምሳሌ ዶክተር፤ ቄስ፤ አስተማሪ እና የመሳሰሉትን፤ ግን የሚያፈሩት ፍሬ የሚጠበቅባቸውን ላይሆን ይችላል። ማንን መሆን እንደምትፈልግ ስታስብ ግን፤ ማንነትህን በያዝከው ስኬት ሳይሆን በምታበረክተው አስተዋጽዎ እየለካህ ነው ማለት ነው። አስተማሪ መሆንን እመኛለው ከማለት፤ ተምሬ ብዙዎችን የምለውጥ ሰው መሆን እመኛለው እንደማለት ነው።
  • አካባቢህን ቃኝ- ሰውን መናቅ ወይም እኔ ከሰው እበልጣለው ማለት ተገቢ አይደለም። ሁሉንም ሰው ውደድ አክብር ፤ ግን ከማን ጋር ጊዜህ እንደምታሳልፍ በጥንቃቄ ወስን። መሆን የምትፈልገውን ሰው የሚመስሉ ሰዎችን ፈልገህ ተቀላቀል። አንዳንዴ አናስተውለውም እንጂ ፤ እንዳንለወጥ አስረው የሚያስቀሩን የምንቀርባቸው ሰዎች ናቸው። እንዳንለወጥ ፈልገው ወይም በክፋት ተነሳስተው ሳይሆን ከለመዱት ወንበር መነሳት ስለሚከብዳቸው እኛንም በቆምን ቁጥር ቁጭ ያደርጉናል። እናም አካባቢህን ቃኝ፤ ካንተ ከተሻለ ሰው ጋር ለመቀላቀል ሞክር።
  • አይምሮህን በቀን በቀን ፈትሽ- አንድ ግዜ ዚግ ዚግለር የተባለው ዝነኛ ተናጋሪና ጸሃፊን (Motivational Speaker) አንድ ሰው እንዲህ ሲል ጠየቀው “የሚያነቃቁ ታሪኮችን ወይም ጽሁፎችን ሳነብ ወዲያው ስሜቴ ከፍ ይልና ሁሉን ነገር ለማድረግ እነሳሳለው፤ ነገር ግን ያ ብዙ አይቆይም መልሼ ወደ ድብርት ስሜቴ እመለሳለው። ለምን የሚያነቃቁ ጽሁፎች ወይም ንግግሮች ዘለቄታዊ ለውጥ አያመጡም?” አለው ዚግ ዝጊለርም መልሶ እንዲህ መለሰለት “ገላህን አንዴ ታጥበህ እስከመቼ ትቆያለህ? ገላህ በቆሸሸ ቁጥር መታጠብህ አይቀርም፤ አይምሮህም እንደዛው ነው፤ በአሉታዊ አስተሳሰቦች በቆሸሸ ቁጥር፤ በመልካም አስትሳስቦች እና በሚያነቃቁ ነገሮች ማጠብ አለብህ” አለው። ስለዚህ ትላንት ለለውጥ እራስህን አዘጋጅተህ፤ ዛሬ የማትችል ቢመስልህ አትደናገጥ፤ አይምሮህን በመልካም ነገሮች ከማነቃቃት አትቦዝን። ዘወትር ለራስህ ገንቢ ንግግሮችን ንግረው። ህይወትህ ላይ እጅግ ትልቅ ተጽዕኖ ያለው የአይምሮህ ክፍል subconscious mind, የሚያምነው ተደጋግሞ የሚነግረውን ነውና መልካሙን ነገር ደጋመህ ንገረው።
  • በመጨረሻ እርሻህን ማረም አትርሳ-አይምሮህ ማንም የፈለገውን ነገር የሚዘራበት ግልጥ እርሻ ነው። መልካም ዘር የሚበቅልበት እርሻ የማድረግ ሃላፊነቱ ያንተ ነው። አሉታዊ አስተሳሰቦች፤ እርሻህን የሚበድሉ አረሞች ናቸውና አዘውትረህ ማረም አለብህ። የአይምሮ አረም ከተለያየ ቦታ ይዘራል፤ ስር እንዳይሰዱ  የማድረግ ትልቅ ሃይል ግን አለህ።

እርሻውን የሚንከባከብ ፤ አረሙን አዘውትሮ የሚነቅል መልካም ገበሬ ሁን፤ ለነፈስህም ለስጋህም በቂ ዘር ለማግኘት ይረዳሃልና።

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *