“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

እኔን? በእንግሊዘኛ ምንድን ነው?

by | Jul 7, 2017 | መነቃቂያ inspiring stories | 1 comment

(በሚስጥረ አደራው) 

ሰው ሲያደናቅፈው፤ ወይም የሆነ አደጋ ሲደርስበት “እኔን” ማለት በእኛ ማህበረሰብ የተለመደ ነው። ያንን ሰው  አወቅነውም አላወቅነውም፤ ለቤተሰባችንም ሆነ ለመንገደኛ “እኔን” ስንል አይምሮዋችን ሁለቴ አስቦ አይደለም። “እኔን” ማለት የለመደብኝ ከእናቴ ነው፤ ሳላውቀው ውስጤ ተዋህዷል መሰለኝ እኔም ሰው ደንቀፍ ሲያደርገው፤ ወይም ሲጋጭ ብቻ የሆነ አስደንጋጭ ነገር ሲከሰት “እኔን” እላለው።

ታዲያ ከሰሞኑን አማርኛ ከማይናገር አንድ ወዳጄ ጋር ደረጃ ስንወጣ፤ አንድ ደረጃ ስቶ ተደናቀፈ፤ እና በሚያስደነግጥ ሁኔታ የሚወድቅ  መስሎ ቆመ። በሁኔታው ደንግጬ “እኔን” ብዬ ጮህኩኝ። ይመስገነው፤ ምንም ሳይሆን ደረጃ መውጣታችንን ቀጠልነው። የእኔ በአማርኛ መጮህ ግራ ያጋባው ሰውዬ ግን “ምን ብለሽ ነው የጮህሽው?” ሲል ጠየቀኝ።

እውነቱን ለመናገር ለማስረዳት ከበደኝ ፤ “እኔን” የሚለው ቃል በእንግሊዘኛ ምን እንደሆን ግራ ገባኝ። ምክንያቱም “እኔን” ቃል ብቻ አይመስለኝም፤ ዝም ብዬ አቻ ትርጉም ብፈጥርለት ግራ የማጋባው መሰለኝ። “Let me think” ብዬ ማሰላሰል ጀመርኩኝ ። መጀምሪያ የመጣልኝ ሃሳብ ይሄ ነበር

ቆይ……ሰው “እኔን” ሲል፤ ጉዳቱን ለእኔ ያድርገው እያለ ነው ስለዚህ ምናልባት “Let it be to me? let your pain be mine? ” ሳቄ መጣ፤ ምናልባት በእኔ የመተርጎም አቅም ፤ የተሰማኝን ብነገረው፤ የማይገባ ነገር አሳስበዋለው ብዬ ተውኩት። “I don’t think there is an English word for that” ብዬ የተርጉሚልኝን ጥያቄውን ዘጋሁት።

ከተለያየን በኋላ ግን፤ በጣም አሰብኩበት። “እኔን” ሳናምንበት ከሚወጡ ቃላቶቻችን አንዱ ነው።  ትርጉሙ በጣም ጥልቅ ነው፤ በየዕለት ተዕለት ወሬያችን እና አጋጣሚዎቻችን እየተወረወረ ተራ መሰለ እንጂ፤ ቃሉስ ክር ነበር፤ የአንድነት ክር፤ የሚያስተሳስር ወሳኝ ቃል። “እኔን” ማለት- ያንተን/ያንቺን መውደቅ አልይ፤ ስቃይህን/ስቃይሽን አልመልከት፤ ያንቺን/ያንተን መቸገር ከማይ እኔን ይቸግረኝ፤ ማለት መሆኑን ማስብ ያሰደነግጣል። ታዲያ እንዴት ብዬ ነው ይህንን የምተረጉመው። ብተረጉመውስ በቅጡ ለማላውቀው ሰው ይህንን ያህል ማሰቤ (አላሰብኩለትም፤”እኔን” ማለት ለምዶብኝ እንጂ) አስመሳይ አያስበልኝም?

አንዳንዴ አኗኗራችን ያሳዝናል፤ በህይወታችን ቁልፍ የሆኑ ነገሮችን ያለቦታቸው እያስገባን ተራ አድርገናቸዋል። ከመጠን በላይ ተጠቅመንባቸው ትርጉማቸውን አሳጣናቸው ፤”Cliche” ሆኑብን ። “እኔን” የሚለውን ቃል በደንብ እንዳስብበት ያደረገኝ ፈተና ነው፤ የትርጉም ፈተና። ቃሉ ምን ያህል የፍቅር ቃል ነው ግን? ከልቡ “እኔን” የሚል ሰው ቢበዛ ብዬ ሳስበው ለውጡ እራሱ ያስደግጣል።

ምናልባት እኔ እስከማውቀው ድረስ “እኔን” በሌሎች ማህበረሰብ ውስጥ መኖሩን እንጃ። ይህንን ጽሁፍ መጻፍ ስጀምር፤ መጀመሪያ የመጣብኝ የደበበ ሰይፉ “ከአክሱም ጫፍ አቁማዳ” የሚለው ግጥም ነበር። ይህ ግጥም “እኔን” የሚለው ቃል ምን ያህል የማህበረሰባችን ምሰሶ እንደሆነ ከተገቢው በላይ አስረድቷል።  በዚህ ግጥም ውስጥ ኢትዮጵያን እረሃብ በጨቀነባት ወቅት ከአንዱ ጫፍ የተነሳው የልመና አቁማዳ  እያንዳንዱን የኢትዮጵያን ክፍል አንኳኩቶ ተመልሶ ከተነሳበት ቦታ ደርሷል። ሁሉም ክልሎች መጨከን አቅቷቸው፤ ከሌላ ለመበደር ሲሞክሩ “እኔን” እያሉ አይደለም? አይምሮዋችን ሳያምንበት ያለፈቃዳችን (Involuntarily) ከአንደበታችን ስለሚወጣ  እንጂ ቃሉስ ታላቅ ቃል ነበረ….በተለይ ከግለሰብ ደርጃ አልፎ ጥቅም ላይ ሲውል!!!

በነገራችን ላይ መተርጎምን ካነሳን አይቀር ፈገግ ያስባለኝን ነገር ላካፋላችሁ። ሬድዮ ላይ ነው የሰማሁት፤ ባልሳሳት “የደራው ጨዋታ” በተሰኘው ፕሮግራም ላይ የአማርኛን ዘፈን ለመተርጎም እንዴት ከባድ እንደሆነ አንድ ፕሮግራማቸው ላይ አቅርበው ነበር። እንደውም አንዱ ፈረንጅ የትዝታን ዘፈን ለመተርጎም ፈልጎ “የእኔ አንጀት” ለሚለው ቃል ቀጥተኛውም ትርጉም “My Intestine” የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል  ሰጥቶት  ወጥ ሃሳቡ ትርጉም አልሰጥ ብሎት እንደነበር ሲናገሩ ሰምቻለው። እሱን አንስቼ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ስንወያይ ደግሞ የመሃሙድን ዘፈን አነሳን ፤ ለምሳሌ “አትስጊ በእኔ ቤት ልብ ይቀርብልሻል” (በጮማው ፋንታ)  የሚለውን እንተርጉም ብንል የሆነ የሆረር ሳውንድ ትራክ ሊያስመስለው ይችላል እንጂ እንዴት ትርጉሙ ሳይዛባ መተርጎም ይቻላል? ብለን ፈገግ በለን ነበር።

ለማንኛውም ቃል፤ ከቃል በላይ ነው!!!እውነተኛው መግባቢያ ስሜት ነው፤ እውነተኛ ስሜት፤ እንጂ ቃላትስ በሽ ነበር!!!

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

1 Comment

  1. Tariku(tare)

    ewnetegna smet enjimkalats besh neber….desss silll

    Reply

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *