ሰኞ ለት ተያየን በድንገት…..እሁድ ቅልጥ ያለው መውደድ

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

(በሚስጥረ አደራው)
“ሰኞ ለት ተያየን በድንገት
ማክሰኞ በህልሜ መጣ ሞኞ
እሮብን ለፍቅር ተሳሰብን
ሀሙስ ልቤን አለው ደስ ደስ
አርብ ላይ ብንውል ሳንተያይ
ቅዳሜ ተኛሁኝ ታምሜ
እሁድ ቅልጥ ያለው መውደድ”

ሰኞ ተጠንስሶ እሁድ ከፍጻሜ የደረሰ ፍቅር አጋጣሟችሁ ያውቃል? ፍቅር እንዲህ መንገዱ አልጋ በአልጋ ቢሆን ማን ይጠላ ነበር። ሰኞ ያገኙትን ሰው እሮብ ለፍቅር ማሰብ፤ ሀሙስ በደስታ መጥለቅለቅ፤ አርብ ስላልተገናኙ ቅዳሜ ታሞ መተኛት፤ እሁድ ደግሞ የለየለት መውደድ ውስጥ መግባት ቀላል ነው። እውነት ፍቅር እንዲህ መንገዱ አጭር ቢሆን ደስ አይልም ነበር? በምናቤ የዚህ ታሪክ ፍጻሜ እንዲህ ሆኖ ታየኝ። ምናልባት ዘፈኑ እንደ “እርጂኝ አብሮ አደጌ ” ክፍል ሁለት ቢኖረው ማለቴ ነው። የመጀመሪያውን ሳምንት አስቴር ከላይ እዳሰፈርኩት ተጫውታዋለች መጪው ሳምንት ግን ሳስበው እንዲህ የነበረ ይመስለኛል… ቅልጥ ያለው መውደድ ከሆነበት እሁድ ቀጥሎ ሰኞ ሲተካ…..
“ሰኞ ለት ፍቅራችን በረደ
ማክሰኞ ቻው ብሎኝ ነጎደ
እሮብን ለፍች ተሳሰብን
ሀሙስ ንዴት ተሰማኝ
አርብ ላይ ምንም ሳንገናኝ
ቅዳሜ ተኛሁኝ ታምሜ
እሁድ ፊርማውን ቅድድ”

ይህ ጽሁፍ ፈጽሞ ስለዘፈኑ ትችት አይደለም። የዘፈኑን መግቢያ ለጽሁፌ መንደርደሪያ ተጠቀምኩበት እንጂ። አሁን ነገሮች ፈጣን ሆነው የሰው ልጅ ትዕግስት ፈተና ውስጥ የገባበትን ወቅት የሚያሳይ ጥበብ ስለመሰለኝ ነው። አሁን ያለንበትን ዘመን ብዙዎች “The age of Instance Gratification” ይሉታል። ያሁን ዘመን ሰው በቴክኖሎጂ መንፈሱ ተጭበርብሮ ነገሮችን ምን ያህል በፍጥነት እንደሚፈልግና ምን ያህል ትዕግስት እንዳጠረው እንዲሁም በነገሮቹ ሁሉ አቋራጭ ምንገዶችን እንደሚመርጥ ለማስረዳት ነው።

እኛ የዚህ ዘመን ሰዎች በህይወታችን አብዝተን የምንፈልጋቸው ነገሮች ዋጋ እንደሚያስከፍሉን ዘንግተናል። በህሊናችን ቀላል የሚመስሉን ነገሮች በተግባር ምን ያህል ውስብስብ እንደሆኑ መገመት ይሳነናል። አንድ ግዜ አንድ መምህር እንዲህ ሲናገር ሰምቼው ነበር “በህይወታችሁ ከባድ ፈተና አይግጠመኝ ማለት፤ ለበለጠ ሹመት ዝግጁ አይደለሁም ማለት ነው” ብሏል። ፈረንጆች “For another level there is another Devil” ይላሉ።የምንፈልጋቸው ነገሮች ውድ በሆኑ ቁጥር ፈተናውም ከባድ እየሆነ ይመጣል። ዋጋ ያላቸው ስጦታዎች ሁሌም ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍሉ ግድ ስለሚል። ዘመናችን ግን ትዕግስት አልባ አድርጎናል፤ ትንሽ ዋጋ የሚያስከፍሉ ነገሮችን ሳይታወቀን እየመረጥን ነው።

ሰኞ ተገናኝቶ እሁድ ቅልጥ ያለው ፍቅር ውስጥ መግባት ለመዝፈን እጅግ ቀላል እና ደስ የሚል ሀሳብ ሲሆን ለመኖር ግን ከባድ ነው።
ዘፈኑ ስለፍቅር ስለሆነ ፍቅርን ቅድሚያ ሰጠሁት እንጂ፤ ለማንሳት የፈለግኩት ነገር ከዛም ይሰፋል። ልጅ እያለን የወደፊቱን ኑሮዋችንን ስናስበው እንደዘፈኑ ቀለል ያለ ነበር፤ ከአንደኛ ደረጃ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ማለፍ፤ ከዛም ኮሌጅ መግባት ሲቀጥል ስራ አለቀ በቃ!!! ስንኖረው ግን እውነታው ከዛ በእጅጉ የራቀ ነው። ሰኞ ተዋውቆ እሁድ እንደመጋባት ቀላል አይደለም።
በትዳርም ብንመጣ እንደዛው ነው፤ ተዋውቆ መጋባት ከዛ መውለድ ከዛ የልጅ ልጅ ማየት ሲዘፍኑት ነው፤ ሲኖሩት ግን ውጣ ውረዱ እጅግ ከባድ ነው። በኑሮ ውስጥ አይምሮ ቀድሞ የማይደርስባቸው፤ ጊዜ ብቻ ሲፈቅድ የሚያሳየን ፈተናዎች ይገጥሙናል።

ሆኖም ግን ሰው እየኖረ መሆኑን የሚያውቀው ሲፈተን ነው፤ ውድቀት ከሌለ ድል እንዴት ይጥማል? ሀዘን ከሌለ ደስታ እንዴት ጣዕሙ ይታወቃል? ምናልባት አንድን የህይወት ጎዳና ጀምረን “እንዴ እኔ እኮ እንዲህ ከባድ አልመሰለኝም ነበር” እያልን ከሆነ፤ ሀሳብ እና ተግባር የሰማይና የምድር ያህል እርቀት እንዳላቸው ለራሳችን እናስታውስ። በአስቴር ዘፈን ፍቅር ይዞት ነገሮች ሁሉ በሳምንት የሰመረለት አፍቃሪ አይገኝም ፡) እንደ ዘፈኑ ፍቅር ቀላል ቢሆንማ ማን ሳያገባ ይቀር ነበር?
መጽሀፉ እንደሚለው “የተጠሩት ብዙዎች የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸው” የተጠሩት ማለት በሀሳብ ደረጃ ነገሩን የሚያውቁት ሲሆኑ፤ የተመረጠት ግን ሀሳቡን በተግባር የማዋል ብርታትና ጽናት ያላቸው ናቸው፤ ምንም መንገዱ ጎርበጥባጣ ቢሆንም።

እንደውም አንድ ነገር ትዝ አለኝ፤ ሰኞ ለት የሚለውን ዘፈን የመረጠ አፍቃሪ በሳምንቱ የሚከተለውን የጥላሁንን ዘፈን የሚመርጥ ይመስለኛል
“አለማወቄ  እንጂ ፍቅሬ እኔ አላረገውም
ፍቅር እንዲህ መሆኑን ባውቅ አልጀምረውም” (ይህ እንኳን ለጨዋታ ያህል ነው)

One thought on “ሰኞ ለት ተያየን በድንገት…..እሁድ ቅልጥ ያለው መውደድ

 1. ጋሽ አለማየሁ የተባሉ የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት የቅኝት መምህር አንድ ዝግጅት ላይ እንዲህ ብለው በግሩም የክራር ችሎታቸው ታግዘው አንጎራጎሩ፦
  አንድ አዝማሪ የፍቅርን ነገር እንዲህ መስሎ አንጎራጉሮታል አሉን
  “የፈጣሪ ነፍሱ መቼም አይማር፣
  ለየቅል አድርጎት ፍቅርን ከትዳር”
  ለምሥጢር ምሥጢር አያብራሩለትም አደራ ብለው በምሥጢር ይተውለታል እንጂ።
  በርቺ እህቴ!

Do you have any comments?