ሀሙስ ከደረስን እሁድ ብዙ አይርቅም!

Posted on Posted in መነቃቂያ

(በሚስጥረ አደራው)

ህይወት ከሰባት ቀናቶች የበለጠ እድሜ የላትም፤ የትኛው ቀን ላይ ነን? ይህንን ያለው ታዋቂው ገጣሚ ሮበት ብላይ ነው።  ገጣሚው ይህንን የተናገረው አሜሪካ በወቅቱ የነበረችበትን ጦርነቶች አስመልክቶ ተቃውሞውን በገለጸበት ግጥሙ ውስጥ ነበር። ይህ ሰው ስነጥብበን ለሰላም ለማዋል ብዙ ተግቷል፤ እንደውም “American Writers Against the Vietnam War” የሚል ማህበርም መስርቶ ነበር፤ ይህ ማህበር በወቅቱ የነበረውን ጦርነት የሚቃወም ማህበር ነበር። ብዕር ከምንም አይነት ጦር የበለጠ ጉልበት እንዳለው ስላመነ፤ በብዕሩ ብዙ ስለሰላም ብዙ ብሏል።

በጽሁፎቻቸው ለሰላም የሚታገሉ ጀግኖች በሁሉም ቦታ አሉ፤ የዛኑ ያህል ግን የጥፋት መልክተኞችም ብዙ ናቸው። ብዕር እንደሌሎች መሳሪያዎች ሁሉ በጥንቃቄ ሊያዝ የሚገባው መሳሪያ ነው። ሰው ሽጉጥ ስላለው ብቻ፤ ሽጉጡን በየቦታው አያወጣም፤ ለቁምነገሩም፤ ለጨዋታውም እየመዘዘ ልዋጋበት አይልም። ብዕርም የዛኑ ያህል ጥንቃቄና ማስተዋልን የሚጠይቅ መሳሪያ ነው። ሁሉም ነገሮች በቃላት ስለሚጀመሩ፤ ቃላትን የሚተኩሰው ዋነኛ መሳሪያ ደግሞ ብዕር ስለሆነ። ለዚህ ነው ይህንን ሰው ላነሳው የወደድኩት፤ ስለሰላም በብዕሩ ስለተዋጋ።

አዋቂ ነን ካልነው ጨቅላዎች ተሻሉ

     በከፋቸው ቁጥር ያለ አንዳች ይሉኝታ ይነፋረቃሉ

አዋቂ ሰው ሁኖ ሰው መጮህ ካልቻለ

ካልተወለደ ጽንስ እንደምን ተሻለ?

I say to myself: “Go on, cry. What’s the sense
of being an adult and having no voice? Cry out!” –Robert Bly

ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው። የሚያሳዝነው ሁላችንም የምንጣለው ዘለዓለም እንደሚኖር ሰው ነው። እኔ በህይወቴ ከሞቶ ዓመት በላይ የኖረ ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም፤ እሱንም በቴሌቭዥን ድንቃድንቅ ወሬዎች ላይ። አብዛኛው ሰው የእድሜው ጣሪያ ከሰማኒያና ከዘጠና አያልፍም፤ ይህንን አጭር ህይወት ነው “ሰባት ቀናቶች” ያለው ገጣሚው። እንደው ሰባ አመትን ብንወስድ እንኳን፤ አርባ የሞላው ሰው ሃሙስ ላይ ደርሷል ማለት ነው። ይህ ጨለምተኝነት አይደለም እውነታ እንጂ። አንዳንዴ ብዙ ጊዜ እንዳለው ሰው እንዘናጋለን፤ በጥላቻና ሰላምን በማራቅ ሳናውቀው እሁድ ይመጣል። ሰው የወጣትነት እድሜው ላይ ከደረሰ፤  እሮብን እንዳለፈ ይቆጠራል፤ ህይወት አትተነበይምና። ያም ሆነ ይህ፤ እሁድ ሳይመጣ ሰላምና ፍቅርን በየቤታችን ያግባልን። የደካሞች አስተሳሰብ ቢመስልም እንኳን፤ ብዙ የምንጣላባቸው ነገሮች ከንቱዎች ናቸው፤ ይዘናቸው የማንሄድ፤ በሰማያዊው ቤት እንኳን ዋጋ የማያሰጡን። ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም የተባለው እኮ፤ ጥላቻና ክፋት በምንም ስሌትና ቦታ ዋጋ እንደሌለው ስለታወቀ ነው።

“Some masters say our life lasts only seven days.
Where are we in the week? Is it Thursday yet?
Hurry, cry now! Soon Sunday night will come.”-Rober Bly

ህይወት ከሰባት ቀናቶች አትበልጥም፤ እሁድ ከደረሰ የደቂቃ እድሜ እንኳን ምርቃት አትሰጥም። ሀሙስ ላይ ካላችሁ ይላል ጸሃፊው፤ እሁድ ብዙ አይርቅም። በቅዳሜ እና እሁድ እድሜ ደግሞ ከሰላምና ከፍቅር የበለጠ እፎይታን የሚሰጥ ምንም  ነገር የለም።

2 thoughts on “ሀሙስ ከደረስን እሁድ ብዙ አይርቅም!

  1. ewunet new enkuan hamus lay honen sayehon segnom lay honen enkuan benehonem kesew gar beselam menor betam asefelagim new tekekelem new thanks selehulu neger

Do you have any comments?