ባዶነትና ደስ የሚለው ዜማ

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

(በሚስጥረ አደራው)
“listened to the story told by reed
of being separated
since i was cut from the reedbed
i have made this crying sound” -Rumi

መቃው ሲናገር ስሙ፤ በዜማው ሲጮኸው ብሶቱን
ናፍቆቱን ሲያስተጋባ፤ ቁልቁል ሲናፍቅ መሬቱን
የጠቢባን ሁሉ ዜማ፤ የጥበብ ጩኸት በራሱ
ናፍቆት ነው መነሻው፤ ባዶነት ነው ጥንስሱ

እንደ ሩሚ አገላለጽ፤ የዋሽንቱ ዜማ እና ለቅሶ ከመሬቱ ስለተለየ ነው። የዋሽንቱን አሰራር ብንመረምር ውስጡ ባዶ ነው፤ ዜማው ወደውስጥ በሚሳብ አየርና በጣት በሚደረግ ጨዋታ የሚፈጠር ነው። መቼም ሁላችንም አንድን ሀሳብ በተለያየ መልኩ እንረዳዋለን። ይህ የመቃ ሀሳብም ለእያንዳንዱ ሰው የራሱ ትርጉም ቢሰጠው የምገረም አይደለሁም። እኔ ግን እንዲህ ተረድቼዋለሁኝ……

ከባዶነት ውስጥ ብዙ ድምጾች ይወጣሉ። በቅድሚያ ባዶነት ( Emptiness) የሚለው ሀሳብ ወይም ቃል፤ ከአለማወቅ ጋር ወይም በተለምዶ “ቦዶ” ከምንለው ተራ አነጋገር ጋር እንዳይምታታብን እጠይቃለው። በመቃው ህይወት ውስጥ የምናስተውለው ባዶነት፤ መቃው ከመሬቱ ( From the source) ሲነጠል ያለውን ክፍተት ነው። ያ ክፍተት ነው ፤ በዋሽንቱ ውስጥ የምንሰማው ዜማና ለቅሶ ።

ይህ ክፍተት እና ባዶነት ይመስለኛል፤ ጽሁፍ ሆኖ፤ ዘፈን ሆኖ፤ ግጥም ሆኖ፤ ቲያትር ሆኖ፤ ስዕል ሆኖ የምናየው እና የምንሰማው። ሰው ሁሌም ከፍተት ባለበት ጎኑ እንደዋሽንት ማዜሙ አይቀርም። አለም ላይ የምናያቸው ፈጠራዎች በሙሉ፤ ከዚህ አይነቱ ክፍተትና፤ ወደምንጭ ለመመለስ ከመናፈቅ የሚመነጩ ናቸው።

ከላይ ያሰፈርኩት የሩሚ ግጥም፤ ሌላኛውን ትርጓሜም ላካፍላችሁ ወደድኩኝ

“listen to the reed -flute
How it complains
Telling the tale of separation
Ever since i was cut from the reed bed
Men and Women have moaned in my lament
I seek out a heart that, being separated
Is Shred into pieces
Then i can describe the pain of longing
Whoever has gone from his origin
Seeks to return to the days of his union.

“የዋሽንቱን እሮሮ ስሙ፤
” ከመሬት ከተገነጠልኩ ጀምሮ እንዲሁ አዜማለው ፤ የሰው ልጅም ከኔው ጋር አብሮ በሀዘን ይተክዛል። ከወደደው ነገር የተለየ ልብን እፈልጋለው በዜማዬ እጠራለው፤ እንዲህ አይነት ልብ ሳገኝ፤ በእንጉርጉሮዬ የናፍቆትንና የመጠበቅን ህመም አስረዳዋለው። ከምንጩ የራቀ ማንኛውም ነፍስ፤ ወደ ምንጩ ለመመለስ ይናፍቃል” ” እንደማለት ነው።

እንደናፈቀ ሰው ስለናፍቆት አሳምሮ የሚጽፍ ማን አለ? ወዶ እንደተለየ ሰው ስለፍቅር ከልቡ የሚያዜም ማን አለ? ስለፍቅር የሚሰብኩት፤ ወደፍቅር ለመመልስ የሚናፍቁት ናቸው። ስለእውነት የሚለፍፉት፤ ወደ እውነት ለመመልስ የሚመኙ ነፍሶች ናቸው። ልክ መቃው ወደመሬት ለለመለስ ካለው ናፍቆት የተነሳ እንደሚያንጎራጉረው ሁሉ።

እንግዲህ የጠቢባን ሁሉ ጩኸት፤ ከሚናፍቁት እውነታ ጋር ለመገናኘት ቢሆንስ? ጸሀፊያን፤ ደራሲያን፤ ሰዓሊያን፤ በምንጩ እና በእኛ መካከል ያለውን ክፍተት ቢሆንስ ጥበብ ብለው የሚሰጡን? የዋሽንት ዜማ የሚያስተክዘን ምናልባት የምንሸሽገውን ክፍተት ስለሚያስታውሰን ይሆን? መቃው ወደ መሬት ለመመለስ ናፍቆ እንደሚጮኸው ሁሉ፤ የእኛ ወደምንለው እውነት ለመመለስ ያለን መናፈቅ ቢሆንስ በተለያየ መልኩ የሚያስጮኸን?
ይህ ክፍተት ሀዘን ቢመስልም ውበት ግን ያለው ይመስላል………ደስ የሚል ዜማ

2 thoughts on “ባዶነትና ደስ የሚለው ዜማ

  1. mistreyeee how are you my dear?am hoping you are fine,am so speechless as what to say to you but l really like what I have read and keep on my dear

Do you have any comments?