“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

በአባቴ ምክንያት ቆሜ እንዳልቀር ፈራው

by | Jun 19, 2016 | Guest writer-እንግዳ ጸሃፍት | 0 comments

በሚስጥረ አደራው

በአባቴ ምክንያት ቆሜ እንዳልቀር እፈራለው። እንዲህ ብዬ ወሬዬን ስጀምር የማታውቁትን አባቴን በክፉ አይናችሁ እንዳታዩብኝ እሰጋለው። ቆሜ የምቀረው አባቴ ምርጫዬን ስላልወደደልኝ አይደለም፤ ወይም እሱ የመረጠልኝን ስላላገባው። ለሱ ሰው ሁሉ መልካም እስከሆነ ድረስ እኩል ነው።

ወላጆቼ በአንድ ጎጆ ኑሮዋቸውን ሀ ብለው ከጀመሩ እነሆ ግማሽ ምዕተ ዓመት ሊሆናቸው ነው። እርግጥ ነው በእኛ በኢትዪጵያን ዘንድ ይህ አዲስ ነገር አይደለም። ምክንያቱም በሚያስደንቅ ሁኔታ ሳይተዋወቁ የሚጋቡት የድሮ እናት እና አባቶቻችን ሞት እስኪለያቸው አብረው ይዘልቃሉ። አሁን በእኛ ጊዜ ደግሞ በመጠናናት እና በመተዋወቅ ብዙ ጊዜ እናሳልፍና፤ ትዳራችን ግን ሌላ ዳገት ሆኖብን ሲከብደን ይታያል። የእኛ እናት እና አባቶች 50 ወይም 40 አመታት ኖሩ ስንል፤ ምንም ጠብ ሳይኖርና ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው እንዳልሆነ እርግጥ ነው። እንደዛ የሚሉ ባለትዳሮች እንደኔ እውነት እየተነናገሩአይደለም። ትዳርን የሚያዘልቀው ፈጽሞ አለመጋጨት አይደለም፤ ወይም እየተሸነጋገሉ መኖር። እንደሚመስለኝ የእኛ እናት እና አባቶች እረጅም ጊዜ አብሮ የመኖር ሚስጥር፤ ሁለቱም ከራስ ፍላጎቶቻቸው በላይ ጎጆዋቸውን ስለሚያስቀድሙ ይመስለኛል። አንዳቸው ቢያጠፉ፤ ትልቁን ምስል በመመልከት ያሳልፉታል። ትዳር ለነሱ በቀላሉ ተገብቶ የሚወጣበት ክፍት ጎጆ አይደለም። ለትዳር ያላቸው ክብር፤ ለቤተሰብ ያላቸው ሃላፊነት መቻቻልን ስለሚያስተምራቸው ይመስለኛል ስኬታማ የሚሆኑት።
የኔ የዛሬ ሃሳብ እንኳን ስለትዳር አልነበረም; እንደው እንደመንደርደሪያ ተጠቀምኩበት እንጂ። ዛሬ የሚከበረውን የአባቶች ቀንን ሳስብ ትንሽ ስለ አባቴ ማለት ፈለግኩኝ። ስለ አባቴ አልኩኝ እንጂ ለኔ ኢትዮጵያውያን አባቶችች የሚያመሳስላቸው ብዙ ነገር አለና ብዙዎቻችን የሚወክል ይመስለኛል።

ሰዎች በአባቴ ምክንያት ቆሜ ቀረው ስላቸው፤ አባቴን ሊወቅሱት ይዳዳቸዋል። ምክንያቴ ግን የሚያስወቅሰው ሳይሆን፤ የሚያስመሰግነው ነው። አባቴን ስጠራው አቢዬ ብዬ ነው። በዚህ እድሜዬ እንኳን እሱ ፊት እንደ ህጻን የሚያደርገኝ ነገር አለ። ያቀብጠኛል፤ እንድቀብጥ ባይፈቅድም እንኳን በግድ እቀብጣለው። እቀብጣለው ስል፤ እራሴን እንድሆን ይፈቅድልኛል፤ በስህተቴ እንዳላፍር፤ በማንነቴ እንዳልሸማቀቅ፤ ሃሳቤን እንዳካፍለው፤ ውሎዬን እንድተርክለት ሁሌም ዝግጁ ነው። ታዲያ ከዚህ በላይ መቅበጥ አለ?
የሚኮራብኝ ባልሆንም፤ አባቴ ግን በእኔ ይኮራል፤ የራሴን ህይወት ስመለከት ምንም የሚያኮራ ስኬት ባይኖረኝም በአባቴ ፊት ግን እንደጀግና እታያለው። ሲከፋኝ መሸሸጊያ፤ ስደሰት መቦረቂያ ቦታዬ ቤቴ ነው። ለዚህ ነው ቆሜ ልቀር ነው ያልኩት። በሴት ልጅ ህይወት ውስጥ የአባት ተጽ ዕኖ ቀላል አይደለም። በወንድ ልጅ ህይወት ውስጥ ደግሞ የእናት ተጽዕኖ እጅግ ወሳኝ ነው። ምክንያቱም ልጆች አድገው የራሳቸውን ኑሮ ሲመሰርቱ፤ ወንድ ልጅ እናቱን የምተምስል ሴት ደግሞ አባቷን የሚመስል ሰው መፈለጋቸው ግድ ስለሆነ። ለዚህ ነው ቆሜ እንዳልቀር ፈራው ያልኩት፡))) አባቴ ባልን የመመዘኛ መስፈርቱ እላይ ስለሰቀለብኝ።
የአባቴ ፍቅር እና እንክብካቤ ከዛ ያነሰ ፍቅርና እንክብካቤን እንዳልቀበል አስገደደኝ። ከቤቴ የወረስኩት መልካም ነገር ከሌላው የሚገባኝን እንጂ የሚሰጠኝን እንዳልቀበል አስተማረኝ። አባቴ እናቴን የሚያይበት መንገድ፤ አባቴ ቤቱን የሚያስተዳድርበት መንገድ እኔም እንደዛ አይነት ትዳር እና ሰው እንድመኝ አድርጎኛል። አባዬ ምናልባት ልጄ ለምን ሰው ትመርጣለች ብለህ የምታስብ ከሆነ፤ ምክንያቱ አንተ ነህ። ያንተ መልካምነት እና ትልቅነት ትንንሽ ነገሮችን እንዳልቀበል አስለምደውኛል። ሁሌ ወርቅ የሚሸለም ሰው ነሃስ ቢሰጡት መች ያረካዋልና። አንተም ወርቅ አስለምደኽኛል፤ ፍቅርን፤ እንክብካቤና እና ደስታን አስተምረኸኛል……….ሴት ብሆንም እንደማንም ሰው የራሴ ኑሮ መምራትን እንደምችል አሳምነኸኛል። እናም የትዳር አጋሬን ስመርጥ በአባቴ መስፈርት ነው……..
መልካም የአባቶች ቀን፤ እረጅም እድሜ እና ጤና ለሁሉም አባቶች ይሁን። እንደው የአባቶች ቀን ሆነ ስለአባት ብቻ አነሳን እንጂ …..የእናትን ነገር ከጀመርን ደግሞ ማብቂያም የለን። ለሁሉም አባቶች መሰረት እናቶቻችን ናቸውና።

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *