“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

ስረ መሰረታችን መልካም ነበር…

by | Jun 7, 2015 | Guest writer-እንግዳ ጸሃፍት | 0 comments

እያንዳንዳችን ያለፍንበትን የህይወት መንገድ ወይም ያለንበትን ሁኔታ ከራሳችን በቀር የሚረዳን እንደሌለ ሁሉ፤ ሌሎችም የውስጣቸውን ከራሳቸው በቀር የሚያውቅላቸው የለም። ሰዎች ሁሉ በተፈጥሯቸው መልካም ናቸው። የህጻን ልጅ ክፉ፤ ወይም በቀለኛ ታይቶ አይታውቅምና። አና ፍራንክሊንን ብዙዎቻችን እናውቃታለን፤ በግፈኛው የናዚ ዘመን ለህሊና የሚከብድ በደል ሰው በሰው ላይ ሲፈጽም እያየች “የሰው ልጆች ሁሉ ከስረ መሰረታቸው ጥሩዎች ናቸው ብዬ አምናለው” ያለችው፤ በዙሪያዋ የሚከናወነው ግፍ አልታያት ብሎ አልነበረም። ይልቁንም የሰው ልጅን ማንነት፤ ከስረ መሰረቱ ለማየት ያልተበረዘው የልጅነት አይምሮዋ ስለፈቀደላት እንጂ።

ማንም ሰው ወዶ ክፉ አይሆንም፤ ይህንን ስል ክፋት በምክንያት የሚደገፍ ተቀባይነት ያለው ነገር ነው እያልኩኝ አይደለም። ነገር ግን ክፉ ሆኖ የተወለደ ከሌለ፤ ሰው መልካም ማንነቱን የቱ ጋር ጣለው? ያሰኛል። መልሱ በህይወታችን የሚያጋጥሙን ውጣ ውረዶች ወይም የለተያዩ  የህይወት አጋጣሚዎች ማንነታችን እንዲገንቡት ስለምንፈቅድ፤ መጥፎ አጋጣሚዎቻችን ጠባሳቸውን ጥለውብን ያልፋሉ።ከልጅነት ወደ አዋቂነት ስንሸጋገር፤ በአዋቂነት ውስጥ የተደበቀ ትልቅ አላዋቂነት ውስጥ ገባን።

የችግራችን መሰረቱ እራሳችንን ከሰው መንጋ ለይተን ለማየት ስለምንሞክር ነው። ነብር ነብርን አይቶ አይደነብርም፤ ምክንያቱም ነብርነቱን በሌላው ነብር ውስጥ ስለሚመለከት። እኛ ግን እራሳችንን በሌላው ውስጥ መመልከት አንችልም፤ ለዚህ ነው ሰው በሰው ላይ በደል ሲፈጽም እንግዳ የማይሆነው። ነገር ግን እያንዳንዳችን እራሳችንን በሌላው ሰው ውስጥ መመልከት ብንችል፤ በኛ ላይ እንዲፈጸም የማንሻውን ነገር እንዴት ጨክነን በሌላው ላይ እናደርግ ነበር? ወፎች አብረው ለመብረር ግዴታ መዛመድ የለባቸውም፤ እያንዳንዳቸው እራሳቸውን በሌላው ውስጥ ስለሚመለከቱ እርስ በርሳቸው አይተናኮሉም። ሰማዩ ጠበበን ብለው አይገፋፉም፤ ጸጥ ብለው ይበራሉ….

ምንም እንኳን ህይወት ብዙ አረም ብትዘራብንም ፤እውነተኛው እና መልካሙ ማንነታችን ሁሌም በውስጣችን አለ፤ ፈጣሪ በአምሳሉ እስከፈጠረን ድረስ እስከመጨራሻው ገንጥለን ልንጥለው አንችልም። ለዚህ ነው እኮ አንድ ሰው ምንም ያህል ክፉ እና ጨካኝ ሆኖ ቢያድግም፤ በውስጡ ትንሽም ቢሆን እርህራሄ የማይጠፋው።

እያንዳንዳችን አለምን ለመለወጥ የሚያስችል አቅም ባይኖረንም፤ እራሳችንን በሌላው ሰው ውስጥ መመልከትን ልምድ ካደረግን ቢያንስ ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት በእጅጉ ይለወጣል። ሰዎች ቢበድሉን እንኳን፤ ከስረ መሰረታቸው መልካም መሆናቸውን ስናስታወስ፤ መልካም ያልሆነው ባህሪያቸው፤ ባለፉበት የህይወት መስመር የተጫነባቸው አጉል ሸክም እንደሆነ እንረዳለን። ስለዚህ ሸክማቸውን በበቀል ለመጣል አንጥርም፤ ምክንያቱም እራሳችንን በነሱ ውስጥ ማየት ስለቻልን። ሁሉም ሰው በውስጡ መልካም ማንነት አለው፤ ያንዳንዶቻችን ማንነት ላይ ግን ብዙ አረሞች በቅለውበታል፤ ፈልገን ሳይሆን በየአጋጣሚው የተዘሩብን አጉል የህይወት አጋጣሚዎች። እንጂ ማናችን ወደን መጥፎ ሆንን?

እርስ በርሳችን አንፈራረድ፤ የሚያለያየን ያለፍንበት የህይወት ጎዳና ነው እንጂ፤ በተፈጥሯችን አንድ ነን፤ መልካም የፈጣሪ ፍጡሮች። ከላይ በምናየው ነገር ከተገማገምን ግን ማንም የማንንም መልካምነት ማየት አይቻለውም። በመጨረሻ አንድ ነገር ብዬ ጽሁፌን ላብቃ፤ እራሳችንን በሌላው ውስጥ መመልከቱን ልምድ እናድርግ። ያኔ የሌላው ሰው ቁስል፤ የሌላው ሰው ሃዘን፤ የሌላው ሰው ደስታ፤ የሌላው ሰው ስሜት በቀላሉ ስለሚገባን፤ አንድ ላይ እንደ ወፍ በነጻነት እንበራለን። ሁላችንም ከስረ መሰረታችን ጥሩዎች ነንና!!!

 

 

 

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *