“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

ነጸብራቅ /Reflection/

by | Aug 16, 2017 | Guest writer-እንግዳ ጸሃፍት | 3 comments

(በሚስጥረ አደራው)

ኑሮን በአጭሩ ከሚገልጹ ቃላቶች ውስጥ “ነጸብራቅ” አንደኛው ነው ልበል?  አንዴንዴ ዞር ብለን መንገዳችንን ስናጤነው፤ ተመሳሳይ ኩነቶችን ( Similar Patterns) ማየታችን የማይቀር ነው፤ ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸውን ሰዎች ማግኘት ወይም መጎዳኘት፤ ተመሳሳይ ስህተቶችን መስራት፤ ተመሳሳይ መልካም ዕድሎችን መሰብሰብ፤ ብቻ ተቀራራቢ የሆኑ ነገሮችን በምናሳልፈው ህይወት ውስጥ ማየታችን የተለመደ ነው።

ይህ መመሳሰል ዝም ተብሎ እንደአጋጣሚ የሚታለፍ ነገር አይደለም። ምክንያቱም አጋጣሚ አይደለምና። ለመቀበል ቢከብድም፤ እውነታው ግን በኑሮ ሂደት ውስጥ የሚገጥሙን ነገሮች ሊያሳዩን የሚሞክሩት የራሳችንን የእምነትና የአስተሳሰብ ነጸብራቅ ነው። ይህን “ በዙሪያችን የምናየው የራሳችንን ነጸብራቅ ነው” የሚለውን አስተሳሰብ፤ መንፈሳዊ መጽሃፍቶች፤ የስነ ልቦና ትምህርቶች እንዲሁም ባህላዊ አባባሎች ሲያሰምሩበት የኖሩት ነገር ነው።

ይህንን ጽሁፍ ለመጻፍ ስነሳ በመጀመሪያ የራሴን ኑሮ ለመቃኘት ሞከርኩኝ፤ እውነትም ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸውን ሰዎች ስስብ፤ ተመሳሳይ ስህተቶችን ስስራ፤ ተመሳሳይ መንገዶችን ስመርጥ እንደነበር ለመረዳት ጊዜ አልፈጀብኝም። ለምን? ምክንያቱም ሳናውቀው በሰዎች ውስጥ የምንፈልገው (የምንስበው) የራሳችንን ባህሪ ስለሆነ፤ ተቃራኒ ቢመስልም እንኳን።

ነገር መቼም በምሳሌ ይበልጥ ወደ ህሊና ይዘልቃልና  ፤ከአንድ የግጥም መድብል (Coleman Barks- Chinese Art and Greek Art) ላይ ያገኘሁትን በግጥም መልክ የተጻፈ የሱፊ ታሪክ ላካፍላችሁ። በድሮ ጊዜ የቻይና እና የግሪክ ጠቢባን ማንኛቸው የተሻለ የስዕል ጥበብ እንዳላቸው ለማስመስከር ክርክር ይጀምራሉ። ክርክሩ ሲጧጧፍ ከቃላት ጦርነት በበለጠ ስዕሎቻቸውን  በተግባር እንዲያሳዩ ተወሰነ። ቻይናዎቹ ብዙ ቀለማት እንዲሰጧቸው ሲጠይቁ ግሪኮቹ ግን ምንም ቀለም እንደማይፈልጉ አሳወቁ። በመጋረጃ በተከፈለ ክፍል ውስጥ፤ ለየብቻ ተቀምጠው የሚወዳደሩበትን የስዕል ስራ እንዲጀምሩ ተደረገ። ቻይናዎቹ ከመቶ በላይ ቀለማትን ተጠቅመው ስዕላቸውን መሳል ተያያዙ። ግሪኮቹ ግን ስዕል በመሳል ፋንታ ዝም ብለው ግድግዳውን ማጽዳት ጀመሩ።  በየቀኑ ቻይናዎቹ መዓት ቀለማትን እየተጠቀሙ  ስዕላቸውን ሲስሉ፤ ግሪኮቹ ግን ዝም ብለው ግድግዳቸው ሰማይ እስኪመስል ድረስ ማጽዳታቸውን ቀጠሉ። በመጨረሻ ቻይናዎቹ  ስራቸውን መጨረሳቸውን በደስታ አበሰሩ። የሚዳኛቸው ንጉስም በቅድሚያ የቻይናዎቹን ስራ ገብቶ ሲመለከት በቀለማቱ ድምቀት ተደነቀ፤ ቀጥሎ የግሪኮቹን ለመመልከት መጋረጃውን ሲያስገልጥ፤ ቻይናዎቹ የሰሩት የስዕል ነጸብራቅ ግሪኮቹ ባጸዱት ንጹህ ግድግዳ ላይ  ተንጸባርቆ ታየ። እንደውም ከተፈጥሮ ብርሃን ጋር ተዋህዶ ከቻይናዎቹ በላይ ልብን የሚሰርቅ ጥበብ ሆነ። ገጣሚው ግጥሙን ሲያጠቃልል የግሪኮቹን ስራ  “የሱፊ ጥበብ” ሲል ይገልጸዋል፤ በመጽሃፍትና በፍልስፍና ሳይሆን፤ ልባቸውን (ፍቅራቸውን- Make their loving clearer and clearer ነው የሚለው) እንደመስታወት በማጽዳት እያንዳንዷን ቅጽበት ያያሉ፤ መልሰውም ያንጸባርቃሉ፤  እራሳቸውን በሌላ ውስጥ ይመለከታሉ፤ ሌሎችም እራሳቸውን በእነሱ ውስጥ እንዲመለከቱ ያደርጋሉ ሲል ያሞግሳቸዋል።

የእኛ ኑሮ ከቻይናዎቹ እና ከግሪኮቹ የስዕል ፉክክር የተለየ አይደለም። እኔን እንደገባኝ፤ በእኛ ኑሮ ውስጥ በመጋረጃ የተከፈሉት አስተሳሰባችን እና በተግባር የሚገጥሙን ነገሮች ናቸው። በአንደኛው ክፍል አስተሳሰባችን ሲገኝ፤ በሌላው ክፍል ኑሮዋችን ይገኛል። አስተሳሰባችን የሳለውን ስዕል፤ ኑሮዋችን ያንጸባርቀዋል። የቻይናዎቹ ስራ አስተሳሰባችን ሲሆን፤ የግሪኮቹ ነጸብራቅ ደግሞ በእውን የሚገጥሙን ነገሮች ናቸው። ማጽዳቱ የሚያመላክተው ደግሞ፤ ንቃትን ወይም Awareness ይመስለኛል። የበለጠ ግድግዳው ሲጸዳ፤ ስለራሳችን ያለን እውቀት ይጨምራል፤ ሁሉም ነገር  የማንነታችን ነጸብራቅ መሆኑ በተሻለ መልኩ ይገባናል። ዓለምን በሌላ መነጽር እንድናይ የሚያስችለን አንዱ ጥብብ ፤ የሚገጥሙንን ነገሮችን እንደ እራሳችን ነጸብራቅ መመልከቱ ነው (Viewing our experiences as the reflection of our thoughts and deepest emotions) ።

ሌላው ቢቀር ሌሎች ሰዎች ላይ የምንጠላው ባህሪ በራሱ፤ እኛ ውስጥ ያለውን ድብቅ ነገር እያሳየን ነው። ለሰዎች እና ለአጋጣሚዎች የምንሰጠው ምላሽ፤ ውስጣችንን እንደ ግሪኮቹ ግድግዳ አንጸባርቆ ያሳያል። የምንናደድባቸው፤ የምንደሰትባቸው፤ የምንጨቆንባቸው፤ የምንመሰገንባቸው ነገሮች በሙሉ የሚያንጸባርቁት ውስጣዊ ባህሪ አለ። እርግጥ ነው ነጸብራቁን በቀላሉ ማየት ከባድ ነው ምክንያቱም የተደበቁ ባህሪያቶቻችንን በቀላሉ ማየት ስለሚከብደን።ለዛም ነው ብዙ ስራና እውቀትን ሳይሆን ብዙ ጽዳትን የሚጠይቀው። እንዲህ የሚሰማኝ ለምንድን ነው ብለን፤ በስሜቶች ውስጥ ሁሉ ባህሪያችንን እና አስተሳሰባችን እንድንጠይቅ ያስገድደናል። ያኔ የሆነው ሁሉ ለምን እንደሆነ በትንሹም ቢሆን መረዳት ይቻለናል።

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

3 Comments

  1. Semira

    Thank you mistre

    Reply
  2. Kedir

    Good job. Keep it up. Thanks

    Reply
  3. Andebet

    እራሴን ያየሁበት ጽሁፍ ስለሆነ አመሠግናለሁ። ብዕርህ ይለምልም

    Reply

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *