“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

አንድ ሺህ መስታወቶች

by | Mar 19, 2015 | መነቃቂያ inspiring stories | 0 comments

ያንተ ተጽዕኖ እስከ ምን ድረስ ይመስልሃል? አስተሳሰብህ ኑሮህ ላይ፤ ጤንነትህ ላይ፤ ከሰዎች ጋር ያለህ ግንኙነት ላይ፤ ሃብትህም ላይ፤ ምን ያህል ድርሻ አለው ብለህ ትገምታለህ ?ብዙዏችን እራሳችን (በተለይም አስተሳሰባችን) የራሳችን ህይወት ላይ ያለውን ትልቅ ተጽዕኖ አናውቅም። ጥቂቶች ግን ይህንን ሚስጥር ስለሚያውቁ፤ አስተሳሰባቸውን በመሞረድ አይምሮዋቸው ከተለመደው በላይ እንዲያገለግላቸው ሲያደርጉ እና ህይወታቸው እንደ ተዓምር ሲቀየር ይታያል። ይህ አርዕስት ሰፊ ነው…….ለዛሬ አለምን የምናይበትን መነጸር የሚያስቀይረንን ታሪክ አገኘሁና እንዲህ አሰናዳሁት።

በድሮ ጊዜ አንድ መንደር ውስጥ በመስታወቶች የተሰራ አንድ ዝነኛ ቤት ነበር። በመንደሩ የሚኖሩ ሁለት ውሾች ወሬውን ይሰሙና ቤቱን ለመጎብኘት ይጓጓሉ።በመጀመሪያ አንደኛው ውሻ በደስታ ጓግቶ ወደ መንደሩ ሄደ፤ ጭራውን በደስታ እያወዛወዘ በመስታወት ወደ ተሰራው ቤት ገባ። ቤቱ እንደተባለውም በሺህ መስታወቶች የተገነባ ነበር። ውሻው በደስታ እያለከለከ፤ ጭራውን በሃሴት እያስጨፈረ….ሲገባ …ሌሎች አንድ ሺህ ውሾች በደስታ እያለከለኩ፤ እንደሱ ጭራቸውን እያስጨፈሩ ተቀበሉት። ለደቂቃ በመስታወቱ ከሚመለከቱት ውሾች ጋር ሲስስቅ  እየሳቁ….ሲዘል እየዘለሉ አብረው አሳለፉ…….ወደ ቤቱ ሲመለስም “በጣም ደስ የሚል ቤት ነው…….ሁሉም በደሰታ የሚጨፍርበት …..አዘውትሬ መምጣት አለብኝ” ብሎ ለራሱ ቃል ገባ

በሌላ ቀን ሌላኛው ውሻ……በመስታወት የተሰራውን ቤት ሊጎበኝ ወደ መንደሩ ተጓዘ። ይህኛው ውሻ እንደመጀመሪያው ውሻ ደስተኛ አልነበረም…..ተናካሽ እና በሆነው ባልሆነው የሚያንባርቅ ነበር። ከመንደሩ ደርሶ ወደ መስታወቱ ቤት ሲዘለቅም፤ ልክ እንደሱ የተኮሳተሩ አንድ ሺህ ውሾችን በመስታወቱ ውስጥ ተመለከተ፤ በንዴት ሲጮህ እነሱም ይጮሃሉ…..ሊናከስ ሲሞክር በመስታወቱ ውስጥ ያሉት ልክ እንደሱ ሊናከሱ ይሞክራሉ….ቤቱን ጥሎ በንዴት ወጣ “ምን አይነት የአውሬ ቤት ነው ሁለተኛ እዚህ ቤት አልመጣም” ብሎ እያጉረመረመ ወደ ቤቱ ተመለሰ።

ሁለቱም ውሾች በሺህ መስታወቶች ውስጥ የተመለከቱት የራሳቸውን ምስል ነው። በመስታወቶቹ ውስጥ የተመለክቱት የራሳቸውን ማንነት እና አመለካከት ነው። ባህሪያቸው ግን ይለያያል። ባህሪያቸው በመለያየቱ አጋጣሚያቸው ተለያየ፤ በቤቱ የነበራቸው ልምድ ተለያየ፤ አለም እንደ አመለካከታቸው አስተናገደቻቸው (የመስታወት ቤቱ እንደ ጸባያቸው አይደል የቀበላቸው?)

እኒህ ውሾች የኛ ተምሳሌቶች ናቸው። በሺህ መስታወት የተገነባው ቤት ደግሞ አሁን እየኖርንባት ያለችው አለም። ህይወት ልክ እንደ መስታወት ናት፤ ስንስቅላት ትስቅልናለች፤ ስንጮህባት ትጮህብናለች። በዙሪያችን ከምናያቸው ውስጥ ብዙ ልንለውጣቸው የምንሻው ነገሮች ይኖራሉ። ግን እንዴት መለወጥ ይቻላል?……መልሱ አይቻልምም ይቻላልም ነው። ከእኛ ውጪ ያለውን ነገር መለወጥ ባንችልም፤ አመለካከታችንን ከለወጥን ግን ሁሉም ነገር ይለወጣል። አመለካከታችንን ስንለው፤ በውጪ የምናያቸው ነገሮች ሁሉ መልካቸውን ይለውጣሉ።

እንደመጀመሪያው ውሻ ደስተኛ መሆን ከቻልን፤ ዙሪያችን በመልካም ነገሮች ይከበባል። ለሳቃችን ሳቅ ይመለስልናል፤ ለምስጋናችን ምሰጋና ፤ ለአክብሮታችን አክብሮት፤ ለደግነታችን ደግነት ይመለስልናል (ሁሌም ባይሆን በአባዛኛው፤ ምክንያቱም እዚህ ምድር ላይ ፍጹም የሆነ ነገር ስለሌለ) ። እንደ ሁለተኛው ውሻ ኑሯችን በፀለምተኝነት የተሞላ ከሆንም፤ እንደዛው። ለንዴታችን ንዴት ይመለስልናል፤ ለግልምጫችን ግልምጫ፤ ለሃዘናችን ሃዘን፤ ለንቀታችነ ንቀት፤ ለመጥፎ ምኞታችን መጥፎ ምኞት።ህይወት ዘመናዊውን ንግድን እስካሁን አልለመደችም። የምትገበያየው “በልውውጥ ገበያ ነው” የሰጠናትን ያህል ትሰጠናለች።

ማንኛውንም  ነገር ለመለወጥ ስናስብ መጀመሪያ ከፊታችን በመስታወት ውስጥ ከምናየው  ሰው እንጀምር።

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *