“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

ቀይ ለባሾቹ……

by | Feb 14, 2015 | Guest writer-እንግዳ ጸሃፍት | 0 comments

ዛሬ ከቢሮዬ አርፍጄ ነበር የወጣሁት ። በጠዋት መግባት ነው እንጂ ሊሳካልኝ ያልቻለው አምሽቶ መስራት ልምዴ ነው። ዛሬ ግን ብቻዬን አላመሸሁም ነበር ያለልምዷ ፀሃፊዬም አምሽታለች። ለወትሮ መውጫ ሰአቷን ለደቂቃ እንኳን አሳልፋ አታውቅም ከሰራተኛ ሁሉ ፈጥና የምትወጣው እሷ ናት ፣ የኋላ የኋላ ስሰማ ባል ተብየው ሁሌ ሰአቷን ጠብቆ በር ላይ እንደሚጠብቃት ሰማሁ። ዛሬ ግን አምሽታ ሳያት ተጣልተው መሰለኝ ። በዛ ላይ በጣም አምሮባታል…….ከላይ ያረገቻት ቀይ ቢጢሌ ቀያይ ጡቶቿን አንሳፈዋቸዋል…..ወንድ ልጅ መቼም እውር ካልሆነ በቀር ምንም አይነት ጠንካራ እና ግትር ቢሆን እንኳን አይኖቹን መግታት አይችልም ። ዛሬ ግን ለምን እንደሆነ ባለውቅም ተለየችብኝ አዘውትራ ነጭ ልብስ ስለምትለብስ ነው መሰለኝ ዛሬ ቀይልብስ አድርጋ ሳያት ልዩ ሆነችብኝ። ከስር ያረገችውም ቀይ መሆኑን ያቅኩት ከወንበሯ ተነስታ ስትቆም ነበር . የወገቧ ቅጥነት እና የዳሌዋ ስፋት ቀይ በቀይ ሆነው ልክ እንደ ኤድስ ሪቫን ተቆላልፈዋል.
ሰአቱ ይበልጥ እየመሸ ነው ። እኔ የራሴ ቢሮዬ ውስጥ ተቀምጫለው ….ቀጥሎ ካለው ቢሮ ፀሃፊዬ ብቻዋን ተቀምጣለች ….ስራ አንዳልስቆያት እርግጠኛ ነኝ…ከባሏ ብትጣላ ነው ያመሸችው ስል ገመትኩኝ…ደሞ ሴቶች ከባሎቻቸው ጋር ሲጣሉ ለምን መዘነጥ እንደሚወዱ አላውቅም በእነሱ ቤት ማስቀናታቸው ነው …..ፀሃፊዬም ዛሬ ባሏን ለማስቀናት ከመዘነጧ አልፎ ሌላ ቦታ እንዳመሸች አርጋ ባሏን ለማቃጠል ቢሮዋ ተቀምጣለች….ሃሳቤን ሰረቀችው…..ቢሮዬን አልፌ ቢሮዋ ስደርስ መስታወት ይዛ ፊቷን ስትመለከት አገኘኋት ሳታስበው ስለገባሁባት ደነገጠች….ፈገግ ስል እሷም የእፍረት የሚመስል ፈገግታ አሳየችኝ….ይመስለኛል ከመልኳ ጋር በእልህ እያወራች ነበር። አይ ሴት በመልካቸው ሲመኩ እኮ ….መልክ ለፈረስም አልጠቀማትም አለች አያቴ.

“ዛሬ ስራ በዛ እንዴ?” አልኳት ጠረንቤዛዋ ላይ እየተቀመጥኩኝ
“አይ ስራ እንኳን አልበዛም ትንሽ ማምሸት ፈልጌ ነው” አለችኝ ቀይ የተቀቡት ከንፈሮቿ የጥርሷን ንጣት አጉልተውታል …..ዛሬ ባጠቃላይ ቀይ ሆና ተውባለች
“በሰላም ነው ? ሌላ ቀን ከሁሉ ቀድመሽ የምትወጪው አንቺነሽ፣ እንደውም እንዳወጣጥሽ አገባብሽ ቢያምር ኖሮ እስካሁን የሁላችንም አለቃ በሆንሽ ነበር” ስላት ሳቀች ዛሬ ምንድን ነው? አሳሳቁዋ እንኳን ተለየብኝ ለነገሩ ከዚህ በፊት ብዙም ንግግር አልነበረንም …..ስለዚህ አስተውዬ አይቻት ስለማላውቅ ይሆናል.
“ማን ነው ያለው?”
“ሁሉም የቢሮ ሰው ያማሻል……ዛሬ ግን እኔም ገርሞኛል…ሁሌ ብቻዬን ስለማመሽ” አልኳት
“ሁሌ ለምን ታመሻለህ?”

“በጊዜ ቤት መግባት አልወድም በጊዜም መጠጥ ቤት መሄድም አልወድም….. ግዴታ ከሁለት አንዱ ጋር ነው የምሄደው ፣ ሁለቱም ደግሞ በጊዜ የሚኬድባቸው አይደሉም …….. የግድ ማምሸት አለብኝ”
ሳቀች እሷ ግን ዛሬ ያለወትሮዋ ለምን እንዳመሸች ጠየቅኳት መልሷን ለመስማት ጓጉቻለው ያቃጠላት ባሏን ለመበቀል እንደሆነ ስትነግረኝ በቃ አይዞሽ ትንሽ ዘና በይ ብዬ ይዣት ለመውጣት አሰብኩኝ…..እሾህን በሾህ አይደል።መለሷ ግን ለምን እንደሆነ አላውቅም አስደነገጠኝ
“ዛሬ እኮ ቫለንታይንስ ዴይ ነው……ከጓደኛዬ ጋር ማታ ነው ቀጠሮዋችን….ስለዚህ ቤት አምሽቼ ከምወጣ እዚሁ አምሽቼ ላግኘው ብዬ ነው” አለችኝ። ለካ የእኛ ሙሽሪት ቀይ በቀይ የተበሰው ለቫለንታይን ቀን መሆኑ ነው……ፀሃፍዬን ውጪ የማግኘት አላማው ኖሮኝ ባያውቅም ዛሬ ግን ሳላስበው …..የሆነ ነገር ተሰምቶኝ ነበር…..ለነገሩ ግልብ ስሜት እንደሆነ ጥርጥር የለኝም….ምክንያቱም ከዚህ በኋላ ለሴት የምሰጠው እንጥፍጣፊ ስሜት የለኝም.
ጠረንጴዛዋ ላይ እንደተቀመጥኩኝ ስልክ ተደወለላት
“ደረስክ ….በቃ መጣሁ…መጣሁ” ብላ ስልኩን ዘጋችው
“በቃ መሄዴ ነው …አንተ ብዙ ትቆያለህ?” አለችኝ
“አይ ……ትንሽ” አለኳት……ከሄደች በሁላ ቢሮዬ ገብቼ በመስኮት ተመለከትኳት……ቀዩዋ ሙሽራ አስፋልቱን ተሻግራ መኪና ውስጥ ስትገባ አየሁዋት……ተሳሳሙ

ዛሬ ቫለንታይን ቀን ነው ማለት ነው?…..አልኩኝ አይምሮዬ ፍቅር ነክ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ እየረሳ መጥታል….ከመስኮቱ ሳልንቀሳቀስ….ሁለት ጥንዶች የአስፓልቱን ጠርዝ ይዘው ሲጓዙ ተመለከትኳቸው….ሴቲቱ ቀይ ለብሳለች……..አሃ ቫለንታይን!!!

ብዙም ሳልቆይ ቢሮዬን ለቅቄ ወጣሁኝ……ሀሳቤ ሲናወጥ ተሰማኝ…..የቀበርኩትን ጉድ ሁሉ ቀይ ለባሾቹ ቆፈሩብኝ….ህመም ለቀቁብኝ…..ወደማዘወትረው መጠጥ ቤት ስደርስ……ሁሉ ተለዋውጦ ጠበቀኝ
በየጠረቤዛው ቀያይ አበቦች ተቀምጠዋል…ጥንዶች ይበዛሉ….ቤቱ አንደሌላው ጊዜ ሞቅ ሞቅ ያለ ሙዚቃ አልተከፈተበትም….ቀዝቃዛ ዘፈኖች….ይከታተላሉ….ቢራዬን አዘዤ ዙሪያዬን ማስተዋል ጀመርኩኝ……ብዙ ቀይ ለባሾች ቤቱን ሞልተዋል…..ጥንዶቹ ሁሉ እንደድራማ ሰሪ እንቅስቃሴያቸው በጥንቃቄ ነበር…..እጆቻቸውን ሲያቆላልፉ…መልሰው ሲላቀቁ….ስደባበሱ…ሲነጋገሩ …..እየተጠባበቁ ሲሳሳቁ….ሳቄ መጣ….እነባዬም ሳቄን ተከትሎ መጣ…ቀይ ለባሾቹ ዛሬ ቁስሌን ቀሰቀሱብኝ….ቀይ ነገር ጠላሁኝ ….ቀይ ሽብር ሁሉ ትዝ አለኝ…ለእኔ ሃዘኑ የዛን ያህል ነውና.

ሳልፈልግ በግድ ሰብለን አስታወስኳት……ገንዤ ከቀበርኩበት በግድ ቆፍሬ አወጣሁዋት……..በፍርድ ቀን ማስታወስ ሲገባኝ በፍቅር ቀን አስታወስኳት…….ሰው ሁለቴ ሶስቴ አፈቀርኩኝ ሲል ይገርመኛል…..ልብ እንዴት ከአንድ ጊዜ ባለይ ለሰው ይሰጣል? እየተቆራረሰ? እየተሸራረፈ? እንዴት ሁለቴ ይፈቀራል…..የሌላውን ባላውቅም እኔን ግን አቅቶኛል…..ከድታኝ ለሄደችው ልቤን ሰጥቻለው….መልሼ ስላልተቀበልኳት…ከዚህ በሁዋላ የምሰጠው ምንም የለኝም.
መጠጥ ቤቱ እየቆየ በቀይ ለባሾች ሞላ……ዘፈኑ እየቀዘቀዘ በሄደ ቁጥር ከኔ በቀር ሁሉም በትዝታ እና በፍቅር ይግላል….እኔ ግን በረዶ እየሆንኩ ስመጣ ተሰማኝ…በላይ በላዩ የምጨልጠው ቢራ ግን እየቆየ ያቀልጠኝ ጀመር.
እንደ ፍቅር እራስን ከፍ የሚያደርጉበት ነገር የለም…..ሁሉም ሰው ሲያፈቅር እንደሱ ማንም ያፈቀረ አይመስለውም…እንደሱ ስለፍቅር የተጎዳ…ስለፍቅር ብዙ ብዙ ነገር የሆነ ማንም እንደሌለ በርግጠኝነት ይወራረዳል….እኔም እኔ ሰብለን እንዳፈቀርኳት…እኔ ስለፍቅር ሁን የተባልኩትን እንደሆንኩት ማንም የለም ብዬ እወዳደራለው…ከፊቴ ያሉትም ሁሉም ቢጠየቁ ይሄኔ እንደነሱ ያፈቀረ ያለ አይመስላቸውም ። አይምሮዬ ሲደማ ተሰማኝ….እንደ ቀይ ለባሾቹ….ቫለንታይንን በቀይ ለማክበር ተገደድኩኝ ቀይ ለብሼ ሳይሆን አልቅሼ…አይኖቼን አቅልቼ……የበይ ተመልካች ሆኜ….ዙራዬን ከከበቡኝ ቀይለባሽ ውቦች ጋር….ብቻዬን ተከዝኩኝ…..ሰብለም ይሄኔ ከባለተረኛው ጋር ቀይ ለብሳ ቫለንታይንን እያከበረች ይሆናል……እሷ ምን አልባት የምትሰጠው ልብ ይኖራታል ፣ ምክንያቱም……ከኔ ጋር እያለች ለኔ አልሰጠችኝም…..አላፈቀረችኝም……ስለዚህ የማፍቀር እድሉ አላት…..እኔ ግን እሷን ብቻ አፍቅሬአለው በቃኝ!

ልክ ነው ሃዘንም እንደ ደም ቀይ ነው….ፍቅርም እንደ ፅጌሬዳ ቀይ ነው….ሁለቱም በቀይ ይከበራሉ…..በቀይ ይመሰላሉ
ሞቅ ሳይለኝ አይቀርም…… አስተናጋጁ ቢራ ሊጨምርልኝ መጣ…..ጠርሙሱ እየከፈተ ፈገግ ሲል….ቀይ ድዱ ፍንትው ብሎ ታየኝ…..ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ አይቼው ባውቅም ቀይ ድዱን አስተውዬው አላውቅም. ከት ብዬ ሳቅኩኝ
“ወገኛ አንተም እንደ ቀይ ለባሾቹ…….ቫለንታየንን በቀይ ማክበርህ ነው?” ብዬ ለብቻዬ ሳቅኩኝ…..አስተናጋጁ ይከፋብኝ አይከፋብኝ አላውቅም። ሌሊቱ እየነጋ ነው…..ሰው ሁሉ ተደስቷል እኔ ግን ሳልሰክር አልቀርም ……ቫለንታየንን እንደ ጉድ አከበርነው አልኩኝ…..ዝሆኗ እና ጉንዳኗን አሰብኳቸው
ዝሆንን እና ጉንዳን ድልድይ ሲሻገሩ ድልድዩ ይነቃነቃል አሉ….ከዛ ጉንዳኗ “ነቀነቅነው” አለች አሉ። እንደምንም……ግን አከበርናት….እስኪነጋ ጨፈርን ….አለቀሰን….ተከዘን…አይ ቫለንታይን….እንደ ለቅሶ በጥቁር መከበር የነበረበትን በአል በቀይ አጨማለቁት!!!!ቀይ ለባሾቹ…

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *