“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

እውነተኛ ወዳጆቻችንን  እንዴት እንለያቸው?

by | Apr 21, 2016 | Guest writer-እንግዳ ጸሃፍት | 0 comments

 

“እንክት ይበል ድቅቅ ጎኔን አይመቸው (2)

መቼም  ያለወዳጅ አይደላም ያለሰው” አለ ዘፋኙ

ሰው ያለ ሰው መኖር የሚችል አይመስለኝም። ያለወዳጅ በብቸኝነት የምትገፋ ህይወት እምብዛም ጣፋጭ አትሆንም። ነገር ግን ማንኛውም አይነት ግንኙነት የእውነት ጣዕም የሚኖረው እውነተኛ ወዳጅ ስናገኝ ነው። ሰው ለሰው ልጅ መጥፊያውም መልሚያውም ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ሰዎች  ለህይወታችን መሳካት አስተዋጽዎ ሲያደርጉ ሌሎች ደግሞ የመውደቂያ ጉድጓዳችንን ይቆፍራሉ። ታዲያ እንዴት እንለያቸው? የሚከተሉት ነጥቦች እውነተኛ ወዳጆቻችንን ነጥለን እንድናውቅ የሚረዱን ነጥቦች ናቸው

እውነተኛ ወዳጅህ ማንነትህን አምኖ ለመቀበል አይከብደውም- ወዳጅ ስል ጓደኛንም ሆነ የፍቅር አጋርን አልያም ቤተሰብን ቢያጠቃልል ደስ ይለኛል። አለ አይደል የሚወዱን ሰዎች ለማለት ያህል። የሚወዱን ሰዎች ማንነታችንን ለመቀበል ችግር የለባቸውም። ልክ ለሸክላ ስራ እንደተቦካ ጭቃ እያገላበጡ ሊቀርጹን አይሞክሩም። ስለሚወዱን በራሳችን ቆዳ ውስጥ ተስማምተን እንድንኖር ይፈቅዱልናል። የእውነት የሚወዱን ሰዎች የሚፈልጉን የጎደላቸውን እንድንሞላላቸው አይደለም። ስለዚህ እኛን የሚያስደስቱን ነገሮች ለነሱ ህይወት ስላልተሰማ ብቻ እንድንለውጠው አያስገድዱንም። የኛን ወዳጅነት ለጥቅማቸው ብቻ የሚጠቀሙ ሰዎች ግን እነሱን በሚስማማቸው መንገድ እንጂ እኛ በመረጥነው ጎዳና ስንሄድ ደስ አይላቸው።

-እውነተኛ ወዳጅህ ለመለወጥ ስታስብ እንቅፋት አይሆንብህም- ከለውጥ እንቅፋቶች መሃከል ቅድሚያ የሚጠቀሱት በቅርብ የምናውቃቸው ሰዎች ናቸው። ሰዎች ከለመዱን ባህሪ ስንለወጥ አይዋጥላቸውም። ብዙ ሰዎች ከተለመዱበት ማህበረሰብ ላለመለየት ሲሉ እራሳቸውን ከመለወጥ ይቆጠባሉ። ስንት ሰዎች ናቸው ለጓደኞቻቸው ሲሉ በሱስ ውስጥ ተዘፍቀው ያሉት? ጓደኝነታቸውን ላለማጣት ሲሉ ሰዎች ለመለወጥ እየፈለጉ በጓደኞቻቸው ተጽዕኖ  እየተጎተቱ ወደታች የሚቀሩ ሰዎች ብዙ ናቸው። የኛ ለመልካም ነገር መለወጥ የማይዋጥላቸው ሰዎችን ወዳጆቻችን ብለን ለመጥራት ይከብዳል።

-እውነተኛ ወዳጅህ በስህተትህ አይዳኝህም- የሚወዱን ሰዎች በስህተቶቻችን አይዳኙንም። ስህተቶቻችን እና ማንነታችንን አያዛቡትም። “ትንሽ በሽታ ሰጥቶህ ወዳጅ ጠላትህን ለየው” የሚልው የሃገራችን አባባል ትልቅ እውነትነት  አለው። ሁሉ መልካም በሆነ ጊዜ እና ከፍ ባልን ወቅት ወዳጅ መብዛቱ አይቀርም። በተከበርንበት ሰዓት አልሁ የሚሉን ብዙዎች ናቸው። በተዋረድን፤ዝቅ ባልን  ሰዓት ግን ማነው ከጎናችን የሚቆመው?

-እውነተኛ ወዳጅህ ደስታህን በራስህ መንገድ እንድታገኝ ይፈቅድልሃል- አሳ እና ወፍ ቢዋደዱ አሳም በባህር ውስጥ ወፍም በአየር ላይ ይኖራሉ እንጂ። አሳ ወፏን ለጓደኝነታቸው ስትል በባህር ውስጥ እንድትኖር አታስገድዳትም። ጓደኝነት እና ወዳጅነት ፍሬያማ የሚሆነው ነጻነት ሲኖረው ብቻ ነው።ሁላችንም ደስታን የምናገኝበት የየራሳችን የሆነ መንገድ አለን። እውነተኛ ወዳጅ የሆነ ሰው ሌላው በራሱ መንገድ እንዲደሰት ይፈቅዳል። የገዛ ደስታን መስዋት እንድናደርግ የሚያስገድደን ወዳጅነት መልካም ወዳጅነት አይደለም።

-እውነተኛ ወዳጅህ  ህልም  ፈቺ ነው- ሁሉም ሰው ህልመኛ ነው። ህልማችን ግን ለብዙ ሰዎች ቅዠት ነው። የእውነት ለሚወዱን ሰዎች ግን ህልማችን እውን ሊሆን የሚችል ሃሳብ ነው። ለእኛ ብቻ የሚታዩን ነገሮች (አላማችን ወይም ህልማችን) ለብዙ ሰዎች እውነትነት የላቸውም። ስለዚህ አይሆንም በማለት ህልማችንን ይገድሉታል። እውነተኛ ወዳጅ ግን ምንም እንኳን ለኛ ብቻ የሚታየን ነገር ቢሆንም፤ በኛ ላይ እምነት ስላለው ህልማችን  ቅዠት ነው ብሎ ወደ ኋላ አይስቀረንም።

-እውነተኛ ወዳጅህ ውለታን አይቆጥርም- እከክልኝ ልከክልህ የወዳጅነት ምልክት አይደለም። ያም ሆኖ የብዙዎቻችን ግንኙነት ከእከክልኝ ልከክልህ አይዘልም። በውለታ የተሳሰረ የጥቅም ግንኙንትን እውነተኛ ወዳጅነት ብለን ልንጠራው አንችልም። እውነተኛ ወዳጅ ውለታን ቆጥሮ ሳይሆነ እጁን የሚዘረጋልን፤ ከመልካም ማንነቱ የመነጨ ነው።

ምንም እንኳን ሁላችንም የየራሳችን የሆነ ወዳጅን መለኪያ መስፈርት ቢኖረንም፤ ከላይ የሰፈሩት መስፈርቶች ግን ዘልቂ ግንኙትን ይፈጥራሉ ብዬ አስባለው። ለርስዎ መልካም ወዳጅ ምን ማለት ነው?

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *