“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

መፍትሄ አለኝ

by | Apr 26, 2015 | Guest writer-እንግዳ ጸሃፍት | 0 comments

አዎ መፍትሄ አለኝ፤ መፍትሄው ግን ችግራችንን ባቋራጭ የሚፈታ ሳይሆን፤ በረጅም ጊዜ ጨርሶ የሚያስወግድ ነው። እናንተዬ ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሄውን ቤታችን አስቀምጠን፤ መፍትሄ ፍለጋ እስከመቼ እንንከራተታለን? ለጥያቄዎቻችን ሁሉ መልሱ እያንዳንዳችን አይምሮ ውስጥ ሆኖ ሳለ እስከመቼ  መልስ ፍለጋ የሌላው መንጋጋ ስር እናንጋጥጣለን?

አዎ መፍትሄ አለኝ፤ ይህን መፍትሄ አስቤ ፤ አውጥቼ አውርጄ፤ ጋራ ቧጥጬ፤ በረሃ አቋርጬ፤ ለፍቼ  ያገኘሁት መፍትሄ አይደለም። እኔ ብቻ የማውቀው፤ ለሰው የተሰውረ፤ የአይንስታይንን ጭንቅላት የሚጠይቅም አይደለም። እርግጠኛ ነኝ ፤ መፍትሄ ያልኩትን ስትሰሙ፤ የማን ቀሽም ናት የምትሉኝ እንዳላችሁም አምናለው። ግን እኔ ነኝ ትክክል፤ እናም ካልተስማማችሁ፤ የዋህነቴ ካልጣማችሁ፤ ስህተቱ የኔ አይደለም።

መጀመሪያ ከጥያቄዎቻችን ልጀምር፤ ለምን  ዱላ ከየአቅጣጫው በዛበን ? ለምን ከቀን ወደ ቀን ቁልቁል ወደታች ወረድን? ለምን ሃዘናችን በዛ? ለምን የሃብታሙ እና የድሃው ልዩነት የሰማይ እና የምድር ያህል እረቀት ኖረው? ለምን እናቶች የወላድ መካን ሆኑ? ለምን ወጥተን መመለስ አቃተን? ለምን የሁላችንም ጉልበት ደከመ? ለምን ልዩነታችን ሰፋ? ለምን እድገት ህልም ሆነብን? ለምን ጠግበው ከሚያድሩ ሆዶች ይልቅ፤ ተርበው የሚያድሩ ሆዶች በዙ? ለምን እስኪብርቶ ከጨበጡ ህጻናቶች ይልቅ፤ ሊስትሮ ህጻናት በረከቱ? …….ለመሆኑ ጥያቄዎቻችንስ ማብቂያ አላቸው? አይመስለኝም። እኔ የማነሳው የፖለቲካ ጥያቄዎችን ሳይሆን የሰብዓዊነት ጥያቄዎችን ነው። እኔ የግሌን ብናገር ከምንም በላይ ሰው መሆንን ቅድሚያ እሰጠዋለው።

ሆኖም ግን ለዚህ ሁሉ ችግር እና ጥያቄዏቻችን መፍትሄው አንድ እና አንድ ነው፤ “ፍቅር”። የኛ ብቻም ሳይሆን የአለም ሁሉ ችግር መንስኤው የፍቅር ማነስ ነው። እኛ ኢትዪጵያዊያኖች የአለም ሁሉ ዱላ የበረታብን፤ ፍቅር ስለጎደለን ነው። አለቅጥ በቀጫጭኑ ተሰነጣጥቀን፤ አንድነት ስለጎደለን ማንም እየገነጠለ ይጥለናል። “በውጪ ካለ ጠላት ይልቅ፤ በውስጥ ያለ ጠላት በእጅጉ ይበረታል” የሚል የአፍሪካዊያን አባባል አለ። የኛም እውነታ ከዚህ አይርቅም፤ የራሳችን ትልቁ ጠላት እራሳችን ነን፨

አሁንም የዋህነቴ ካልተዋጠላችሁ ይቅርታ፤ እኔ ግን የማንነው ማናችንም ብንሆን፤ ኢትዮጵያ አሁን ለገጠማት ችግር ተጠያቂ ነን። አንዳችንም ብንሆን እንደ ጲላጦስ እጃችንን ታጥበን ንጽህናችን ለማስመስከር አንችልም። ፍቅር የለንም፤ እራስ ወዳድነት ተጠናውቶናል፤ እኔ ብቻ ልበልጽግ፤ እኔ ብቻ ሆዴን ልሙላ ስንል፤ ተያይዘን ማለቃችን ነው። ለሃገራችን እኮ፤ በእኛ በእያንዳንዳችን  ኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ትንሽ ፍቅር ቢያድር ፤ ቢያንስ ጥቂት ሰዎች በልተው አያድሩም? ቢያንስ ጥቂት ህጻናት ትምህርት አያገኙም? ቢያንስ ጥቂት አዛውንቶች ጎናቸውን አያሳርፉም? አስተዋጽዎ እኮ ትልቅ እና አለም ሁሉ የሚያየው መሆን የለበትም። እያንዳንዳችን ሌላውን ለመርዳት  የሚያስፈልገን ገንዘብ እና እውቀት ሳይሆን መጀመሪያ ፍቅር ነው።

ነጋዴው የኔ ብቻ ኪስ ይዳብር ባይል፤ መምህሩ ከተማውን ብቻ ላበልጽግ ባይል፤ የመንግስት ሰራተኛው እኔ ብቻ ሆዴን ልሙላ ባይል፤ ሃኪሙ ሃብታሙን ብቻ ላድን ባይል፤ ፖለቲከኛው እኔ በቻ ልንገስ ባይል፤ ወጣቱ እኔ በቻ ልንቃ ባይል፤ እያንዳንዳችን ለአንድ ተጨማሪ ሰው ብናስብ እና ትንሽ ፍቅር ቢያድርብን፤ ለውጥ አይኖርም ትላላችሁ? እስቲ ዛሬ እራሳችንን አንድ ጥያቄ እንጠይቅ “እኔ ለሃገሬ ምን አደረግኩላት?” እንበል። ሃገር ማለት ህዝብ ነው ብሏል እና ጸሃፊው ፤ “እኔ ለህዝቤ ምን አደረግኩለት?” ብለን እራሳችንን እንመርምር።

አባቶቻችንን፤ እናቶቻችን፤ወንድሞቻንን ፤እህቶቻችንን፤ በረሃብ እየተቆሉ፤ በበረሃ እያለቁ፤ በድህነት እየተሸማቀቁ፤ በዘር መጣላታችን፤ በፖለቲካ ጀርባ መሰጣጠታችን፤  ምን ይባላል?  እንኳን ኢትዮጵያዊነትን ያህል የሚያስተሳስረን ነገር ኖሮን ይቅርና  አንድ ለመሆን ሰው መሆናችን ብቻ በቂ አልነበረምን? ወገናችን እኮ በወገኑ ተስፋ አጥቷል፤ ሆዳችን ለመሙላት የምናንጋጥጠው እኮ ወደ ወገናችን ሳይሆን ወደ ባዕዱ ነው፤ ለምን?

የችግራችን ሁሉ መንስዔዎቹም መፍትሄዎቹም እኛ ነን። ኸረ እራሳችንን መበደል ይበቃናል፤ ወገን የወገኑን ደም መጠጣት ይብቃው። ሙስና ማለት ከደሃ መንጋጋ ምግብ መንጠቅ መሆኑን ብዙዏቻችን አናውቅም፤ ትክክለኛው ሃገር ወዳድነት ኢትዮጵያን ማስቀደም መሆኑ አብዛኛዎቻችንን አልገባንም። ሆዳም፤ እራስ ወዳድ፤ ዘረኛ ትውልድ እዚህ ላይ ይብቃ። ለሁሉም መፍትሄው ፍቅር ነው፤ እራሳችንን እንውደድ፤ ቤተሰባችንን፤ ወገናችንን፤ ሃገራችንን እንውደድ፤ ከምንም በላይ ፈጣሪያችንን እንውደድ። ሰው በሚወደው ነገር ይደራደራል እንዴ?…….በፍጹም። እናም መፍትሄ ያልኩት ፍቅርን ነው። ስግብግብ ካልሆንን ያለን በቂ ባይሆንም መበርከት ይችላል። ምንም አልባት ሃገር በእንዲህ አይነት የዋህነት አትመራም የሚሉ ይኖራሉ፤ ግን ከፍቅር እና ከአንድነት በላይ መፍትሄ ያለው ካለ ይቅረብ።

እናም ፈጣሪ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ፍቅርን ይዝራ፤ የሁሉም ነገር መፍትሄው ፍቅር ነውና። እያንዳንዳችን  የኢትዮጵያ ችግር እና መከራ ውስጥ እጃችን አለ። እንደ ጲላጦስ እጁን መታጠብ የሚችል ማንም ኢትዪጵያዊ የለም። በመጨረሻ አንድ እውነት ልናገር፤ አሁን ጽሁፌን ሳጠናቅቅ እራሴን “ለሃገሬ ፤ ለህዝቤ ምን አደረግኩለት?” ብዬ ጠየቅኩኝ። ምላሽ አጣው……አንደበቴ ተሳሰር….

 

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *