“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

በአንገታችን ላይ ያለውን ሀብል ፍለጋ……

by | Dec 26, 2016 | መነቃቂያ inspiring stories | 0 comments

(በሚስጥረ አደራው)

ሳምንቱን ሙሉ የስልኬን ቻርጀር ፈልጌ አጥቼው ጠፋ ብዬ ተስፋ ቆረጬ ነበር። አዲስ ቻርጀር ለመግዛት በማሰብ ላይ ሳለው፤ ዛሬ ጠዋት ድንገት አገኘሁት። ያገኘሁት ደግሞ አስር ጊዜ ፈልጌ ካጣሁበት ከቦርሳዬ ውስጥ ነበር። በራሴ ሳቅኩኝ……እንኳንም ሌላ ከመግዛቴ በፊት አገኘሁት ብዬ ደስ አለኝ። ግራ የገባኝ ግን፤ ያለማጋነን ይህንን ቦርሳ ደግሜ ደጋግሜ ፈትሼዋለው፤ እንዴት አላየሁትም? የሚለው ነው። ነገሩ የገባኝ በኋላ ነው፤ ለካ ቻርጀሩን ያስቀመጥኩት ብዙም በማልጠቀምበት ኪስ ውስጥ ነበር።

እዚህ ላይ ነው ከዚህ በፊት ደጋግሜ የሰማሁትን የሩሚን ግጥም ያስታወስኩት።

“You wander from room to room
Hunting for the diamond necklace
That is already around your neck!”

“በአንገትህ ላይ ያለውን ሀብል ፍለጋ፤ ከክፍል ክፍል ትዞራለህ” ማለቱ ነው። የኔም የዛሬው ጠዋት ገጠመኝ ከዚህ አልተለየም። ነገር ግን ይህ የህይወት ሚስጥር በስልክ ቻርጀር ወይም በአንገት ሀብል የሚያቆም አይምስለኝም። አጠጋብችን ሆነው ሳሉ፤ እሩቅ ቦታ የምንፈልጋቸው ስንት ነገሮች አሉን? አንገታችን ላይ ታስረው በየክፍሉ እየበረቀስን ለማግኘት የምንደክምላቸው ፤ብዙ አመት አብረውን ከርመው ሳለ፤ እኛ ግን ገና ይመጣሉ ብለን የምንጠብቃቸው ብዙ ነገሮች አሉን። የሌሉን የሚመስለን፤ በሚስጥር ኪሳችን ውስጥ ተደብቀው ያሉ እጅግ ብዙ ሀብቶች አሉን።

አንዳንድ ሰዎች ለምን እራሳቸውን እንዳማይለውጡ ስትጠይቋቸው እንዲህ አይነት መልስ ይሰጣሉ “እራሴን እስካገኝ”፤ ታዲያ ይህ አንገት ላይ የታሰርን ሀብል ሌላ ቦታ እንደመፈለግ አይደለም? ተሰጥዋችን እና ችሎታችን እንዲሁም ማንነታችን እኮ አንገታችን ላይ እንደታሰረው ሀብል ነው። አብሮን የኖረ ሆኖ ሳለ….እኛ ግን ሁሌም ፍለጋችን ውጪ ውጪውን ነው። ለዚህም ነው ለምንፈልገው ኑሮ የሚረፍድብን ብሎም የማንደርሰው።

ከዚህ ጋር የሚያያዝ አንድ ሌላ ታሪክ ጨምሬ ላካፋልችሁ፤ ሰውየው የቤቱን ቁልፍ ቤቱ ውስጥ ይቆልፍበትና ይወጣል። ከሄደበት ሲመለስ ቁልፉን ፍለጋ ይጀምራል። ከበሩ ደጃፍ ላይ እየተዘዋወረ ፍለጋውን ይያያዘዋል። በእሱ በኩል የሚያልፍ አንድ ሰው ይመለከተውና “ቁልፍህን እዚህ አካባቢ ጥለኸው ነው?” ሲል ይጠይቀዋል። አብሮት ለማፈላለግ ማለት ነው። ይሄኔ ሰውየው “አይ ቁልፉን እንኳን ውስጥ ነው የቆለፍኩበት” ይላዋል። መንገደኛውም ግራ ተጋብቶ “ታዲያ ለምን ውስጥ የጣልከውን ቁልፍ ውጪ ትፈልጋለህ” ሲለው፤ ሰውየውም “አይ ውስጥ ጨለማ ስለሆነ ነው” ሲል መለሰለት አሉ።

ውጪ ብርሃን ስለሆነ ብቻ ውስጥ የጣልነውን ነገር መፈለግ የእኛም ልማድ ነው። በቤታችን ያጣነውን ሰላምና ፍቅር ውጪ የምንፈልግ ስንቶቻችን ነን? ውስጣችን የጠፋውን ማንነት ብርሃን ባየንበት የምንፈልግ በጣም ብዙዎቻችን ነን።

በህይወታችን ለሚገጥሙን ችግሮች አብዛኛው መፍትሄ ውስጣችን ነው ያለው። የኛ ሞኝነት ግን ልክ ሀብሉን በአንገቱ አስሮ በፍለጋ እንደሚደክመው ሰውዬ ወይም የቤቱን ቁልፍ በውስጥ ዘግቶበት ብርሃን ስላገኘ ብቻ ውጪ ውጪውን እንደሚፈልገው ሰው መሆናችን ነው። ፍለጋችን ከውስጣችን ካልጀመረ…..የምንፈልገውን ማንኛውንም ነገር ለማግኘት ብዙ መድከማችን አይቀርም።

የምንመኘው ፍቅር፤ የምንጓጓለት ቤተሰብ፤ የምንፈልገው ማንነት ምናልባት አንገታችን ላይ ታስሮ ሊሆን ይችላልና፤ ውጪ በፍለጋ ከመድከማችን በፊት መፍትሄውን ውስጣችን እንፈልግ። የጠፋብን ሰላም እና ፍቅር የተደበቀው እኛው ውስጥ ቢሆንስ…..ከሌላ ሰው ልብ ውስጥ ከመፈለጋችን በፊት የኛን ጓዳ እንፈትሽ። አብዛኛው የችግሮቻችን መፍትሄ በእርግጥም አንገታችን ላይ ታስሯል። ሲጀምር ሳይጠፉብን ለምን በፍለጋ ህይወታችን ይባክናል?

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *