“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

መሶብ ሰፍቼ፤ ላም ገዝቼ…..

by | Aug 26, 2015 | መነቃቂያ inspiring stories | 0 comments

ይህንን ታሪክ ከልጅነቴ ጀምሮ፤ ከእናቴ አባቴ አፍ ሲቀባበል የሰማሁት ታሪክ ነው። በቤተሰባችን መሃከል ከዛሬ የራቀ ነገር ተነስቶ ክርክር ሲነሳ የአባቴ ወይም የእናቴ ማሳረጊያ ይህ ነው “መሶፍ ሰፍቼ….” እያሉ ታሪኩን ከዚህ በፊት አንድ ሺህ ጊዜ ደግመው ቢናገሩት እንኳን ደግመው ይተርኩታል። ታሪኩ ለፈገግታ በየመሃሉ ጣል የሚደረግ ቢመስልም፤ ሶስተኛ አይን ኖሮት ላስተዋለው ሰው ትልቅ መልዕክት አለው።

ታሪኩ እንዲህ ነው፤ ሁለት አንዲስ የተጋቡ ባልና ሚስቶች፤ አንድ ቀን ስለወደፊት ኑሮዋቸው ማውራት ይጀምራሉ። ሚስትየዋ የምተመኘውን ነገር እንዲህ ብላ ለባለቤቷ ትነግረዋለች ” መሶብ ሰፍቼ፤ መሶቡን ሸጬ፤ በገንዘቡ ላም ገዝቼ እዚህች መደብ ላይ አስራታለው” አለች። ይሄኔ ባልየው በሃሳቧ ሳይስማማ ይቀርና  “ላሟማ እዚህ መደብ ላይ አትታሰርም” ይላል። ሚስትየዋ መልሳ “አይ እዚህ ላይ ነው የምትታሰረው” ትላለች። ባልየው በንዴት “አትታሰርም ብያለው፤ አትታሰርም” ይላል። ሚስትየዋም በተራዋ ቱግ ብላ “ትታሰራለች” ብላ ድርቅ። ክርክራቸው እየናረ እየናረ ሄደ። በመጨረሻም የባልየው ትዕግስት ተሟጠጠና ፤ ክርክሩን አላቆም ያለችውን ሚስቱን ፈንክቶ ገደላት  ይባላል።

እንግዲህ ባልና ሚስቱ ለዚህ የበቁት፤ ገና መሶቡ ሳይሰፋ፤ መሶቡም ሳይሸጥ፤ ላሟም ሳትገዛ ነው። ገና የወደፊቱን በማሰብ፤ እና በሃሳብ ባለመግባባታቸው ብቻ፤ የትዳር ህይወታቸው እንዲህ በአጭር ተቋጨች። እኔ በግሌ በተረቱ ውስጥ የሁላችንም ህይወት በቅንጫቢው ማየት እችላለው። ገና ላልተሰፋው መሶብ፤ ላልተገዛው ላም እየተጨነቅን፤ ቅጽበቷን መኖር ያቅተናል።

ሁሌም ይህንን ታሪክ ስሰማው፤ ከተረትነቱ ይልቅ እውነታው ይገዝፍብኛል። የዚህ ዘመን ትልቁ የሰው ልጅ ችግር ጭንቀት ነው። ጭንቀት ደግሞ የሚመጣው ከሁለት ምክንያቶች ብቻ ነው። ወይ በትናንት ውስጥ በመኖር አልያም በነገ ውስጥ በመዋዠቅ ነው። ነፍስ ሰላም ኖሯት መኖር የምትችለው፤ ከጊዜ ጋር እኩል መራመድ ስትችል ብቻ ነው። ነፍሳች ከጊዜ ልቅደም፤ ወይም ወደኋላ ልበል ስትል፤ ቅራኔ ውስጥ ትገባለች። አመንም አላመንም የጭንቀት መንስዔው ዞሮ ዞሮ ከነዚህ ምክንያቶች አይዘልም።

“መሶብ ሰፍቼ፤ መሶቡን ሸጬ፤ ላም ገዝቼ……”እያልን አንድ ሰበዝ እንኳን ሳንመዝ፤ ብዙ መላምቶችን እየመዘዝን፤ መሶቡ ሳይሰፋ፤ ትልቅ የችግር ሰፌድ ሰፍተን እንጨርሳለን። ምኞታችን ገና ከጅምሩ የሚቀጠፈው እኮ፤ አንድ እርምጃ ሳንራመድ ስለጎዳናው ጠመዝማዛነት ስለምናስብ ነው። የሰው ልጅ ትልቁ ፈተና፤ ከዛሬ ጋር ተስማምቶ መኖር ነው። ከጊዜ ጋር ተስማምቶ መኖር ጥበብን ይጠይቃል። ብዙዎቻችን ገና መሶባችን ሳይሰፋ፤የላሟ መታሰሪያ ቦታ ያስጨንቀናል። አንድ ሰበዝ ሳንስብ፤ ወስፌያችን  ይለግማል።

አንድ ሺህ እርምጃ የሚጀመረው ከአንድ እርምጃ ነው። ሰው አንድ ሺህ እርምጃ ነው የምራመደው ብሎ አስቦ መንገዱን ቢጀምር፤ እሩቅ ሳይጓዝ ይደክማል። ሃሳቡ እያንዳንዷ እርምጃ ላይ ብቻ ከሆነ ግን፤ ሳያስበው አንድ ሺው እርምጃ ያልቃል። የሚያስጨንቀንን ነገር እስቲ እናስተውለው? እውነት ጭንቀታችን ወቅቱን የጠበቀ ነው ወይስ …”መሶብ ሰፍቼ፤ መሶቡ ሸጬ …..”አይነት ነው?

 

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *