“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

ወደ አላማህ እየተጓዝክ ከሆነ የተመልካቹን ጩኸት አትስማ

by | Jan 29, 2015 | መነቃቂያ inspiring stories

ብቅ ባልኩኝ ቁጥር የሚኮረኩሙኝ ሲበዙ……በእኔ ቅድሚያ ማመን ያለበት ማነው? እያልኩኝ ማሰብ ጀመርኩኝ፤ እኔ ወይስ ሌሎች ሰዎች?

ከልጅነት እስከ እውቀቴ ድረስ አንድ ነገር ለመስራት ስነሳ “አዪ…..ይህማ የማይሆን ነገር ነው”፤ “ አይሳካም”፤ “ሁሉም ሰው ሞክሮት አልተቻለም” የሚሉ ኮርኳሚ ንግግሮችን እስኪሰለቸኝ ሰምነቻለው። ሰምቻለውም ብቻም ሳይሆን ተቀብያቸው እግር እና እጆቼን እንደካቴና አስረዉኝ ኖረዋል። ሁሉም በክፋት ሳይሆን ፤ ለእራሳቸው አይሳካም የሚል አስተሳሰብ ስላላቸው ነው። ይህንን ሃሳብ በደንብ ፈትፍቶ የሚያስረዳ አንድ ሳነብ ያገኘሁትን ታሪክ ላጫውታቹህ…..

አንድ ቀን ኤሊዎች ሁሉ ይሰበሰቡና አንድ ትልቅ ተራራን ለመውጣት እንዲወዳደሩ ተደረገ። ተራራው ትልቅ ነበርና ውድድሩን የሚመለከተው ሁሉ “አይ…አይሆንላቸውም”፤ “ተራራው ጫፍም በፍፁም አይደርሱም” “ኤሊ እኮ ናቸው እንዴት ሊሳካለቸው ይችላል”፤ “ኸረ አሁን ይወድቃሉ” “ሆ ሆ የማይሆን ነገር …ለምን ይለፋሉ?” ይላል። ሁሉም የተሰማውን ይሰነዝራል።አንድም ተመልካች አንዳቸውም ከተራራው ጫፍ ይደርሳሉ ብሎ ያመነ አልነበረም።
የተመልካቹን ጩኸት ተከትሎ ፤ቀስ ቀስ እየለ….ተወዳዳሪዎቹ አንድ በአንድ መቀነስ ጀመሩ፤ አንድ በአንድ ተስፋ እየቆረጡ….ከውድድሩ ወጡ። ጥቂቶች በተስፋ ውድድሩን ይቀጥሉ ጀመር። ተመለካቹ “የማይሳካ ነገር ነው…..ቆይ አሁን ያቋርጡ የለ” ይላል። ውድድሩ በገፋ ቁጥር የተወዳዳሪዎቹም ቁጥር መቀነሱን ቀጠለ……በመጨረሻ አንድ ኤሊ ብቻውን ቀረ። ያ ኤሊ ታራራውን መውጣቱን ተያያዘው…..ውድድሩን ያቋረጡትን ኤሊዎችን ሳይመለከት ብቻውን ገሰገሰ።

ተመልካቹ አሁንም እንደማይሳካ ቢጮህ እሱ ግን መንገዱን ከራሱ ጋር ተያያዘው። እንዳሰበውም ከተራራው ጫፍ ደረሰ። ይህ ሁሉንም ያስገረመ ነበር። ውድድሩን ያቋረጡት ኤሊዎች እና ተመልካቾች ይህ ኤሊ ብቻውን ውድድሩን እንዴት እንደጨረሰ ገረማቸው…..ሊጠይቁት ሲሄዱ ግን፤ ያ ውድድሩን ያሸነፈው ኤሊ የማይሰማ ደንቆሮ ሆኖ ተገኘ። የአሸናፊነቱ ሚስጥርም የማንንም ጩኸት እና ንግግር ባለመስማቱ ነበረ።

ታልቅ ምኞት ካለህ፤ ጆሮህ ሌላውን አይስማ፤ “አይቻልም” “የማይሆን ነገር ነው” የሚል ተመልካች ሞልቷልና ዝም ብለህ መንገድህን ተጓዝ። የተምለካቹን ንግግር የምንሰማ ከሆነ…..የነፍሳችንን ጥሪ መስማት ያቅተናል፤ አላማቸንን በእንጭጩ ይቀጩታል፤ ልንኖርለት የሚገባንን ህልም ቅዠት ያደርጉታል። “አይቻልም” “አይሆንም” ሲሉ…….ነገሩን በራሳቸው አቅም መዝነው መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ህልም ካለን፤ አላማ ካለን፤ የምንኖርለት ነገር ካለ፤ ጀሮዋችንን ደፍነን መጓዙ ይጠቅመናል።

የተመላካች አፍ የስንቱን ተወዳዳሪ ተስፋ አጨለመ፤ የስንቱን የተስፋ ጭላንጭል በትንፋሻቸው አጠፋ? የስንቱን ጉልበት አንብረረከ። ተራራውን በስኬት ወጥተው የምናያቸው ሰዎች ሁሉም፤ ውድድሩን መጀመሪያ ሲጅመሩ ብቻቸውን አልነበሩም፤ እጅግ ብዙ ሰው አብሮ ተሳትፏል። ነገር ግን አሸናፊ የሆኑት የሰውን ጩኸት ያልሰሙት ብቻ ናቸው። እኔም እናንተም ልንደርስበት የምንጓጓለት ትልቅ የህይወት ተራራ ይኖራል…….እናም ከጫፉ ለመድረስ ከፈለግን ጆሮዎቻችን አሉታዊ ነገሮች እንዳይሰሙ እንድፈናቸው።

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments