የምትሰጡትን ልብ በሉ! Reconsider what you offer!

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

(በሚስጥረ አደራው)

“Queen Sheba loads forty mules with gold bricks

As gift for Solomon …..

What foolishness is to take gold?

To Solomon, when the dirt of his land

Is gold. You who think to offer your intelligence, reconsider.”- Rumi

ያቺ ንግሥት ሳባ፤ ጠቢቡን ሰለሞን በጎበኘች ጊዜ

አነውልሏት ነበር? የምኞት የናፍቆት የጉጉት አባዜ?

አልሰማ ብላ ነው? ወይስ መካሪ አጥታ

ለሸክም የሚከብድ ወርቅ ይዛ መሄዷ፤ ለክብሩ ስጦታ

ወርቅ ለሰለቸው፤ ወርቅ እየረገጠ፤ ወርቅ ሆኖበት ቤቱ

ማላገጥ አይሆንም? ወርቅን እጅ መንሻ ስጦታ መስጠቱ?

እኛም

ለሰው እጅ መንሻ የገበርነው ግብር

እውቀት፤ ጥበብ፤ ፍቅር፤ ሙገሳና ክብር

ለእኛ ውድ ሆኖ እጅ…..ግ አግዝፈነው

ተቀባዩ እጅ’ላይ ፤ ተራ ኢምንት ሆኖ፤ ሲረክስ አየነው!!!

ይህን ግጥም የፐርሽያው ሩሚ ፤ የንግሥት ሳባና የጠቢቡ ሰለሞንን ግንኙነት ተንተርሶ ከጻፋቸው ግጥሞች ውስጥ አንደኛው ነው። ለነገሩ የግጥሙ ሃሳብ በንግስተ ሳባ እና በጠቢቡ ሰለሞን ላይ ያንዣብብ እንጂ፤ መልዕክቱ እንደሌሎቹ የገጣሚው ስራዎች ከታሪኩ የራቀና የጠለቀ ነው። ምክንያቱም ገጣሚው ሁሌም ለሃሳቡ መግለጫ ሜታፎር Metaphor ስለሚጠቀም።

“You… who think to offer your intelligence reconsider” ከባድ ሃሳብ ነው። ወርቅ ለተረፈው ወርቅ ሰጥተን እንዲገረም መጠበቅ ሞኝነት ነው ይላል ። ለእኛ ውድ የሆነው ነገር ለሌላውም ሰው ውድ እየመሰለን ስንቴ ተሸውደን ይሆን? ብዙ የምናውቅ መስሎን ከእኛ በላይ ለሚያውቅ ብዙ አውርተን፤ ከእኛ በላይ ለኖረ ስለኑሮ ሰብከን፤ ከእኛ በላይ ለታገለ ስለ ትግል አስረድተን፤ ከእኛ በላይ ለሚያምን ስለ እምነት ሞግተን፤ ወርቅ ለተረፈው ወርቅ ሰጥተን አናውቅም?

በንግሥተ ሳባ ዘንድ ውድ የሆነው ወርቅና፤ ጠቢቡ ሰለሞንን ግን በዝቶ ያሰለቸው ወርቅ ዋጋው በሁለቱ ዘንድ እንዴት እኩል ይሆናል? ብዙ ነገሮች እርስ በእርሳችን የሚያጋጩን ዋጋቸው ለእያንዳንዳችን ስለሚለያይ ይሆን? ለእኛ ብርቅ የሆነብንን ለሌሎች ተራ ሆኖ ስናየው ይከፋናል። ስህተት ሆኖ ሳይሆን፤ የአንድን ነገር ዋጋ በግል ብቻ መተመኑ ልዩነትን ስለሚያመጣ ነው።

በቃላት እና በቁስ ለማይመሰሉ ስጦታዎች ነው ሩሚ፤ “የምትሰጡትን ነገር ልብ በሉ” ሲል የሚያስጠነቅቀው። እንካችሁ የምንለውን ጥበብ፤ ምክር፤ ፍቅርና እምነት እኛ ጋር ብቻ ባለው ዋጋ ብንመዝነው፤ ለሰጠነው ሰው ዋጋው በዝቶ ሊያስደስተው ወይም አንሶ ሊያስከፋው ይችላል ። ተራ ተራ ነገሩን እንኳን በምስጋና እየተቀባበልን የምናሳልፈውና በዚህ ሃሳብ ውስጥም የሚጠቀስ አይደለም (የገጣሚውን የሃሳብ ጥልቀት ስለማይመጥን)።

ገጣሚው በሌላ እይታ ይህንኑ ሃሳብ ሲያስቃኘን እንዲህ ይገልጸዋል።

“When have I asked you?

For a sop for my soup, I don’t want gifts

From you. I want you to be ready for the gifts I Give”

“ከአንቺ ስጦታ አልፈልግም፤ የምፈልገው እኔ ለምሰጥሽ ስጦታ ዝግጁ እንድትሆኚ ነው”

ይህ እንግዲህ ጠቢቡ ለንግስቱቷ የመለሰላት መሆኑ ነው። ተቀባይ መሆን ሲገባን፤ ሰጪ የምንሆንባቸውን አጋጣሚዎች ሲያስረዳን። በተቀባይ ቦታ ሰጪ፤ በሰጪ ቦታ ተቀባይ ሲቀመጥ ስጦታ ዋጋውን ያጣል ። እኛ የጎደለንን ለተረፋቸው ስንሰጥ ባይናገሩትም የሚመልሱልን ይህንን ነው። ሌሎች ስለ ንግሥተ ሳባና ስለሰለሞን የከተባቸውን ግጥሞች ከቻልኩኝ አካፍላችኋለው……አካፍላችኋለው ስል፤ “የምትሰጡትን ልብ በሉ” የሚለውን የተጻረርኩኝ መሰለኝ። ለማለት የፈለግኩት፤ እንወያይበታለን ነው፤ እናንተም እንዴት እንደተረዳችሁት ብታካፍሉኝ ደስ ይለኛል።

6 thoughts on “የምትሰጡትን ልብ በሉ! Reconsider what you offer!

  1. ጥሩ ሀሳብ ነው። ነገር ግን “ያለውን ያካፈለ ንፋግ አይባልም።” ከሚለው አባባል ጋር እንዴት ማስማማት እንችል ይሆን?

  2. 1st & 4most I Wanna Thanx U More Than I Can Say B/c Mistre Really U R Ze Great & Right Person In Right Place & Time. Ur Ideas R Ze Bridges & Keys Of Locked Doors, Closed Roads & e.t.c Excellent Continue. May CREATOR Be With All Of Us! Peace, Love & Prosperity 4 Our Planet! Wait U Soon… Bye Stay In Peace.

Do you have any comments?