“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

ምናልባት….ምናልባት…..

by | Dec 2, 2017 | Guest writer-እንግዳ ጸሃፍት | 0 comments

(በሚስጥረ አደራው)

ቁርሴን ከረፈደ ስለበላሁኝ፤ የምሳ ሰዓቴን ለእረፍት ልጠቀምበት አሰብኩኝና፤ ከመስራ ቤቴ ፊት ለፊት ወዳለው መናፈሻ ሄድኩኝ። አግድም አግድም ከተዘረጉት ወንበሮች ወደ አንደኛው እየተጓዝኩኝ ሳለ፤ከሳሩ መካከል የቀደበቀች የወረቀት ቁራጭ አይኔን ሳበችኝ። በእጅ ጽሁፍ ከተጻፈ ደብዳቤ ላይ ተቀዳ የቀረች የወረቀት ቅዳጅ ናት። የወደቀ ወረቀት የማንሳት ልምድ ባይኖረኝም የሆነ ስሜት ይህቺን የወረቀት ቅዳጅ እንዳነሳት አስገደደኝ። አነሳኋት “እኔ ግን በቅቶኛል” የሚል መዝጋያ የሚመስሉ ቃላቶች ብቻ ነበሩ በወረቀቱ ቅዳጅ ላይ የቀሩት። ሲመስለኝ ደብዳቤውን የጻፈው ሰው ሃሳቡን ቀይሮ  አላያም ደብዳቤውን የተቀበለው ሰው ደብሮት በጫጭቆ ጥሎት መሆን አለበት።

ብጫቂ ወረቀቷን አንስቼ አግዳሚው ወንበር ላይ ተቀምጬ ማሰላሰል ጀመርኩኝ። ምን አይነት ሰው ሊሆን ይችላል? ወጣት? ሽማግሌ? ህጻን? ሴት? ወንድ? በህሊናዬ የዚህ ደብዳቤ ባለቤት ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ የማስባቸውን ማውጣት ማውረድ ጀመርኩኝ።

ቆይ ወጣት ከሆነ “እኔ ግን በቅቶኛል” ሲል ምኑን ይሆን? ምናልባት ለሚወዳት ልጅ ቢሆንስ የጻፈው፤ እሷን መለማመጥ ሰልችቶት? መልስ አለመስጠቷ አናዶት?ወይስ የምትፈጽምበት ክህደት በቅቶት? ወይስ የገዛ የህልም እሩጫው አስልችቶት። ወዲያው አይምሮዬ ሴት ብትሆንስ? ሲል ጠየቀኝ። እምም……. ምናልባት የባሏ በደል ይሆን የበቃት? ወይስ አንድ ቀን አገባሻለው እያለ የሚሰጣት የማያልቅ ቀነ ቀጥሮ? ወይስ የአማቷ ጭቅጭቅ? ወይስ ልጅ ለመውለድ የምታደርገው ትግል? ወይስ የአረብ አገር ኑሮዋ? ወይስ …..

ብዙም በሃሳቤ ሳልዘልቅ የሆኑ ሽማግሌ አዛውንት በህሊናዬ መጡ። እሳቸውስ ቢሆን የጻፉት? ምኑ ይሆን የሚበቃቸው? የአልጋ ቁራኛ ያደረጋቸው ህመም? ወይስ የልጃቸው ናፍቆት? ወይስ የነበራቸውን ክብርና ሃብት ተነጥቀው ተራ ሆነው መታየቱ ነው የበቃቸው? ወይስ እየተቆራረጠ የሚሰጣቸው ከስድብ የማያንስ የጡረታ ገንዘብ?  ወዲያው አንዲት አሮጊት ቀስ እያሉ ከመላምት መንደሬ ገቡ። እሳቸው ከሆኑ የዚህ ደብዳቤ ጸሃፊ፤ ምን ይሆን “እኔ ግን በቅቶኛል” ያሰኛቸው? በመጦሪያቸው ጊዜ የልጅ ልጅ ማሳደጋቸው? አውሬ ሆኖ ነክሶ የያዛቸው የኑሮ ውድነት? ወይስ የወላድ መካን እንዲሆኑ ያስገደዳቸው ስደት? ወይስ የራሳቸውን ጎጆ ለማቅናት ሲሉ የረሷቸው የልጆቻቸው ናፍቆት? ወይስ አልታበስ ያላቸው እንባ እና አልሰማ ያላቸው ጸሎት? ምኑ ይሆን የበቃቸው?

የመላምት መንደሬ በሰዎች ተጨናነቀ…….

አንድ ህጻን ቢሆንስ ግን ይህንን ደብዳቤ የጻፈው? በዚህ እድሜው “እኔ ግን በቅቶኛል” ያሰኘው ምን ይሆን? ቀንና ማታ የሚሰማው የወላጆቹ ጭቅጭቅ? ዞር ብሎ ያላው የአባቱ ናፍቆት?  ከሃብታም ልጆች ጋር እየተማረ እኩል ባለመሆኑ የሚደረሰበት መሸማቀቅ ይሆን የበቃው? ወይስ በባዶ ሆዱ ትምህርት ቤት መሄዱ?  ወዲያው ደግሞ የእሱ እኩያ የሆነች ህጻን ልጅ በህሊናዬ ታየችኝ። እሷስ ጽፋው ቢሆን? በእንጀራ እናቷ የሚደርስባት በደል ይሆን የበቃት? በሴትነቷ የደረሰባትን በደል መደበቁ ይሆን የበቃት? አባቷ እናቷን በነጻነት መደብደቡ ይሆን የበቃት? ያለ እድሜዋ የሰው ገረድ መሆኑ ይሆን የበቃት? ከትምህርት መልስ የሚጠብቃት ስራ ይሆን የበቃት? ምኑ ይሆን እኒህን ህጻናት “እኔ ግን በቅቶኛል” የሚያሰኛቸው?

አንዲት የቤት ሰራተኛ ደግሞ ቀስ እያለች ወደ ምናልባት መንደሬ ዘለቀች…… “እኔ ግን በቅቶኛል” ያስባላት ብዙ ነገር ሳይኖራት አይቀርም። ያለደሞዝ የሚደርስባት ብዝበዛ? የአሰሪዋ ጥፊ? የዘበኛው ትንኮሳ? ዛሬ ነገ ትማሪያለሽ የሚለው ሽንገላ? ያለ ጥፋቷ የሚደርስባት ክስ? ሰዓት እና ገደብ የሌለው የማያልቀው ስራ? ምኑ ይሆን በዚህ ደብዳቤ “እኔ ግን በቅቶኛል” ያሰኛት? በመላምት መንደሬ የተመላለሱት በሙሉ “እኔ ግን በቅቶኛል” ሊያሰኛቸው የሚችል ብዙ ምክንያቶች እንዳላቸው ተረዳሁኝ።

አይምሮዬ ሊፈንዳ ደርሰ፤ ብዙ ምናልባቶች በዚህች ብጫቂ ወረቀት ውስጥ ታዩኝ። በደብዳቤው ቀዳዳ አሾልኬ ብዙ ነፍሶችን ዳሰስኩኝ። ያድክማል፤ እውነት……. ከእርግጠኝነት መራቅ ሲበዛ ያደክማል። ምናልባትም በመሰለኝ የምናደርገው ውሳኔ ልክ እኔ ይህችን ብጫቂ የደብዳቤ ቅዳጅ ይዜ ሙሉ ታሪኩን ለመተረክ እንደማደርገው ሙከራ  ሳይቆጠር አይቀርም። ይህንን እያሰብኩኝ ፈገግ አልኩኝ፤ ሰለሞንን ልጣላው ውስኜ የነበረው በዚሁ የሃሳብ ቁራጭ ላይ ተንተርሼ ነበር። በተቀጣርንበት ጊዜ እና ቦታ ስላልተገኘ፤ ብሎም ስልኩን ስላልመለሰ አኩርፌው ነበር ። ምክንያቱን እንዲያስረዳ እንኳን እድል ሳልሰጠው ቀረሁኝ።

የደብዳቤዋን ቁራጭ እንደያዝኩኝ፤ ምናልባት ሰለሞን በቀጠሮው ያልመጣው የሆነ ችግር ገጥሞት ሊሆን ይችላል ብዬ ማሰላሰሌን ተያያዝኩት። ምናልባት አሞት? ምናልባት የሚያስታምማት አክስቱ ብሶባት? ምናልባት ያ ጨቅጫቃ አለቃው ስራ አዞት? ምናልባት ስልኩ ተሰርቆ? ምናልባት በጎን የጀመረው የግል ስራው አላፈናፍን ብሎት……ይህ ሁሉ ነገር እያለ አንዲት መላምት ይዤ ለጥል መንደርደሬ አሳፈረኝ። እውነተኛውን ታሪክ መስማት ከብዙ ስህተቶች ያድናል። የዚህችን ቁራጭ ደብዳቤ ቀሪውን ባገኝ በመላምት ከማበድ ያድነኝ አልነበር?

ቁራጯን ወረቀት በኪሴ ከትቼ ወደ ቢሮዬ ተመለስኩኝ…….ከብዙ ስህተቶች የምታድነኝ ወሳኝ መመሪያ ትሆነኛለች። በግምት ላይ ተቁሞ እንደሚወሰን ውሳኔ ምን ስህተት አለ? የሚያስቀው ደግሞ አባዛኛዎቹ አይምሮዋችንን የሚያጣብቡት ነገሮች ግምቶች ናቸው። በቀዳዳ እያጮለቅን የምናያቸው ሙሉ ያልሆኑ እውነታዎች! ቁራጭ ሃሳብ ይዘን የምንተርካቸው ታሪኮች!!! አይ የምናልባት መንደር!

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *