የሜቭላና ሰባቱ ጥበቦች

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

(በሚስጥረ አደራው)
“In generosity and helping others, be like a river
In compassion and grace, be like the sun
In concealing other’s faults, be like the night
In anger and fury, be as if you have died
In modesty and humility, be like the earth
In tolerance, be like the sea
And either appear as you are, or be as you appear”
እንሂን ሰባት የሜቭላና ጥበቦችን እኔ እንደሚከተለው ተረድቻቸዋለው። ዘርዘር አድርጌ ከሌሎችም ነገሮች ጋር እያጣቀስኩኝ አቅርቤያቸዋለው፦

 ለሰዎች ደግ ስትሆን እንደወንዝ ሁን– ወንዝ ሰው መርጦ አያጠጣም። አጎንብሶ ሊጠጣ ለወደደ ሁሉ ሳይሰስት ያጠጣል። ምናልባትም ደግነታችሁ እንደወንዝ ይሁን ያለው፤ ሳትመርጡ፣ ለለመናችሁ እጃችሁን ዘርጉ ለማለት ይመስለኛል። ሌላው ወንዝ ወደፊት ብቻ የሚሄድ ወደኋላ የማይመለስ ሲሆን ቀጣይነቱን ይመሰክራል፤ የኛም ደግነት እንዲህ እንዲሆን ሲመኝልን ይሆን? ዛሬ ተጀምሮ ነገ የማያበቃ፤ እንደወንዝ የሚፈስ መልካምነት ድንቅ ነው። ሌላው የወንዝ ውበቱ ዝቅ ብሎ ሳይጮህ መፍሰሱ ነው። ዝቅ ብሎ ሌሎችን ከፍ እንደማድረግ ምን ውብ ነገር አለ? ይህንን አደረግኩኝ፤ እንዲህ ደግ ሰራው እያሉ መጮህ የደግነትን ክብር ይነካል፤ እንደወንዝ በዝምታ፤ ለሌሎች መልካም መሆን ነው እውነተኛው ደግነት።
 ስትራሩ እና ለሰው ስታዝን እንደጸሃይ ሁን– እዚህ ላይ ሌላኛው የፐርሺያ ገጣሚ ያለው ትውስ አለኝ። “ከዚህን ያህል ጊዜ በኋላም እንኳን ጸሀይ ለምድር ውለታ አለብሽ አላለቻትም፤ ከውለታ የጸዳ ፍቅር እንደጸሃይ ያበራል” ሲል ገጥሟል። ለዚህም ነው ስታዝኑ እና ለሰው ስታስቡ እንደጸሀይ ሁኑ ያለው። ውለታ እንደዋልን ሳይሰማን የምንሰጠው ደግነት ጸዳል ያለው ስለሆነ። ጸሀይ ለምድር ብርሃን እንደሆነች ሁሉ፤ ከውለታ የጸዳው ምግባራችን ለኑሮዋችን ብርሃን ነው።
 የሰውን ጥፋት ስትሸፍን እንደ ምሽት ሁን– ሰው በምሽት ብዙ ነገሮች የሚያደርገው የሌላውን ሰው አይን ሸሽት ነው። ጨለማ ጉድ ደባቂ ነው። ብዙ ሰዎች ከስህተቶቻቸው በላይ ይቀጣሉ ብዬ አምናለው (በግሌ)። አንዷ ስህተታቸው በአደባባይ እየበዛችባቸው፤ ብዙዎችን ከትናንት ስህተታቸው ጋር ተጣብቀው እንዲቆዩ አድርገናቸዋል። እንደጨለማ የሰው ስህተትን እንሸፍን ሲባል፤ መወቀስ ያለበት አይወቀስም፤ ስህተት የሰራ ሁሉ እየተሸፋፈነለት ይኑር ማለት አይመስለኝም። ይልቁንም የሌሎችን ስህተት ለኛ መመጻደቂያ አናድርገው ለማለት ነው። እንደሰው ሁላችንም ስህትትን እንሰራል፤ ነገር ግን ትናንት በሰራነው ስህተት ዛሬንም ነገንም ማጣት የለብንም። ለሌሎችም እንዲሁ፤ ለንጋታቸው እድል እንስጣቸው (ሁለተኛ እድል)።
 በንዴትህ ወቅት እንደ ሞተ ሁን- ሞት የእንቅልፍ ታላቅ ወንድም ነው ይሉታል። ከጸጥታ ሁሉ በላይ የከበደ ጸጥታ ሞት ነው። በንዴት ውስጥ እንደሞተ ሰው ጸጥ ማለት፤ ከጥበቦች ሁሉ በላይ የገዘፈ ጥበብ ይመስለኛል። እንደሞት ሁሉን የሚያሳልፍ ትዕግስት ይኑራችሁ ሲለን ነው።”ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ነገር አትስራ” ይላሉ። ንዴታችንን ለቅጸበት በጸጥታ ብናሳልፈው፤ ምን ያህል ከጸጸት እራሳችንን እናድን ነበር።
 ሌላውን ስታከብርና እራስህን ዝቅ ስታደርድ እንደ ምድር ሁን– “ይህ ሰው መሬት ነው ጸባዩ” ሲሉ እሰማ ነበር። መሬት ሁሉን ቻይ ናት፤ ለሁሉም እድል የምትሰጥ ዝቅ ብላ ሌሎችን በላይዋ የምታኖር ናት። ሰው እንደምድር ይሁን ሲባል፤ ሁሉም እየተነሳ ይርገጠው ማለት ሳይሆን፤ የሰውን እኩልነት አምኖ፤ በፍቅር ይኑር ለማለት እንጂ። ሌላው ማንሳት ያለብን የምድር ጸጋ ሀብቷ ነው።ምድር ሀብታም ባለጸጋ ናት፤ ለሰው የማትነፍገው ብዙ ሀብት አላት። ሰውም እንደምድር የብዙ ጸጋዎች ባለቤት ነው። መልካም ነገር ዘርተውበት ክፉ ፍሬ የሚያበቅል መሬት የለም። ሰውም በላዩ መልካም ምግባሮችን ሲዘራ፤ መልካም የህይወትን ፍሬ ሊለቅም የተፈጥሮ ህግ ይፈቅድለታል።
 የመቻቻል አመልህ እንደ ውቂያኖስ ይሁን– ሰፊ የመቻል ልብን ሲያመላከተን ነው እንግዲህ። በተለይ ለዚህ ለእኛ ዘመን ሰዎች እንደውቂያኖስ ከሰፋ መቻቻል በላይ ምን የሚያስፈልገን ነገር አለ? መቻቻል ከንትሹ ቤተሰብ፤ ጀምሮ እስከትልቂቱ አለም ደረስ እየጠበበ የመጣ፤ ከውቂያኖስነት አልፎ ልትደርቅ እንደተቃረበች የውሃ ሽንቁር መስሏልና።
 ሌላው የመጨረሻው የገጣሚው እረድፍ እንዲህ ይላል “ወይ የሆንከውን ምሰል፤ አልያም የመሰልከውን ሁን”። አብዛኛውን ጊዜ የምንናገረውን አይደለንምና። የምንመስለው እና እውነተኛው ማንነታችን ክፍተት አለበት። ይህ ክፍተት የሌለበት አንድም ባይኖርም፤ እራስን እየፈተሹ መጓዙ ግን ክፍተቱን እያጠበበው ይሄዳል። ሰው ለፍጹምነት መጓዝ የለበትም፤ ፍጹም ንጹህ መሆን ለሰው የተሰጠ አይደለምና፤ በቆሸሹ ቁጥር መንጻት ግን ባህሪያችን ሊሆን ይገባዋል። የሆንነውን ለመምሰል፤ አልያም የመሰልነውን ለመሆን ሁሌም ወደውስጣችን ልናይ ይገባናል።
እንግዲህ ከወንዝ፤ ከጸሀይ፤ ከምሽት፤ ከምድር፤ ከውቂያኖስ፤ እንዲሁም ከሞት የተቀመመን ባህሪ አስቡት፤ እኔ እንደሚመስለኝ፤ የኑሮዋችን መምህራን፤ ከመጽሀፍት እና ከተለምደው እውቀት በላይ ተፈጥሮ እና አካባቢያችን ይመስሉኛል። ይህንን ለማይት ግን ሶስተኛ አይንና ስድስተኛ የስሜት ህዋስን ይጠይቃል።

Do you have any comments?