“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

“Be the change you want to see in the world.”

አሻራዬ መነቃቂያ ገፅ

ሶሰቱ ማጣሪያዎች (Socrates’ Triple Filter Test)

by | Jan 29, 2015 | Guest writer-እንግዳ ጸሃፍት

በጥንታዊቷ ግሪክ ውስጥ ሶቅራጠስ ከሰው ሁሉ የተለየ እውቀት እንዳለው ይነገር ነበር። ፍልስፍናው እና እውቀቱ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች እንዲለይ አድርጎታል ። ከእለታት አንድ ቀን አንድ ለወሬ የቸኮለ ሰው ሶቅራጠስን በመንገድ ያገኘውና እንዲህ ሲል ይነግረዋል።

“ሶቅራጠስ……ስለ ጓደኛህ የሰማሁትን ነገር አውቀሃል?” ብሎ ወሬውን ሊቀጥል ሲል
“አንዴ አቁም” አለው ሶቅራጠስ ቀጥሎም “አንድ ፈተና አለኝ…….”ሶስቱ ማጣሪያዎች” ብዬ እጠራቸዋለው፤ እነሱን ካለፍክ የሰማኸውን ወሬ ትነግረኛለህ ፤ እኔም አዳምጥሃለው ……ካላለፍክ እና ከወደቅክ ግን የሰማኸውን ወሬ እንድትነግረኝ አልፈቅድልህም “

ሰውየው ግራ ቢገባውም ከሶቅራጠስ ጋር መሟገቱን አልፈለገምና በነገሩ ተስማማ። ሶቅራጠስም ወደ ጥያቄው አመራ
“የመጀመሪያው ማጣሪያ “እውነት” ነው፤ የሰማኸው ወሬ እውነት መሆኑን አረጋግጠሃል?” ሰውየውም-“ መስማቱን ነው እንጂ የሰማሁት ……እውነት መሆኑን እንኳን አላረጋገጥኩም” ሲል መለሰ
ሶቅራጠስ- “እሺ….እውነት መሆኑን አላረጋገጥክም…..ወደ ሁለተኛው ማጣሪያ እንለፍ….ሁለተኛው ማጣሪያ “ጥሩነት” ነው….ስለጓደኛዬ የሰማኸውና ልትነግረኝ የፈለግከው ነገር ጥሩ ነገር ነው?”
ሰውየው- “አይ…ጥሩ ነገር አይደለም….በአንፃሩ መጥፎ ነገር ነው” ሲል መለሰ
ሶቅራጠስ- “እሺ….የምትነግረኝ ነገር መጥፎ ነው…..በዛ ላይ እውነትነቱን አላረጋገጥክም……ሶስት ፈተናዎች ናቸው ብዬህ የለ…..አሁንም እድል አለህ….ሶስተኛውን ካለፍክ ማለት ነው……ሶስተኛው ጥያቄ “ጥቅም” ነው…..ስለጓደኛዬ የምትነግረኝ ነገር ምን ያህል ይጠቅመኛል?”
ሰውየው-“ አይ…..ጠቃሚ እንኳን አይደለም” አለው ይሄኔ ሶቅራጠስ ነገሩን በማጠቃለል
“እሺ ወዳጄ…..የምትነግረኝ ነገር እውነት ካልሆነ፤ ጥሩ ነገር ካልሆነ፤ ጥቅም ከሌለው ለምን ትነግረኛለህ?” አለው፤ ሰውየውም መልስ አልነበረውምና በዝምታ ተሰናበተ።

ሰዎች ስለ ሰው ሲያወሩ፤ አንድ ነገር አስባለው ከራሳቸው ህይወት የተረፈ ሰዓት እንዴት ኖራቸው? ወይስ የራሳቸውን ኑሮ ወደ ጎን አስቀምጠውት ነው? የራሱን ኑሮ የሚኖር ሰውማ እርግጥ ነው በዚህ በተጣበበ ኑሮ እንዴት ጊዜ ተርፎት የሌላውን ኑሮ ይኖራል?

እንደው የምንኖርበትን ማህበረሰብ እናስተውል፤ የራሳችንን ኑሮ ባለመኖራችን፤ ሌላውም የራሱን ኑሮ እንዳይኖር አደረግን። አፍ ፈርተው ስንት ሰዎች ችሎታቸውን ደበቁ? አፍ ፈርተው ስንቶች የተመኙትን ኑሮ መኖር አቃታቸው? አፍ ፈርተው ስንቶች ልዩነታቸው ካዱ? በአፍ ስንት እውነት እረከሰ? በአፍ ስንት ተስፋ ጨለመ? በአፍ ስንት ስህተተት ሳይታረም ቀረ? በአፍ ስንት ስብራት ሳይጠገን ቀረ? በአፍ ስንቱ ነፃነቱን ተነጠቀ?

ጣቶቻችንን እየተቀሳሰርን ለምን ኑሯችንን የተጠንቀቅ ኑሮ እናደርገዋለን? ተፈጥሯችንማ እንደ ወፍ በነፃነት መብረር ነበር፤ እንደ ሁሉም የምድር እንስሳ በነፃነት መኖር፤ ምን ያደርጋል ከተፈጥሮ እርቀን በገዛ ካቴናችን ነፃነታችንን አሰርነው እንጂ።
ለማነኛውም የሶቅራጠስን መንገድ መከተሉ ምን አልባት የወሬን በሽታ በትንሹ ያስታግስ ይሆናል፤ ስለ ሰው ወሬ ከመስማታችን በፊት ሶስቱን ፈተናዎች ማለፋቸውን እናረጋግጥ።

Mistre

Mistre

About Mistre I am the founder of this website www.asharaye.net. I enjoy learning and sharing personal development topics and love to entertain thought-provoking ideas. Writing to me is the best way to express my feelings and understandings about life in general. I am not an expert on any of the subject matters shared. I am just an individual with an opinion; therefore, anything I write and share on this platform is my understanding of the topic.

0 Comments