“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

እንደትልቅ ሰው አስብ እንደ ህጻን እመን!!!

by | Dec 12, 2016 | ትርጉሞች | 0 comments

(በሚስጥረ አደራው)

በቀደም ጠዋት ይህንን  አባባል ከሰማሁኝ በኋላ፤ ቀኑን ሙሉ በህሊናዬ ሲያቃጭል ዋለ። ማመን ምን ያህል ከባድ ጥበብ መሆኑን ተረዳሁኝ። ሀሳቦቻችን እና ምኞቶቻችን እጃችን ሊገቡ ያልቻሉት፤ አዋቂነትቻን ጣልቃ እየገባብን መሆኑ በግልጽ ገባኝ። እምነት የሁሉም ነገር መሰረት ነው። መቼ እንደሆነ ባላስታውሰውም አንድ ሰው እንዲህ ስል ሰምቼው ነበር “በህይወቴ ቀላሉ ነገር፤ብዙ ሀብት ማካበት ነበር፤ ከባዱ ነገር ግን ያን ያህል ሀብት ማካበት እንደምችል ማመኑ ነበር” ብሏል። የእያንዳንዳችን ስኬት የሚወሰነው በእምነታችን ልክ ነው።

የብዙዎቻችን ችግርም እዚህ ላይ ይመስለኛል። የሚከብደን የምንፈንልገውን ነገር ማግኘቱ ሳይሆን፤ እንደምናገኝ ማመኑ ነው። የሚገርመው ደግሞ ከሌሎች በላይ እኛ በገዛ እራሳችን ላይ እምነት ማጣታችን ነው። ኮንፊሺየስ አንድ ድንቅ አባባል አለው “እሱ እችላልው የሚለውም አልችለውም የሚለውም፤ ሁለቱም ትክክል ናቸው” ይላል። እውነት ነው፣ እያንዳንዳችን የእምነትቻን ውጤቶች ነን። በህይወታችን የምናግኛቸው ነገሮች በሙሉ የእምነታችን ፍሬዎች ናቸው።

ፈጣሪ “የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እምነት ቢኖራችሁ?” ሲል እምነት ምን ያህል ከባድ ክህሎት መሆኑን እያስረዳን ነው። ምክንያቱም ሰናፍጭ እጅግ ደቂቅ፤ አይኑ በቅጡ ለማይሰራ ሰው የማትታይ ደቃቅ ስለሆነች። የዛችን ደቃቅ እህል ያህል እምነት እንዴት ማግኘት ተሳነን? ከተግባሩ በላይ ማመኑ ለምን ከብደን?

ከዚህ በፊት ውሃ እና ዋና(ሊንኩን በመጫን ማንበብ ይችላሉ) በተሰኘው ጽሁፌ ላይ እምነት ምን ማለት እንደሆነ ለሁላችንም በሚገባን ምሳሌ ለማስረዳት ሞክሬዋለው። በጽሁፉ ላይ እንዲህ የሚል መልዕክት ሰፍሮም ነበር

” እምነት ልክ እንደዋና ነው። ዋናተኛ ከውሃው ላይ ለመንሳፈፍ ከፈለገ፤ እጁን ዘርጋ አድርጎ በነጻነት በውሃው ላይ ይወራጫል እንጂ፤ ላለመስመጥ ሲል ዉሃውን ልጨብጥ አይልም። ውሃውን ልጨብጥ ብሎ ግትር የሚል ሰው እጣ ፋንታው መስመጥ ብቻ ነው፤ በውሃ ላይ ለመንሳፈፍ ምንም ነገር መጨበጥ የለብንም ፤ ዋና መዋኘት እና ህይወትን መኖር በጣም ተመሳሳይነት አላቸው”

የሰው ልጅ እውነተኛ ተፈጥሮ  በልጅነቱ ጊዜ ያለው ማንነት  እንደሆነ የሚስማሙ ጠቢባን ብዙ ናቸው። ምክንያቱም በልጅነት ውስጥ ጥርጣሬ የለም፤ የህጻናት እምነት ሰውን ብቻም ሳይሆን አምላክን ሀሴት ውስጥ የሚከት እምነት ነው። ህጻናት ሲረበሹ እና ሲጨነቁ የማይታዩት በሁሉም ነገር እምነት ስላላቸው ነው። ልክ ዋናተኛው በውሃው ላይ እምነት እንዳለው ሁሉ፤ ህጻናትም በዙሪያቸው ባለው ነገር ሁሉ እምነት አላቸው።

ምናልባት በኑሮዋችን ብዙ ነገሮች እምነት አሳጥተውን ይሆናል። እያለፍንበት ያለው ችግር፤ ነገ መልካም ቀን ይሆንልናል ብለን እንዳናስብ ሊጋርደን ይችላል። አንዳንዴ ግን አይናችን እስከዋሻው ጫፍ ድረስ መመልከት ቢሳነው እንኳን፤ መራመዳችንን እስካላቆምን ድረስ መውጫ እንደምናገኝ ማመን አለብን። በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነን በእምነታችን መጽናት፤ የእምነትቻንን ጥንካሬ እና እውነተኛነት ይመሰከራል።

ማታ “ደህና እደሪ” “ደህና እደር” ብለን የምነትኛው እኮ ነገ እንደሚነጋ ስለምናምን ነው። እንዲህ አይነቱን እምነት በምንሰራቸው ነገሮች ሁሉ መተግበር ከቻልን፤ ህይወታችን ሌላ ገጽታ በኖረው ነበር። እምነት ያልተጨመረበት ማንኛውም ምኞት እውን አይሆንም። የሰው ልጅ አቅም ውስን ነው፤ በሚኖረው የእምነት መጠን ግን ትልቅነቱ ይወሰናል። በምኞታችን፤ በህልማችን እና በግባችን ላይ እምነት ይኑረን…….ያኔ ማን ያስቆመናል? ተራራውን ነቅለን በባህር ላይ እስከማስቀመጥ ድረስ!!!

ጹሁፌን በዚህች አጭር ስንኝ እቋጫለው

እምነት ማለት…….

ከሸለቆ  በታች  ሸለቆ ፣ ከተራራ በላይ  ተራራ

ከሠማይ  በላይ  ሠማይ ፣ ከደመና በላይ  ጋራ

ከመኖር  ባሻገር  መኖር ፣ ከሞት  በኋላ  ትንሳኤ

ከዘመን  በኋላ  ዘመን፣ ከኑሮ  ሌላ ህላዌ

ከተስፋ  በኋላ  ተስፋ ፣ ከእውነት  ወዲያ እውነት

ከሸለብታ  ግርጌ  መንቃት ፣ ከሞት  ወዲያ  መሰንበት

አለ ብሎ ማሰብ ……ዝም  ብሎ መገመት

ይሄው  ነው ትርጉሙ ……የእውነት  እምነት  ማለት!

በቃ!!!!!

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *