ሶስት አለሞች አንዲት ነፍስ 

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

(በሚስጥረ አደራው)

እንደዛሬ ያለው ቀን ሲገጥመኝ ይህን አስባለው። ሰው በሶስት አለሞች ውስጥ ገባ ወጣ እያለ እድሜውን የሚፈጅ ፍጡር ይመስለኛል። በእያንዳንዱ አለም የምንሰነብትባቸው የግዜ እርዝማኔዎች ቢለያዩም። ከአንዱ አለም ወደ ሌላው እየተዘዋወርን ይህንን እረጅም የህይወት ጉዞ እንለዋለን….
“ይህች አንዲቷ ነፍስ ሶስት አለሞች ለምዳ
እፎይ ብላ አትኖርም አዬ የሰው እዳ”

የመጀመሪያው አለም- ከሰውም ከራሳችንም ሸሽተን የምንሰነብትበት አለም። ይህ አለም ብዙን ግዜ ከእምነት እና ከጥሞና ጋር የሚዋሃድ አለም ነው። በዚህ አለም ብዙ ባንሰነብትም እንደው ከግርግሩ መሸሽ ሲያምረን እፎይ የምንልበት ምናባዊ ስፍራ ነው። ልክ አንድ የፉከራ ዘፈን ላይ እንደሰማሁት ዘፈን “ገለል በልና ገለል አድርጋቸው” አይነት ፍልፍና የዚህ አለም እውነታ ይመስለኛል። ገለል በማለት ገለል የምናደርጋቸው ብዙ የህይወት እውነታዎች አሉ። ከሰው ጋር ብንወያያቸው መልስ የሌላቸው፤ ወደ ውስጣችን ዘልቀን ከራሳችን ጋር ብንወያይ መልስ የማይገኝላቸው፤ አንዳንድ ጥያቄዎች አሉ። ምንም እንኳን እነዚህ ጥያቄዎች ሁሌም በውስጣችን ቢኖሩም፤ ጩኸታቸው ያየለ ቀን፤ ከሁለተኛውም ከሶስተኛው አለም አስሩጠው እዚህ አለም ውስጥ ያሰነብቱናል……

ሁለተኛው አለም- ሰው ከሰው ሸሽቶ ከራሱ ጋር ብቻ መሆን ሲያምረው የሚሰነብትበት አለም ። አንዳንዴ እኮ መስማት ይሰለቻል፤ ውጭ ውጭውን ማየት እጅ እጅ ይላል። መልሶች ሁሉ ተደርድረው ጥያቄው የሚጠፋበት ወቅት አለ፤ ያኔ ነው በሩጫ እያለከለክን ወደዚህ አለም የምንገባው። በዚህ አለም፤ መልስ ሞልቷል፤ የጠፋው ጥያቄ ነው፤ እሱን ፍለጋ ነው የምንዳክረው። ይህ ሁለተኛው አለም፤ ከመጀመሪያውም ከሶስተኛውም አለም በእጅጉ የጠበበ ነው። የግል አለም ለምን ይሰፋል? እንግዳ የማይደፍረው ቤት ለምን ይሰናዳል? ይህ አለም ወደላይ ለማንጋጠጥ እምነቱን ስናጣ፤ ወደ ሰው ለምቅረብ ብርታቱን ስናጣ መቆዘሚያ መደባችንን የምንዘረጋበት ሁለተኛውም ምናባዊ አለም ነው።

ሶስተኛው አለም- ሰው ከራሱም ከፈጣሪውም ሸሽቶ በሰው ግርግር ውስጥ የሚደበቅበት አለም ነው። በዚህ አለም ነው አዘውትረን የምንገኘው። ውክብክብ ያለ፤ ሰው የራሱን ጩኸት አፍኖ የሌላውን ሹክሹክታ የሚያዳምጥበት፤ የብዙሃን አለም ነው። በዚህም አለም ሰዎች ሁሉ ከራሳቸው ሸሽተው በጋርዮች ስርዓት፤ በጋራ እምነትና አስተሳሰብ፤ በጋራ ፍልስፍናና እውነት የሚደነቋቆሩበት፤ ሰፊ አለም ነው። ሰው ከራሱ ጋር ብቻ አኩኩሉ ሲጫወት የሚታየው በዚህ በሶስተኛው አለም ብቻ ነው። በዚህ አለም የጋራ እውነት እንጂ የግል አመለካከት የለም፤ ፍርድ እንጂ መረዳት የለም፤ ጩኸት እንጂ ትርጉም ያለው ንግግር የለም፤ ሳቅ እንጂ ሀሴት የለም። ቢሆንም ግን በሰመመን የሚያኖር ጊዜ ማሳለፊያ አለም ነው፤ መደበኛ መኖሪያችን ነው……
ምንም እንኳን ጓዝና ቀለባችን በሶስተኛው አለም ውስጥ ቢሆንም፤ ግርግሩ ሲሰለቸን፤ የውጭውና የውስጡ ጦርነት ሲግል፤ ወደ ሌሎቹ ሁለት አለሞች ጎራ ማለታችን አይቀርም። እናም አንዲት ነፍስ በሶስት አለሞች ትኖራለች፤ መጓዝ፤ መሄድ የማይሰለቻት የሰው ልጅ ነፍስ…….

2 thoughts on “ሶስት አለሞች አንዲት ነፍስ 

  1. Thanks Mistrye for sharing and inspiring with such blessed articles all the time, i really admire your commitment and courage to share such motivational story with out any reward. however, i would like to ask u that “introspection” where did u put among the three world…coz i often get myself on it.

    1. I think most of us pretty much have the same patterns. I find myself a lot on the third one as well. But i think the main thing is having the awareness.

Do you have any comments?