“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

ሁሉ ዳኛ ሁሉ ተከሳሽ

by | Jun 16, 2015 | Guest writer-እንግዳ ጸሃፍት | 0 comments

ግርም ስለሚለኝ ነው። ሁላችንም በራሳችን የተሾምን ዳኞች ሆንን፤ ሌሎችን ፈራጆች፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች እራሳቸውን ሾመው ዳኛ ሆኑ፤ እኛ ደግሞ ተከሳሾች። የምን ፍርድ እና ክስ ነው ትሉኝ ይሆናል።  አዘውትረን ስለምንሰየምበት የዳኝነት ወንበር፤ መልሰን ደግሞ ስለምንቀመጥበት የተከሳሽ ወንበር ነው የማወራላችሁ።

በዳኝነት ወንበራችን ሌሎች በራሳቸው ህይወት የሚወስኑትን ውሳኔ የኛን ህልውና ይነካ ይመስል፤ የራሳቸውን መንገድ ስለመረጡ ብቻ  ሰዎችን እየጎተትን ባልተጻፈ የምናብ ህገመንግስታችን ለፍርድ እንገትራቸዋለን።  አብዛኛዎቹ ጥፋታቸው በህሊና ሚዛን የተለካ ሳይሆን፤ በደመነፍስ የሚሰፈር ነው። ስራቸው ድንበር አልፎ የኛን ህይወት ባይነካም፤ እጣታችን ግን ድንበር አልፎ ይቀስርባቸዋል።

ሌሎችም እንደዛው፤ በጓዳችን የሚገነፍለው ሽሮ፤ የነሱን ጓዳ ያቆሽሽ ይመስል ጠዋት ከተሰየምንበት የዳኝነት ወንበር ጎትተው ለክስ ይጠሩናል። እርስ በርሳችን በነጻነት መኖር አልቻልንም ምክንያቱም ሁሉም ዳኛ ሁሉም ተከሳሽ ነውና። ሰው ምን ይለኛል በሚል የኑሮ ስርዓት ለመኖር ተገደናል።  እያንዳንዳችን ለምንወስነው ውሳኔ የሌሎችን ይሁንታ ማግኘቱ ከተከሳሽነት የሚያድነን ብቸኛው አማራጭ ነው።ተፈራርተን እስከመቼ እንኖራለን?

ሁሉም በህይወቱ የራሱ የሆነ ምርጫ አለው። ምርጫቸው ከኛ ጋር አልተስማም ማለት ህገ ወጥ አያሰኛቸውም። ምን አልባት የሰውን አፍ ባንፈራ ልናደርጋቸው የምንሻቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ግን ሁሉም ዳኛ ነውና ፍላጎታችንን ገታ ማደረጉ ግድ ይለናል። የራሳችንን ህይወት በአግባቡ ሳንቃኝ፤ የፍርድ ወንበር ላይ ቂጥ ማለቱ የሁላችንም ልምድ ሆኗል። እርግጥ ነው ሰዎች በህይወታቸው ስህተት ይሰራሉ፤ አንዳንዴ የሚደርስባቸው ቅጣት ግን ከስራቸው በላይ ነው፤ ለምን? ሁሉም ዳኛ ስለሆነ። የሚገርመው ደግሞ ዳኞቹም፤ በሌላ ሜዳ ተከሳሽ መሆናቸው ነው። ኑሮዋችን ቅጥ አንባሩ የጠፋበት ፍርድ ቤት ነው። ነጻነታችንን እርስ በእርሳችን ተነጣጥቀን፤ ሁላችንም በአይናችን የተሸከምነውን ጉድፍ ትተን ለምን እጣታችን የሌላው አይን ይጎረጉራል?

ብዙ ሰዎች ተሸማቀው እንዲኖሩ ተፈርዶባቸዋል ፤ ሊያውም የሰሩት ስራ ከራሳቸው ህይወት ዘሎ የሌላውን ሳይነካ። ፍርዳችን ግን ድንበር ያልፋል።በሚመለከትን እና የኛን ህይወት፤ የማህበረሰቡን ህልውና በሚነኩ ጉዳዮች ለፈርድ መቆሙ ግዴታችን ነው። አለበለዚያ ግን በማይመለከተን  የሰዎች ህይወት ውስጥ እየገባን፤ ሌሎችም በማያገባቸው በኛ ኑሮ እየገቡ፤ አንዴ ፈራጅ አንዴ ተከሳሽ እየሆንን ኑሮዋችን እስከመቼ እናቃውሳለን?

ሰዎች የራሳቸውን ኑሮ እንዲኖሩ እንፈቀድላቸው።  ሌሎችም የራሳችንን ኑሮ እንድንኖር ይፍቀዱልን። ማንም ከስህተት የጸዳ የለም፤ መካሰሱን ትተን መተራረሙን ብንለምድ ይበጀናል። ለራሳችንም ሆነ ለሌላው ሰው ነጻነት ስንል የዳኝነቱን ወንበር እንልቀቅ፤ እስከነአካቴው ሳይሆን ቢያንስ በማይመለከቱን ጉዳዮች ለፈርድ አንቁም። በራሳችን እንዲደረግብን የማንፈልገውን ነገር ስለምን ሰዎች ላይ እናድርገው?

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *