ሲያምኑኝ ከፋኝ

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

(በሚስጥረ አደራው) 

በእርግጥ…..ስስቅ አይተውኛል፤ በደስታ ስቦርቅ ስጮህ ሰምተውኛል። ሀዘንና ጭንቀት ይጋባል ስላሉኝ፤ በሽታዬን ለሌላው እንዳላጋባ፤ የውስጤን ደብቄ ደስተኛ መስዬ መታየት ጀመርኩኝ። የማስመስለው ደስተኛ መስዬ በመታየት የሰዎችን ክብር እንዳገኝ አልነበረም፤ የማስመስለው በእኔ ሀዘንና ጭንቀት ሌሎች እንዳይጨነቁ በማሰብ ብቻ እንጂ። ከዚህ በላይ ለሌሎች የሚሰጥ ምን ስጦታ አለ? የእናትነትን ፍቅር ከሌሎች ፍቅር በላይ የሚያደርገው እኮ የማስመሰል ሀይል ስላለው ነው።የእናት ፍቅር ትልቅ የማስመሰልን ጥበብ ያላብሳል፤ ውስጥ እያለቀሰ ጥርስ በልጅ ፊት ይስቃል፤ ሆድ እየጮኸ እጅ ልጅን ያጎርሳል፤ ልብ እየተከዘ ጉልበት ግን ልጅን ያባብላል። እኔም ትክክለኛው ስጦታ መሰለኝና ተቀበልኩት።

ሀዘኔን ደብቄ ደስተኛ መስዬ መታዬት ጀመርኩኝ። ቢያንስ የኔ መከፋት እንዳያስከፋቸው፤ ለሌላ ሰው ጭንቀት እንዳልሆን በማሰብ። በእኔ ላይ የዳመነው የሀዘን ደመና እንዳይዘንብባቸው የማስመሰል ጸሃዬን በላዬ አኖርኩኝ። በፊታቸው እየሳቅኩኝ እንባዬን ለማታ ማቆየት ጀመርኩኝ። ለሚጠይቁኝ ነገር ሁሉ ምላሼ ተመስገን ሆነ፤ ቢያንስ ይህ ጎደለኝ ብዬ ለእኔ እንዳይጸልዩና ጸሎታቸውን እንዳላረዝምባቸው በማሰብ። በማያስቀው እስቃለው፤ ቢያንስ የእኔ ሳቅ ዝም ያለውን ቤት ቢያደምቀው ብዬ። በማስመሰሌ ብዙ ገፋሁበት። ከጊዜ በኋላ ግን  እነሱ ከሳቁት በላይ መሳቄን ሲያዩ፤ ሀዘንና ደስታዬን ከገጽታዬ ሲያጡት፤ ቀንና ማታ መልሴ ተመስገን ሲሆንባቸው …… አመኑኝ!!! የምስቀው ከልቤ፤ ተመሰገን የምለው ሁሉ ነገር ሞልቶልኝ እንደሆነ አመኑ።

ማስመሰሌ እውን ሆኖ ያስከፋኛል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። ከዚህ ሁሉ ማስመሰል በኋላ ዛሬ ከልባቸው ሲያምኑኝ ግን ከፋኝ። እርስ በእርሳቸው ሲተዛዘኑ፤ እኔ ግን ሁሉ እንደተሟላለት ሰው አይዞኝ የሚለኝ ጠፋ ። ለረጅም ጊዜ የገደብኩት እንባ መፍሰስ ሲጀምር፤ ብዙ ከመሳቅ የመጣ እንጂ የሃዘን እንባ መሆኑን መረዳት አቃታቸው። ተመስገን ስል ይሰሙኝ ስለነበረ፤ ዛሬ ከምር ከፍቶኛል ስላቸው ሀዘን እንደማልችል ደካማ ቆጠሩኝ፤ “ዛሬ ገና ቀን ቢጎድል የምን እንዲህ ማማረር ነው” ብለው ተሳለቁብኝ። ማስመሰሌን አመነው አስቤው በማላቀው መጠን አስከፉኝ።

እርግጥ ስስቅ አይተውኛል፤ ተመስገን ስል እውነት ነው ሰምተውኛል። ግን እኮ ስስቅ የከረምኩት ደስታ ለሰው የሚሰጥ ስጦት ስለመሰለኝ እንጂ እኔም እኮ እንደነሱ ይከፋኝ ነበር። ተመስገን ስል የከረምኩት እኮ ሳይጎድልብኝ ቀርቶ አልነበረም፤ እንዳላሳስባቸው ጭንቀት እንዳልጨምርባቸው ብዬ እንጂ። የተከዙ ጊዜ አብሬ ያለተከዝኩት እኮ ቢያንስ የኔ መጠንከር ቢያጠነክራቸው ብዬ ነበር። ሲላቀሱ አብሬ ያላለቀስኩት እኮ ሀዘናቸው ላይ ሀዘን እንዳልጨምር ነበር። የሆኑትን ሁሉ እኔም ሆኜ ሳለ ማስመሰሌን አምነው ዛሬ አስከፉኝ።

የማስመስለው እንዲያምኑኝ አልነበረም? ወይስ የማልችለውን መንገድ ነበር የጀመርኩት?  ዛሬ ሁሉ ነገር የማስመሰል ገደቡን ጥሶ ሲያልፍና እኔም እንደነሱ አይዞኝ መባል ሲያምረኝ፤ በቸልታ አለፉኝ። ይሄኔ ነው ማስመሰሌን እንዳመኑት የገባኝ። ያንን ሁሉ የማስመሰል ጥረቴን እረስቼ፤ “ሰው እንዴት በቀላሉ ያምናል?” እያልኩኝ ይኸው ወቀሳ ጀምሬያለው። ሺህ ጊዜ ብስቅ እንዴት “እውነት ከልብ የመነጨ ሳቅ ነው?” ብሎ የሚጠይቅ ይጠፋል? ሺህ ጊዜ ተመስገን ብል “ይህ ማመስገን የእውነት ነው?” ብሎ የሚሞግት እንዴት ይጠፋል። አንዳንድ ሰው የሚያስመስለው እንዲታመን ሳይሆን የሚሞግተው ሰው እየፈለገ ቢሆንስ?

One thought on “ሲያምኑኝ ከፋኝ

Do you have any comments?