እንደ ጨው ያለች ትንሽዬ ቅናት

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች
(በሚስጥረ አደራው)
ከአበባው መልኩ ግጥሞች ውስጥ “ቅናት” የተሰኘውን ሲበዛ እወደዋለሁ። በተለምዶ በሚወዱት ሰው መቅናት የፍቅር ምልክት ነው ይላሉ፤ የሌላው አይነት ቅናት(ምቀኝነት) መጥፎነቱ ጥያቄ ውስጥ ስለማይገባ አናነሳውም። የፍቅር ጥልቀቱ ባሳደገው የቅናት መጠን እንደሚገለጽ የምናምን ሰዎች አለን፤ ትክክል ነው ማለት ግን አይደለም። መቅናት የሚወዱትን የግል ከማድረግ የሚመነጭ ሃይል እንደሆነ በማሰብ የሚያደርሰውን ጥፋትና የክፋት ሃሳብ በምክንያት ልንደግፈው እንወዳለን። ልክ እንደ ገጣሚ አበባው መላኩ፦
 
ፍቅሬን ሜዳ ላይ ጥላ ስትከዳኝ አይቻታለሁ
እንደ ገፋችኝ ትገፋ እያልኩ እረግማታለሁ
ዘወትር ሙሾ ታላዝን የእንባ ማዕበል ይጠባት
ደስታዬን እንዳጨለመች ደስታዋ ይጨልምባት
ሺህ እጥፍ ትጨድ አበሳ ለዘራችብኝ ጥፋት
እያልኩ እረግማታለሁ
የኮራችበትን ገላ መብረቅ ያንድደው በቁጣ
በላይዋ ዲን ይውረድባት ጥጋት መሸሻ ትጣ
እያልኩ እረግማታለሁ
የምድር የቀላይ ጥፋት በላይዋ ይወረድ ኩነኔ
ኑሮዋን ሲዖል ያድርገው ስቃይዋን ያሳየኝ በአይኔ
እንደከዳችኝ ትከዳ የኔ ያለችው ይሽሻት
ቀላዋጭ አይኗን ያፍርጠው ከውካዋ እግሯን ያልምሻት
ክንዷ በመጅ ይሰበር ሌላ ያቀፈችበት
አባ ጨጓሬ ይሙላው ፍራሹ የተኛችበት
የሌላ ሆና ብትከዳኝ አይጠሉ ጠልቻታለሁ
ስለማተቤ ብጠየቅ በአለም ላይ ካለ የምሻው
የረገምኳትን እላለሁ ሌላም እርካታ የለኝ
እሷን አምጡልኝ እላለሁ
ጥላቻዬና ፍቅሬ ናት እርግማኔና በረከቴ
ያለሷ ህይወት የሌለኝ ያሳበደችኝ ቅናቴ
 
ስለቅናት ከተነገሩ አባባሎች ውስጥ አንደኛው እንዲህ ይላል “ቅናት ማለት እንደ ጨው ነው፤ ጨው በመጠኑ ሲሆን ምግቡን ያጣፍጠዋል፤ ሲበዛ ግን ምግቡን የማይበላ ያደርገዋል። ቅናትም እንደዛው በትንሹ ፍቅርን ያጣፍጠዋል፤ ሲበዛ ግን ያስጠላል” ምናልባት ይህኛው አባባል ብዙዎችን ያስማማል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ትንሽ ቅናት የሚወዱን ሰዎች እኛን ምን ያህል ማጣት እንደሚፈሩ ስለሚያሳብቅ።
 
ላዎትዙ ግን ስለቅናትና ፍቅር እንዱህ ሲል ይጠይቃል “ በቅናት የሚያብብ ምን አይነቱ ፍቅር ነው?” ለጥያቄው መልስ ሲሰጥም “ሰዎች የሚቀኑት የሚፈልጉትና የሚሹት በሙሉ በውስጣቸው እንዳለ ባለማወቃቸው ነው” ይላል። ቅናት ከፍርሃት የሚመነጭ ስሜት ነው። መጠኑ ሲበዛ በእጃችን ያለውን ያስረሳናል፤ በውስጣችን ያለውን እንዳናይ ያደርገናል። በቅናት ውስጥ ፍቅራችን ካለማበቡም በላይ የራሳችንንም ማንነት ያደበዝዘዋል። አንዳንዴ እኮ ሌሎችን በመውደድ ውስጥ የእራሳችንን ዋጋ እንቀንሳለን፤እኛ እራሳችን የምንወደድ መሆኑን እንዘነጋለን። በምንወደው ሰው መቅናታችን ምናልባትም የራሳችንን ዋጋ ከማሳነስ የተነሳ ቢሆንስ? ይህንን ያልኩበት ምክንያት አንዳንድ ጊዜ በፍቅር ስም የሚጸነሰው ቅናት የምንወደው ሰው ሌላ ከእኛ የተሻለ ወይም የሚመርጠው ሰው ቢያገኝስ ብለን ከሆነስ?
 
ለማንኛውም እንደጨው ያለች ትንሽዬ ቅናት ከሁሉም ልብ ውስጥ የምትጠፋ አይመስለኝም። እንደው የአበባው መላኩን ግጥም በማሰብ ያሰፈርኩት እንጂ ምንም የተለየ ሃሳብ ለማስተላለፍ አይደለም። የጥበብ ስራዎች ስሜትን በቀጥታ ከመናገር ይልቅ በሾርኒ ወይም በተለየ መልኩ ሲገልጹት ውበት አለው ብዬ ስለማምን ይሆናል፤ በተለይ ግጥም። ለዚህም ነው ከላይ ባሰፈርኩት እርግማን በተሞላበት ግጥም ውስጥ እንኳን ጥልቅ ፍቅር የሚታየኝ።

Do you have any comments?