“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

ከምድር ሁሉ ሃብታሙ ስፍራ……..መቃብር!

by | Apr 19, 2016 | መነቃቂያ inspiring stories | 0 comments

 

“The graveyard is the richest place on earth, because it is here that you will find all the hopes and dreams that were never fulfilled, the books that were never written, the songs that were never sung, the inventions that were never shared, the cures that were never discovered, all because someone was too afraid to take that first step, keep with the problem, or determined to carry our their dream.”― Les Brown

ለምን እንደሆነ ባላውቅም ብዙዎቻችን ስለሞት ማሰቡን አንወድም። ለነገሩ ሞት ምን ደስ የሚል ነገር አለውና። ለማለት የፈልግኩት ግን ስለ ሞት ማሰቡም ሆነ ማውራቱን ከመጥላታችን በላይ አኗኗርችን ሲቃኝ ሞትን ፈጽሞ የዘነጋነው ይመስላል። ጎረቤታችንን እየወሰደ እያየን እንኳን እኛን ደፍሮ የሚነካን አይመስለንም። ለዚህ ነው አለቅጥ የምንዘናጋው።  መጽሃፍ ቅዱስ ላይ ሳይዘጋጁ ተዘናግተው መኖር የሚያመጣውን ጣጣ የሚያስረዳ ድንቅ ታሪክ አለ።

“በዚያን ጊዜ መንግስተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አስር ቆነጃጅትን ትመስላለች፤ ከእነርሱም አምስቱ  ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ። ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከነሱ ጋር ዘይት አልያዙምና ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ። ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ። እኩለ ሌሊትም ሲሆን እነሆ ሙሽራው ይመጣል ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ሁካታ ሆነ። በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሱና መብራታቸውን አዘጋጁ። ሰነፎቹም ልባሞቹን መብራታችን ሊጠፋብን ነው ከዘይታቹህ  ስጡን አሏቸው። ልባሞቹ ግን መልሰው ምናልባት ለእኛ እና ለእናንተ ባይበቃስ ይልቅስ መደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሏቸው። ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ ደጁም ተዘጋ። በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቆነጃጅት መጡና “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ ክፈትልን አሉ”፤ እርሱ ግን መልሶ “እውነት እላችኋለው አላውቃችሁም” አለ። ቀኒቱን እና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ አላቸው።

ነገ ለሁላችንም የቅርብ እሩቅ ነው፤ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል። የብዙዎቻችን አኗኗር ልክ እንደ አምስቱ ሰነፍ ቆነጃጅት ነው። ለብዙ ነገሮች ቀጠሮን መያዝ እንወዳለን። ሞትን እንደጥላችን ይዘነው እንደምንዞር ስለምንዘነጋ እርምጃችን ዘገምተኛ ነው። ለሁሉ ነገር ነገን እንመርጣለን፤ ነገ ሲመጣ ደግሞ ሌላ ነገ ይወለዳል። ከላይ የሰፈረው የሌስ ብራውን አባባል ትልቅ እውነት ነው። መቃብር በምድር ብዙ ሃብት ያለበት ስፍራ ነው። ምክንያቱም ጥቂቶች ብቻ ናቸው የተሰጣቸውን ተሰጥዎ ተጠቅመውበት የሚያልፉት። ብዙዎቻችን ግን አይምሮዋችንን ሳንጠቀምበት፤ ሰውነታችን ሳንሰራበት፤ እውቀታችንን ሳንገለገልበት ጀምበራችን ትጠልቃለች።

ተዘጋጅቶ መኖር በመንፈሳዊውም ሆነ በስጋዊው ህይወታችን ወሳኝ ነገር ነው። ብዙ እውነቶች ሳይነገሩ፤ ብዙ ይቅርታዎች ሳይጠየቁ፤ ብዙ ካሳዎች ሳይከፈሉ፤ ወደመቃብር ወርደዋል። ለዚህ ነው ሌስ ብራውን መቃብርን ሃብት የተሞላበት ስፍራ ሲል የገለጸው። ልክ እንደ ሰነፎቹ ቆነጃጅት የቅንነትን ዘይት፤ የእውነትን ዘይት፤ የይቅርታን ዘይት፤ የተስፋን ዘይት በእለት ተእለት ኑሮዋችን ይዘን ስለማንዞር፤ ድንገት ሙሽራው ሲመጣ ፤ ጨለማ ይወጠናል፤ ደጁ በላያችን ይዘጋል።

አያድረገው እንጂ  ነገ ትሞታላችሁ ቢባል ፤ለነገ የሳደርናቸው ስንት ሃሳቦች አብረውን ይሞታሉ?ለነገ ያቆየናቸው ስንት ግቦች አብረውን መቃበር ይወርዳሉ?ሳንፈትሽ ያቆየናቸው ስንት ተሰጥዖዎች ቁልቁል ይቀበራሉ? ሳይፈንጥቁ የኖሩት ስንት ተስፋዎች ይቀጫሉ?ያላበረከትናቸው ስንት ደግነቶች አፈር ይበላቸዋል? ያልተነገሩ ስንት ይቅርታዎች ላይመለሱ ይሞታሉ? ያለተተነፈሱ ፍቅሮች ሳያብቡ ይሞታሉ?

ሞትን እንደማሰብ ብርታትን የሚሰጥ እና ቀናውን መንገድ የሚመራ ሃይል ያለ አይመስለኝም። መጨራሻን ሞት መሆኑን ስናውቅ ይህችንን አለም መልካም ከማድረግ በቀር ምንም  ምርጫ ሊኖረን ባልተገባ ነበር። ነጋችን ዋስትና እንደሌለው  ስንረዳ ሰውን ሰው ሊያሰኘው የሚችሉትን ምግባሮች ለማድረግ ቀጠሮ ባልያዘን ነበር። እናም አላማህን ፈጽሞ አታዘግየው ማን እንደሚቀድምህ አታውቅምና። ህይወታችንን ሙሉ ከስርዓት ውጪ ኖረን፤ ለንስሃ ጊዜ እናገኛለን ብለን አንዘናጋ። ዘይታችንን ሙሉ አድረገን እንጓዝ በሩ መቼ እንደሚዘጋብን  አናውቅምና።

 

 

 

 

 

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *