“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

መጀመሪያ ቃል ነበረ……

by | Nov 7, 2016 | መነቃቂያ inspiring stories | 0 comments

“መጀመሪያ ቃል ነበረ….” ይላል ቅዱሱ መጽሃፍ። ቃል ትልቅ ሀይል እና ጉልበት ያለው ነገር መሆኑን ይህ ጥቅስ ያስረዳል። ይህ አባባል ከሀይማኖታዊ ትርጓሜው በዘለለ በእለት ተእለት ኑሮዋችንም ትልቅ ጉልበት ያለው መልዕክት ነው። በቃል መልካምም መጥፎም ነገሮች በኑሮዋችን ውስጥ ህይወት ይዘራሉ።

እውን ሆነው በአይናችን የምናያቸው ነገሮች ሁሉም ሁለቴ የተፈጠሩ ናቸው። በመጀመሪያ በአይምሮዋችን ይሳላሉ ሁለተኛ በእውን ይፈጠራሉ። በአይምሮዋችን የምናስባቸውን ነገሮች በቃል ስንናገራቸው ያኔ እውን ለመሆን ይዘጋጃሉ።ለዚህ ነው ቃል ትልቅ ጉልበት የሚኖረው። በዚህች አለም ላይ ሰላም የሚመጣውም ሆነ የሚደፈርሰው መጀመሪያ በቃል ነው። የሀገራችን ሰዎች “ከአፍ የወጣ ቃል  ከእጅ የወደቀ እንቁላል” እያሉ የሚተርቱት አሁንም የቃል ጉልበት ሲያንጸባርቁ ነው።

አዘውትረን የምንናገራቸው ቃላቶች አስተሳሰባችንን ያሳብቃሉ። አስተሳሰባችንንም ብቻ ሳይሆን ኑሮዋችንንም ይናገራሉ። የተለያዩ የስነ ልቦና ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት፤አስተሳሰብቻንም ብቻ ሳይሆን ከአንደበታችን የሚወጡቱም ቃላቶች ህይወታችንን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አላቸው። በኑሮዋቸው ደስተኛ ያልሆኑ ሰዎች አዘውትረው የሚጠቀሟቸው ቃላቶችና በኑሮዋቸው ደስተኛ የሆኑ ሰዎች የሚጠቀሟቸው ቃላቶች እጅግ የተለያዩ ናቸው። ህይወታቸው የተሳካላቸው ሰዎችና ያልተሳካልቸውም እንዲሁ የሚያወሩት የተለያየ ቋንቋ የሚጠቀሟቸውም የተለያዩ ቃላቶችን ነው።ታዲያ የሁለቱንም ኑሮ አስተውለን ስናይ እያንዳንዳቸው አስተሳሰባቸው፤ ከአንደበታቸው የሚወጡት ቃላቶች እንድሁም ኑሮዋቸው እርስ በእራሳቸው ይጣጣማሉ።

አንዳንዴ “ተመስገንን” የሚያበዙ ሰዎች አጋጥመዋችሁ አያውቅም? እንደዚህ አይነት ሰዎች አዘውትረው “ተመስገን” የሚሉት ኑሮዋቸው ሙሉ በሙሉ የተሳካ ሆኖ ምንም ነገር ሳይፈልጉ ቀርተው ሳይሆን። ከአንደበታቸው የሚወጣው ቃል፤ ያላቸውን እንደሚባርክላቸው የሌላቸውንም እንደሚያመጣላቸው ስለሚያምኑ ነው። “ላለው ሁሉ ይሰጠዋል ይበዛለትማል……ከሌለው ግን ያው ያለውም እንኳን ይወሰድበታል” እንደሚለው ቅዱሱ መጽሀፍ።

ይህንን አባባል ደጋግሜ ብሰማውም ትርጉሙ እሰከ ቅርብ ጊዜ እምብዛም አይገባኝም ነበር፤ Rhonda Byrne የተባለችው ጸሃፊ ግን አባባሉ በህይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲኖረው አድርጋዋለች። ይህች አውስትራሊያዊት ፀሃፊ በ2012 ያሳተመችው “The Magic” በተሰኘው መፅሃፏ ደግሞ አንድ ቃል የህይወትን ትርጉም ምን ያህል እንደሚለውጥ ድንቅ በሆነ ሁኔታ ለማስረዳት ሞክራለች።

“ላለው ሁሉ ይሰጥዋል ይበዛለትማል……ከሌለው ግን ያው ያለውም እንኳን ይወሰድበታል”የሚለው ቃል መፅሃፍ ቅዱሳዊ ቃል ነው። እንደው በግልብ ከተመለከትነው ትርጉሙ “ ያለው ካለው ላይ እየተጨመረለት ሃብታም እየሆነ ይሄዳል….የሌለው ደግሞ ካለው ላይ እየተቀነሰበት ይበልጥ ወደ ድህነት አዘቅት ውስጥ ይገባል” የሚል ትርጉም ያዘለ ይመስላል። ፀሃፊዋ ግን በዚህ ሚስጥራዊ አባባል ውስጥ አንድ ቃል ተደብቋል ትላለች ይህም “ምስጋና” ነው።እስቲ “ምስጋና” የሚለውን ቃል በዓረፍተ ነገሩ ጨምረን እንደገና እናንብበው

“ “ምስጋና” ላለው ሁሉ ይሰጠዋል ይበዛለትማል….”ምስጋና” ለሌለው ግን ያው ያለውም እንኳን ይወሰድበታል” የሚል ትርጉም ይሰጠናል። አንዲት ቃል ምን ያህል የትርጉም ለውጥ እንደምታመጣ በዚህ መመልከት እንችላለን።

እንግዲህ የቃልን ሀይል ከተረዳን ከአፋችን የሚወጡትን ቃላቶች ማስተዋል አለብን። ሁሌም የምናማርር ከሆነ በእርግጠኝነት ኑሮዋችንን ማሻሻል አንችልም። ይህ አለም የምተመራበት ተፈጥሮዋዊ ህጓ ነው። ቃላቶቻችን በጥንቃቄ እንምረጥ፤ ለሌሎች የምንናገራቸውንም ሆነ ለገዛ እራሳችን የምናገራቸውን ነገሮች በጥንቃቄ ማስተዋል አለብን። አዘውትረን ቀና የሆኑ ንግግሮችን መጠቀም እንልመድ። “ይጎድለኛል፤ የለኝም፤” የሚሉትን ቃላቶች “ይኖረኛል፤ ይሞላልኛል” በሚሉት እየተካን ምን ያህል ለውጥ እንደሚያመጡ እንይ።በየትኛውም የኑሮ ሁኔታ ላይ ብንሆንም የምናመሰግንበት ነገር አናጣምና። አንደበታችንን በአብዛኛውን ጊዜ የአስተሳሰባችን ነጸብራቅ ነውና፤ እስቲ ለችግሮቻችን መፍትሄውን በውስጣችን መፈለጉን እንሞክረው።

 

 

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *