ልምጥነት The beauty of Flexiblity

Posted on Posted in Uncategorized

(በሚስጥረ አደራው)
ልምጥነት ለ Flexiblity ያገኘሁት ተቀራራቢ ቃል ነው። ስለዚህ በዚህ ጽሁፍ ልምጥነት ስል Flexiblityን እየገለጽኩ እንደሆነ ይታወቅልኝ።
ግትርነት ከሰው እስከ ህይወት የሚያነካካን መልካም ያልሆነ ባህሪ ነው። ነገሮች እኛ ባላሰብናቸው መንገድ ሳይሄዱ ሲቀሩ ፤ ከህይወት ጋር እንዴት ነው መግባባት የምንችለው? እንዴት ነው እጥፍ ዘርጋ ብለን ከኑሮ ንፋስ ጋር መሄድ የምንችለው? ለዚህ ጽሁፍ ሶስት ምሳሌዎችን እንደሚከተለው አቀርባለው ።

የዳዎ የልምጥነት ፍልስፍና

ሰዎች ሲወለዱ ተለማጭ ናቸው፤ እንደ አስፈላጊነቱ የሚዘዋወሩ፤ሲሞቱ ግን ግትር ናቸው
ዛፎች መብቀል ሲጀምሩ ስስ ናቸው፤ሲሞቱ ግን ደረቅ ናቸው
ግትርነትና ድርቅ ማለት እንድግዲህ የሞት ቀለሞች ናቸው
ልምጥነት የመኖር ምልክት ነው
ዛፍ ጠንካራ ሲሆን፤ ለጥቅም ይቆረጣል
ግትርነት እና ጥንካሬ ወደታች ያወርዳሉ
ልምጥነና ዝግታ ወደ ላይ ያደርሳሉ
አንዳንዴ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን ማለት፤ ከሰው ከተፈጥሮ ባህሪ እና ከተፈጥሮ ከራሱ ጋር አብሮ አይሄድም። የሰው ልጅ አቅም ውስን ነው። ምኞቶቻችን እና ግቦቻችን በሙሉ በሁለት እውነቶች ላይ የተመሰረቱ ናቸው። አንደኛው በእኛ ቁጥጥር ስር ያሉ ነገሮች ሲሆኑ፤ ሁለትኛ ከእኛ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ነገሮች ናቸው። የእኛ ሀላፊነት በራሳችን ቁጥጥር ስር ያሉ ነገሮችን በአግባቡ ማደረግ ነው፤ ከእዛ ውጪ እኛ ያሰብነው ነገር ባይሳካ፤ ከሁኔታው ጋር ልምጥ ሆኖ መጓዙ ይበጀናል። ግትርነት የመንፈስ መሞት ነውና፤ ልምጥነት ግን የመኖር ምልክት።

ጎንበስ በል አትሰበር

በባህር ዳር ላይ የሚበቅሉ ዛፎች፤ አውሎ ንፋሱን የሚቋቋሙት፤ ጎንበስ በማለት ነው። እንዚህ ዛፎች ግትር ብለው ቢቆሙ እጣ ፋንታቸው በአውሎ ንፋሱ መሰበር ነው። ጎንበስ ማለታቸው የመኖራቸው ሚስጥር ነው። የሰው ልጅ ህይወትም ከዚህ አውሎ ነፋስ አያመልጥም፤ ጎንበስ ካላላን ሰብሮን የሚያልፍ ከባድ ነፋስ አለ:: ማጎንበስ የመሸነፍ ምልክት አይደለም፤ በአንጻሩ የብልህነትና ልዩ የሆነ የማሸነፍ ጥበብ ነው። ነገሮች እኛ ካሰብናቸው ውጪ ሲሆኑ፤ ጎንበስ ማለትን እንደመሸነፍ አንቁጥር።

ውሃ…

አንድ ወራጅ ውሃን እንደምሳሌ እንውሰድ፤ ወደታች ቁልቁል እየወረደ አንደ ከፍታ ቦታ ቢያገኘው፤ “ይህ ደንቃራ ቦታ ስለምን ከፊቴ ተገተረ” ብሎ አያዝንም፤ ሌላ ለመቅደድ የሚመች መንገድ መርጦ ይፈሳል እንጂ። ብዙ ጠቢባን ሰውን ከውሃ ጋር እጅግ ያመሳስሉታል። የእኛም ባህሪ ከውሃ ልምጥነት መለየት የለበትም። አንድ እክል ሲያጋጥመን፤ የጉዞዋችን መጨረሻ ነው ማለት አይደለም፤ ምናልባት መንገዳችን ያ እንዳልሆነ እየተነገረን ይሆናል።
እንግዲህ ጽናትና ልምጥነት እንዳይምታቱብን እንጠንቀቅ። ጽናት ማለት ለቆሙለት አላማ፤ ለሚያልሙት ህልም፤ ለወጠኑት ውጥን፤ ለሚመኙት ምኞት እስከወዲያኛው መታገል ሲሆን፤ ልምጥነት ግን ወደ ግባችን የሚያደርሰንን መንገድ እንደ አስፈላጊነቱ መለዋወጥ ማለት ነው። ከላይ ያሰፈርኩትን የዳዎ ፍልስፍናን እንደ መዝጊያ ልጠቀመው እወዳለው::( From the book, The Spirit of Tao)
When people are born
When people are born they are supple
and when they die they are stiff
when trees are born they are tender
and when they die they are brittle
stiffness is thus the cohort of death
flexibility is the cohort of life.
when a tree is strong
it is cut for use
so the stiff and strong are below
the supple and yielding on top.

ለአላማህ ግትር ሁን ለመንገዱ ግን ልምጥ ሁን!!!

2 thoughts on “ልምጥነት The beauty of Flexiblity

Do you have any comments?