“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

በመተው….

by | Dec 11, 2017 | Guest writer-እንግዳ ጸሃፍት | 2 comments

(በሚስጥረ አደራው)

በቀደም ለታ አንዲት የማደንቃት ድምጻዊት ቃለመጠየቅ ሲደረግላት እየሰማሁኝ ነበር። ይህች ምርጥ ኢትዮጵያዊ ድምጻዊት ባለትዳር ነበረችና ጋዜጠኛው የሚከተለውን ጥያቄ ሰነዘረ።

“በዚህ ሙያሽ ላይ ባለቤትሽ እርዳታ ያደርጋል? ይደግፍሻል?”

“ባለቤቴ ይደግፈኛል……በመተው ይደግፈኛል፤ እራሴን እንድሆን በመተው፤ የስራ ቀጠናዬ ውስጥ ባለመግባት በመተው ይደግፈኛል” ብላ መለሰች። መልሷ ውስጤ በእጅጉ ስለገባ ይህንን አጭር ጽሁፍ እንድሞነጭር መነሻ ሆነኝ። ምናልባት የድምጻዊቷን ማንነት መግለጽ ካለብኝ፤ ድምጻዊት ዘሪቱ ከበደ ናት።

እውነትም በተመው ብቻ ብዙ ሰው መርዳት እንችላለን። ሌላ ነገር ማገዝ ቢያቅተን እንኳን በመተው ብቻ ያ ሰው ሙሉ አቅሙን እንዲጠቀም እንፈቅድለታለን። ከዚህ ቀደም በአንደኛው የማነቃቂያ ጽሁፌ ላይ የተጠቀምኩትን አጭር ታሪክ በድጋሜ ላንሳው። በአንድ የክረምት ወቅት፤ ሁለት ህጻናት እየተጓዙ ነበር። እየተጓዙበት የነበረው መሬት በረዶ የሰራ ነበርና በጥንቃቄ መጓዝ ነበረባቸው።ምክንያቱም መሬቱ ቢሰነጠቅ የሚቀበላቸው እጅግ የቀዘቀዘ ውሃ ነበርና። አንድ ሰው ከሰመጠም የሰመጠውን ሰው ለማውጣት እጅግ ከባድ ጉልበት ይጠይቃል። ታዲያ በጉዞዋቸው መካከል በረዶው ይሰነጠቅና አንደኛው ልጅ ይሰምጣል። ሌላኛው ልጅ ጓደኛውን ለማዳን ያንን የተጋገረ በረዶ በሰፊው መፈረካከስ ነበረበት፤ ለዛ ደግሞ ከፍተኛ ጉልበት ይጠይቃል። ሲበዛ የጨነቀው ወጣት፤ ጓደኛውን ለማዳን ይሯሯጥ ጀመረ፤ በአካባቢው  ማንም  ሰው አልነበረምና፤ እየሮጠ ሄዶ ከአንድ በረዶ ካደረቀው ዛፍ ላይ ትልቅ ቅርንጫፍ ይዘነጥልና ያለ የሌለ ጉልበቱን ተጠቅሞ ጓደኛውን ከተቀረቀረበት በረዶ እንደምንም ብሎ ያወጣዋል።

ቀጥሎ የሰፈሩ ሰዎች የሆነውን ሲሰሙ ግራ ተጋቡ። ደቃቃው ወጣት በምን አቅሙ ያንን የሚያህል የዛፍ ቅርንጫፍ ገንጥሎ፤ ያንን የበረዶ ክምር ለብቻው ያለ ማንም እርዳታ ደቅድቆ፤ ጓደኛውን እንዴት እንዳወጣው ግራ ገባቸው። ተዓምር ሆኖባቸው በጥያቄ “እንዴት አድርገህ?” እያሉ ያጣዳፉት ጀመር። ይሄኔ ከመካከላቸው አንድ አዛውንት እንዲህ ሲሉ ልጁን ወክለው መልስ ሰጡ።

“እኔ እነግራችኋለሁ፤ ይህ ወጣት ለጉልበተኛ ሰው  እንኳን የሚከብደውን ስራ ሊሰራ የቻለው፤ በአካባቢው ማንም “ተው አትችልም” የሚለው ሰው ስላልነበረ ነው፤ ብቻውን ስለሆነ፤ ሌላ ሚስጥር የለውም” አላቸው። አጋዥ ባይኖር እንኳን ተው የሚል አለመኖሩ እራሱን የቻለ ትልቅ እርዳታ ነው።

የዘሪቱን የቤተሰብ ሁኔታ አላውቅም። ለእኔ ግን ለጥያቄዋ የሰጠችው መልስ አይን ገላጭ መስሎ ታይቶኛል። እውነተኛ ድግፍንና ፍቅርን ደስ በሚል መልኩ ገልጻዋለች። አጠገባችን ያሉ ሰዎች “በመተው” ብቻ ብዙ እርዳታ ማድረግ እንደሚችሉ፤ እኛም ለሌሎችን “በመተው”ብቻ ብዙ እርዳታ ማድረግ እንደምንችል የሚያስታውስ ድንቅ ንግግር ነበር። የአና ፍራክን ያህል የዋህነት ባይኖረኝም፤ በሰዎች መልካምነት አምናለሁ። የምንቀርባቸው ሰዎች አውቀው ይጎዱናል ብዬ ማሰቡ ደስታን አይሰጠኝም። ከፍቅር የተነሳ እንቅፋት ሊሆኑ ግን ይችላሉ። እኛም ከፍቅር እና ከቅርበት የተነሳ እንቅፋት ልንሆን እንችላለን። ምክንያቱም ሰው እራሱን እንዲሆን መተው ከባድ ስለሆነ፤ ሰው በራሱ እቅድ እንዲመራ መተዉ ቀላል ስላይደለ። እኛ ሰውን  እንደምንፈልገው መለወጡ ስለሚያስደስተንና ትክክል ስለሚመስለን።

ቤተሰብንና ጓደኝነትን የሚያስተሳስረውና ይበልጥ እንዲያብብ ማዳበሪያ የሚሆነው “ነጻነት” ይመስለኛል። ሰው የሚወደውን እንዲሆን “መተው” ትልቅ እገዛ ነው። ሌስ ብራውን የተባለው ጸሃፊ እንዲህ ይላል “ሌሎችን ለመለወጥ አትሞክር፤ እራስን መለወጥ የሙሉ ሰዓት ስራ ነውና”። ሰዎችን እንደሆኑት መቀበል ለእኛ ለሰዎች ከባድ ስራ ነው። ምክንያቱም ሌሎችን ለመወደድና ለመቀበል እኛ እንደንፈልገው እንዲሆኑልን ስለምንፈልግ። ምንም እንኳን  ሰዎች እኛ እንደምንፈልጋቸው እንዲሆኑልን ብንፈልግም፤  ማንም ያለገዛ እራሱ ፈቃድ አይለወጥም። በእኛ ጉትጎታ ያ ሰው ቢለወጥ እንኳን አስመሰለ ወይም ተገደደ ነው እንጂ የሚባለው፤ እራሱን ሆነ ማለት አንችልም። በመተው ውስጥ ግን የሰውን እውነተኛ ማንነትና ባህሪ ማወቅ ይቻለናል…….ከምንም በላይ ግን ለሰዎች እውነተኛ ማንነታቸውን እንዲሆኑ መተው መቻላችን  ለእነሱ ትልቅ እገዛ ነው። ከማገዝ እኩል ትልቁ ድጋፍ መተው ነው ማለት ነው እንግዲህ!

 

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

2 Comments

  1. Tariku geremeq

    Am with u reading ur posts…
    እንደ መተው ያለ እገዛ በርግጥ የለም
    …..እኔም በመተው መተባበርን ጀምሬያለሁ…

    Reply
  2. Hirsi

    On the ebs tv. I seew that interview . Ehud meznaga

    Reply

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *