ጠጌ ጠጌ አይነኬ “Asymptote”

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

(በሚስጥረ አደራው) 
ምንም እንኳን ሂሳብ ላይ እምብዛም ብሆንም ካልተረሱኝ ጥቂት የሂሳብ ጥበቦች (መደመርና መቀነስ ናቸው ዋነኞቹ መቼም) ሌላ አይምሮዬ ውስጥ አልላቀቅም ብሎ የቀረው “Asymptote” የሚለው የሂሳብ ጽንሰ ሃሳብ ነው። የያኔው የሂሳብ አስተማሪዬ አቶ ኤሊያስ ለ” Asymptote” የሰጡን አማርኛ ፍቺ በወቅቱ “ጠጌ ጠጌ አይነኬ” የሚል ነበር። በመጀመሪያ ስያሜው ስለሚያስቀኝ ነበር ከህሊናዬ አልጠፋ ያለው፤ እየቆየ ሲሄድ ግን ይህ “ጠጌ ጠጌ አይነኬ” የሚባለው ነገር የሂሳብ ጽነሰ ሃሳብ ብቻ አልመስልሽ እያለኝ መጣ፤ ከብዙ ነገሮች ጋር እየተነካካብኝ ይኸው ዛሬም ደረስ ያስቀኛልም ያስገርመኛልም።

እንግሊዘኛው ትርጉም ይህ ሲሆን- A line that continually approaches a given curve but does not meet it at any finite distance.
መስመሩን የሚጠጋ፤ በእጅጉ የሚቀራረብ ነገር ግን ፈጽሞ እውነተኛውን መስመር የማይነካ ሌላ ሃሳዊ መስመር እንደማለት ነው። “ጠጌ ጠጌ አይነኬ” መስመር ምንም ቢጠጋ እውነተኛውን መስመር ፈጽሞ አይነካውም። ዛሬ እንዴት አነሳሽው ካላችሁኝ? ማወቅ እና መኖር ትንሽ ግራ አጋብተውኝ ነው። ስለብዙ ነገሮች እናውቃለን፤ ግን ኖረናቸው አናውቅም። ሰው አንድን ነገር የእውነት ካልኖረው፤ ስለዛ ነገር ሲያወራ ለእውነቱ የቀረበ እንጂ እውነት እንዴት ሊሆን ይችላል?

የመኖርን ትክክለኛ ሚስጥር ማወቅ የሚቻለው ሲኖሩት ብቻ። መንገዱም ሲሄዱበት እንጂ እንዲሁ ከሩቅ ሊያዩት አይቻልም። እዚህ ላይ የምንሸወደው ነገር ቢኖር፤ መኖርን ከመኖራችን በፊት ለመረዳት ስንሞክር፤ የምናሰምረው መስመር “ጠጌ ጠጌ አይነኬ” አይነት ነው እንጂ፤ መኖር ቢመስልም የመኖርን ያህል አይሆንም። ሳቅን ሲስቁት እንጂ ስለሳቅ ሲያስቡ ስሜት አይሰጥም። አንድ ሰው ስለሳቅ ብዙ ሊመራመር፤ ሊያነብ ሊፈላሰፍ ይችላል፤ እስካልሳቀ ድረስ ግን እውነተኛውን የሳቅ ስሜት ሊያውቀው አይችልም፤ ልፋቱ ሁሉ “ጠጌ ጠጌ አይነኬ” መስመሮችን ማስመር ይሆናል።

ብዙ የህይወት እንቆቅልሾች የሚፈቱት በማወቅ ብቻም ሳይሆን በመኖርም ጭምር ነው፤ እንደሚመስለኝ ብዙውን ጊዜ የህይወት መስመሮቻችን “ጠጌ ጠጌ አይነኬ” አይነቶች ሳይሆኑ አይቀሩም። በሃሳብ ደረጃ እናውቃቸዋለን፤ ግን ኖረናቸው አናውቅም። ለእውነት የተጠጋ ግን እውነት ያልሆነ እንደማለት ነው። እውነት ደግሞ ፍጹም እውነት ካልሆነ በቀር ትንሽም ቢሆን ቅጥፈት ከተቀላቀለበት እውነትነቱ ይረክሳል። እንደውም “ግማሽ እውነት ብዙውን ጊዜ ከግማሽ ያነሰ ነው” ይባላል። ለእውነት የቀረበ እውነትን በፍጹም እውነት ልንለው አንችልም። ምንም ያህል ለእውነት ቢጠጋ “ጠጌ ጠጌ አይነኬ” ከመሆን አይዘልምና።

ማወቅና መኖር ግራ የሚያጋቡን ምናልባትም ለዚህ ነው።አንዳንድ ነገሮችን ከመጠን በላይ እናውቃቸውና የኖርናቸው ያህል ያጃጅሉናል፤ ግን “ጠጌ ጠጌ አይነኬ” መስመሮች እንጂ እውነተኛው መስመሮች አይደሉም። ብዙ ስለደግነት ስናወራ ደግ የሆንን ይመስለናል፤ ስለፍቅር አብዝተን ስንሰብክ እንደአፍቃሪ እራሳችንን እንቆጥራለን፤ ስለሰላም ስንሰብክ ሰላማዊ የሆንን ይመስለናል እነዚህ ግን ለእውነት የተጠጉ “ጠጌ ጠጌ አይነኬ” መስመሮች ናቸው። ይህንን ለእውነት የተጠጋ እውነት፤ እውነት የሚያደርገው “ተግባር” ብቻ ነው።

የመኖርን ያህል ስለኑሮ የሚያስረዳ ትክክለኛ መንገድ የለም። ሌሎች መስመሮች ሁሉ “ጠጌ ጠጌ አይነኬ” አይነት መስመሮች ናቸው። ለምን ይመስላችኋል በተመሳሳይ የታሪክ መስመር ውስጥ “ኖረናል” እና “እናውቃለን”  የሚሉት ተመሳሳይ ታሪክን ሲናገሩ የሚለያዩት? የኖሩት ትክክለኛው መስመር ላይ፤ እናውቃለን የሚሉት ደግሞ “ጠጌ ጠጌ አይነኬ” መስመር ላይ ስለሚራመዱ ነው። ስለ አንድ ነገር ማወቅ ለእውነት ያቀርባል እንጂ እውነት የሚሆን አይመስለኝም፤ የእውነት መስመር በመተግበር፤ በመኖርና በመሆን ውስጥ ብቻ የሚሰመር መስመር ስለሆነ። ሌሎቹ ሁሉ “ጠጌ ጠጌ አይነኬ” መስምሮች ናቸው።

Do you have any comments?