“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

ከመስመሩ በላይና በታች

by | Dec 16, 2015 | መነቃቂያ inspiring stories | 1 comment

 

በኑሮ ላይ የተሰመረ ሃሳባዊ መስመር አለ። ጥቂቶች ከመስመሩ በላይ ሲኖሩ ብዙሃኑ ግን ከመስመሩ በታችን ይኖራሉ። ይህ መስመር የአስተሳሰብ መስመር ነው። ከመስመሩ በታች ለመኖር እጅግ ቀላል ነው፤ ቀላል የሆነው ምቹ ሆኖ ሳይሆን ጥረት እና ልፋት ስለማይኖርበት ነው። እራስን ለማሻሻልም ሆነ እራስን ለማነጽ ምንም አይነት ሙከራ የማይደረግበት፤ የጨለምተኝነት ጭጋግ የወረሰው ስፍራ ነው። ከመስመሩ በታች የሚኖሩ ሰዎች ትናንታቸው ከዛሬ ዛሬያቸው ከነገ ለውጥ የለውም። የሰው ልጅ ዛሬም እንደትናንት ካሰበ እንዴት የተለየ ዛሬ ሊኖረው ይችላል?

ብዙ ጊዜ በህይወታችን ለውጥ ለማምጣት እንፈልግና ጥረታችን ሁሉ ከንቱ ሲሆንብን ኑሮ ልክ እንደ ክብ መንገድ ዞሮ ዞሮ የሚያመመጣን የቆምንበት ቦታ ይመስለናል። ነገር ግን ለውጥ ማምጣት የሚሳነን፤ እራስን መለወጥ ስለማይቻል ሳይሆን፤ አስተሳሰባችን ዛሬም እንደትናንት ስለሆነ ነው። ከመስመሩ በታች የሚኖሩ ሰዎች አስተሳሰባቸውን ለመቀየር ፤በህይወት ላይ ያላቸውን አመለካከት ለመለወጥ ጥረት አያደርጉም ምክንያቱም ቀላል አይደለምና። አሉታዊ አስተሳሰቦችን ማሰብ በጣም ቀላል ነው፤ በኑሮዋችን ላይ የሚያመጡትን ተጽዕኖ ተቋቁሞ መኖሩ ግን በፍጹም ግን ቀላል አይደለም።

ከመሰመሩ በላይ የሚኖር ሰው አስተሳሰቡ የእጣ ፋንታ ጉዳይ ሳይሆን የምርጫ ጉዳይ እንደሆነ የሚያምን ሰው ነው ። ከመስመሩ በላይ መኖር ቀላል አይደለም ነገር ግን ህይወት የምትጋርጥብንን  ፈተና ለማለፍ ግን መነገዱን ቀላል ያደርገዋል። አወንታዊ አስተሳሰብን በእለት ተለት ኑሮ ላይ ለመተግበር ቀላል አይደለም። ምክንያቱም ብዙ ከኛ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ነገሮች ስላሉ። ብዙ ሰዎች አንድ መጽሃፍ አንብበው እስከዛሬ የገነቡትን የህይወት ልምድ ለመቀየር ይጥራሉ። ምንም እንኳን ለጠቢብ አንድ ቃል በቂው ነው ቢባልም፤ ባህሪን እና ልምድን በቀላሉ አሽቀንጥሮ መጣል ግን ለብዙዎቻችን ይከብዳል። ለዚህ ነው ብዙ ሰዎች የለውጥን ጎዳና ይጀምሩና ለውጡን በአንድ ጀንበር ሲያጡት ተስፋ ቆርጠው ተደብቀው ወደነበሩበት ጉድጓድ መልሰው የሚገቡት።

እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን አንድ ወሳኝ ነገር አለ። አንድ ሰው አንዴ 100 ኩንታል ስለተሸከመ በአንድ ቀን ጡንቻ አያወጣም። ጡንቻ ለማውጣት አልያም ደህና የሰውነት አቋምን ለማይዝ ያ ሰው ለብዙ ጊዜ ያለማቋረጥ እንቅስቃሴ ማድረግና እራሱን ያለመታከት መጠበቅ ይኖርበታል። አይምሮም ከዚህ አይለይም፤ ጤነኛ አይምሮን ለመያዝ የዘወትር ክትትል ያስፈልጋል። አይምሮዋችን እያወቅንም ሆነ ሳናውቅ በምናከማቻቸው መረጃዎች የሚመራ ነው። በተለይ ሳናውቅ (subconsciously) እንደዘበት የምናጠራቅማቸው መረጃዎች፤ ልምድ ይሆኑብና አሁን ያለንን  ማንነት እንዴት እንደያዝነው ሳናውቅ በደመነፍስ እንኖራለን።

ደስ የሚለው እውነታ ግን በማንኛውም የህይወት መስመር ላይ ብንሆንም ወደምንፈልገው መንገድ ለመሄድ እድሉ አለን። የሁሉም ነገር ቁልፉ ግን አስተሳሰባችን ነው። አስቡት ማንኛቸውም  ነገሮች አለማችን ላይ እውን ሆነው ከመከሰታቸው በፊት በቅድሚያ አይምሮ ውስጥ መጸነስ አለባቸው። ይህም አሁን እውን ሆኖ የምናየው  እያንዳንዱ ነገር በመጀመሪያ ሃሳብ ነበር ወደሚለው መደምደሚያ ያደርሰናል። ስለዚህ አስተሳሰብ የምንም ነገር ፈጣሪ ነው ማለት ነው። ታዲያ ይህንን ትልቅ ሃይል ለመልካም ፈጠራ ብንጠቀምበትስ? ያኔ ከመስመሩ በላይ መኖር እንጀምራለን። ከመስመሩ በላይ ነጻነት፤ ደስታ እና ፍቅር እንዲሁም ተስፋ በበቂ ይኖራሉ። በቅጡ የማይመራ አስተሳሰብ ግን፤ ከመስመሩ በታች ያለነጻነት ያለተስፋ በእጣ ፋንታ ገመድ አስሮ ያኖረናል።

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

1 Comment

  1. Kasahun

    ተባረኩ ስለትምህርታችሁ አመሰግናለው

    Reply

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *