“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“አይን አይኑን የሚያዩት ውሃ ቶሎ አይፈላም”

by | Aug 5, 2016 | መነቃቂያ inspiring stories | 0 comments

(በሚስጥረ አደራው)

አለም አንድ ሆናለች በሚባልበት በዚህ ዘመን፤ ነገሮች እጅግ በፈጠኑበት በዚህ ጊዜ፤ የፈለግነውን መረጃ በቀላሉ እና በአፋጣኝ በምናገኝበት ወቅት፤ ነገሮችን በትዕግስት መጠበቁ እጅግ ከባድ ሆኖብናል። የምንፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ በቀላሉ ማግኘት እንደምንችል የምንኖርበት ጊዜ እየሞገተን ነው ያለው። ጥረት እና ትዕግስት ከጊዜ ወደ ጊዜ ዋጋቸው እየወረደ መጥቷል። የጊዜ ፍጥነት፤ የሁኔታዎች መመቻቸት፤ ትዕግስትን ሳይሆን ተስፋ መቁረጥን እንደአፋጣኝ ምርጫ እንድንወስድ አድርገውናል።

እናት አባቶቻችንን ብናስተውል ለነገሮች ያላቸው ጥንቃቄ፤ ለሁኔታዎች ያልቸው ትዕግስት እና አልሸነፍ ባይነት፤ እኛ የዚህ ዘመን ሰዎች ለምን ይህን ያህል ትዕግስት የለሾች እንደሆንን እንድንጠይቅ ያደርገናል። ነገረ ስራችን ሁሉ ፈጣን ነው። ግንኙነታችን ፈጣን፤ እድገታችን ፈጣን፤ ብልጽግናችን ፈጣን፤ ውጤታችን ፈጣን፤ እርምጃችን ፈጣን፤ ጊያዝችን ፈጣን፤ ውሳኒያችን ሁሉ ፈጣን  ነው።ማስታዎቂያችን እራሱ “ጊዜ ይሮጣል”  የሚል ነው። ነገር ግን ጊዜ ነው የሚሮጠው ወይስ እኛ ነን ትዕግስት ያጣነው?

“ለሁሉም ጊዜ አለው” የሚለው የጠቢቡ ሰለሞንን አባባል በየቦታው  ደጋግመን ስንሰማው ተራ እየመሰለን የመጣ ይመስላል። ወይም በራሳችን ትርጓሜ ሌላ ትርጉም ሰጥተነዋል። የምንፈልገው ነገር እኛ በፈለግነው ሰዓት እና ጊዜ ስላልሆነ እደለቢስነት የሚሰማን ሁላችንም ነን። እርግጥ ነው የተመኙት ሳይሳካ ሲቀር፤ የፈለጉት እውን ሳይሆን ሲቀር፤ ያለሙት ሳይፈታ ሲቀር፤ እንደው እንደዘበት ” ሁሉም ለበጎ ነው” ብሎ መቀበሉ ቀላል ነገር አይደለም። ሁሉም ነገር በጊዜው  እንደሚሆን አምኖ መቀበሉ ያቅተናል ብቻም ሳይሆን፤ ከፈጣሪ ጋርም እሰጣ እገባ የምንገባበት አጋጣሚ ብዙ ነው።

“አይን አይኑን የሚያዩት ውሃ ቶሎ አይፈላም” ይባላል። ብዙን ግዜ እንደው በደፈናው ብናየው፤ የምንጓጓላቸው ነገሮች ወይም እጅግ አብዝተን የምንጠብቃቸው ነገሮች ሳይሳኩ ይቀራሉ። እንደውም ጉጉታችን እና ምኞታችን ልካቸውን አልፈው ጭንቀት ይሆኑብናል። ልክ አይን አይኑን ሲያዩት ውሃ ቶሎ እንደማይፈላ ሁሉ፤ እውን እንዲሆኑ የምንጓጓላቸው ነገሮች እውን ለመሆን እረጅም ጊዜ የወሰዱ ይመስለናል። እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን፤ ምኞቶቻችን እና ፍላጎቶቻችን እረጅም ጊዜ ወስደው ሳይሆን፤ የእኛ ትዕግስት ማጣት ጊዜ የሮጠ እንዲመስለን ስላደረገው ብቻ ነው። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የአንስታየን የንጽጽር ቲዎሪ ትርጉም የሚሰጠን። አንድን ነገር ችላ ስንለው ያለጊዜው ቶሎ የደረሰ ይመስለናል ፤ በአንጻሩ እጅግ ስንጓጓ ጊዜው አለቅጥ የረዘመ ይመስለናል።

ሁላችንም የየራሳችን የሆኑ ፍላጎቶች እና ምኞቶች አሉን፤ አንዳንዶቹ ግዜ የሚሰጡን አንዳንዶቹ ደግሞ አሁኑኑ እውን እንዲሆኑ የምፈልጋቸው ናቸው። ፍላጎታችን፤ ጥያቄያችን እና ምኞታችን ምንም ሆነ ምን ያለጊዜው የሚከወን ምንም ነገር የለም። የእኛ ሃላፊነት ከእኛ የሚጠበቀውን ሟሟላት ብቻ ነው። ጊዜን የማራቅም ሆነ የማቅረብ ምንም አቅም የለንም። ብዙዎቻችን አላስፈላጊ ጭንቀት እና ውጥረት ውስጥ የምንገባው፤ ከግዜ ጋር እሽቅድድም ስለምንጫወት ነው። የራቀውን ለማቅረብ፤ የቀረበውን ለማራቅ የማይሆን እልህ ከጊዜ ጋር እንጋባና እንሸነፋለን።

የዛሬው  መልዕክቴ ይህ ነው “አይን አይኑን የሚያዩት ውሃ ቶሎ አይፈላም” እንደሚባለው፤ አለቅጥ ፍላጎት እና ምኞታችን ላይ አናተኩር፤ የጊዜን የበላይነት አምነን መቀበል ይኖርብናል። ዳይላ ላማ ከዚህ  ጋር የሚዛመድ አባባል አላቸው “የተመኘቱን አለማግኘት፤ አንዳንዴ መታደል ነው” ብለዋል። የተመኘነው ነገር አሁን ባይሳካ ጊዜ የተሻለ ነገር ይዞ ሊመጣ አስቧል ማለት ነው። እስካሁን ብዙ ለፍተን ያሰብነውን እውቅና አላገኘን ይሆናል፤ ብዙ ሞክረን የተመኘነውን ትዳር አልሰጠን ይሆናል፤ ብዙ ጥረን ያሰብነው ስኬት ላይ አልደረስን ይሆናል……..እኛ ባሰብነው ጊዜ አልሆነም ማለት ግን ፈጽሞ አይሆንም ማለት አይደለም። “ሁሉን በጊዜው ውብ አድርጎ ሰራው ” እንደሚለው ቅዱስ መጽሃፍ፤ ውብ የሆኑት ነገሮች ሁሉ እውን የሚሆኑት እኛ ባልነው ሳይሆን እሱ በፈቀደው ጊዜ ብቻ ሲከወኑ  ነው።  ውሃው እስኪፈላ አይን አይኑን እያየ እንደሚጠብቅ ሰው አንሁን ትዕግስት ያሳጣልና……..ውሃውን በስርዓቱ ጥደን ዞር ስንል ግን በጊዜው ፈልቶ እናገኘዋለን። በህይወታችን ውስጥም ተመሳሳይ አመለካከት ይኑረን……ሃላፊነታችን እንወጣ፤ ከእኛ የሚጠበቀውን እናድርግ……ቀሪውን ግን ለጊዜው ትተን ዞር እንበል።

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *