በፍቅር “መውደቅ” ወይስ “መነሳት”

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

እንደው በምዕራብያውያን ዘንድ ስለፍቅር የሚደሰኮርበት ወቅት ነውና ትንሽ ስለፍቅር ልሞነጭር ፈለግኩኝ።አንስታይን “በፍቅር ለወደቀ ሰው የመሬት ስበት ተጠያቂ አይደለም” ማለቱ ይነገራል። በፍቅር መውደቅ ምን ማለት ነው? “መውድቅ” የሚለውን ቃል ለመጠቀም ለምን እንደመረጥን ሳስብ ነበር ሰሞኑን። ምናልባት “መውደቅ” ብለን የምንጠራው ተሞክሮ ለወደድነው ሰው የምንሆንለትን ነገር፤ የምንከፍለውን መስዋትነት ለማጠቃለል ይመስለኛል።

ኤሮስ፤ ፊሊይ….አጋፔ እና ስቶርጅ

በግሪካውያን ዘንድ ፍቅር በአራት መልኮች ይገለጻል።

ኤሮስ- ፆታዊ ፍቅርን ወይም በአካዊ መሳሳብ የሚመጣ ፍቅርን የሚገልፅ ሲሆን፤ ይህ አይነቱ ፍቅር አንድ ወንድ እና አንዲት ፍቅር በስሜት ላይ ተመስርተው የሚፈጥሩት አካላዊ ጥምረት ነው።

ፊልያ- ኤሮስ አካላዊ ጥምረት ሲሆን፤ ፊልያ ደግሞ የነፍስ መዋሃድን የሚገልጽ የፍቅር አይነት ነው። በጓደኝነት ላይ የተመሰረተ አልያም ተመሳሳይ ፍላጎት እና ባህሪ ባላቸው ሰዎች ዘንድ የሚመሰረት፤ ከአካላዊ መሳሳብ በዘለለ ስሜት የሚፈጠር ፍቅር ነው።

አጋፔ- ከሁሉም የጠለቀ ትርጉም ያለው ፍቅር ነው፤ምክንያታዊ ያልሆነ እውነተኛን ፍቅር፤ መስዋትነት የሚጠይቅ፤ የወደድነውን ሰው እንድናስቀድም የሚያስገድድ የፍቅሮች ሁሉ የበላይ የሆነ ፍቅር ነው። አምላክ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር የገለጸው በእንደዚህ አይነቱ ጥልቅ ፍቅር ነው። አንድ ልጁን መስዋት ያስደረገ፤ በምንም የማይለወጥ እውነተኛ ፍቅር። ይህ አይነቱን ፍቅር “ብስል” ፍቅር ሲሉም ይጠሩታል።

ስቶርጅ- የሚባለው የፍቅር አይነት ደግሞ በጥንታውያን ግሪኮችም ዘንድ ቢሆን በብዛት የሚጠቀስ አይደለም ሆኖም ግን ቤተሰብ ለልጅ ያለውን አይነት ፍቅር የሚገልፅ እንደሆነ ይነገራል።

ታዲያ በአብዛኛዎቻችን ዘንድ የሚታወቀው ወይም የተለመደው የፍቅር አይነት ኤሮስ የሚባለው ነው፤ (ቀን ተቆጥሮለት እየተከብረ ያለው ማለት ነው)።እንቅልፍ የሚነሳው ፤እህል የሚዘጋው፤ያፈቀርነውን ሰው ካላየን ቀኑ የማይመሽልን የሚመስለን አይነቱ ፍቅር ነው እንግዲህ ኤሮስ ተብሎ የሚጠራው።ኤሮስ በጥንታውያን ግሮኮች አፈታሪክ መሰረት እራሱ የፍቅር አምላክ ነው።ሲመስሉትም አይኑን በጨርቅ የተሸፈነ ፍጡር አድርገው ነው፤የዚህ ትርጉሙ ፍቅር እውር መሆኑን ለማመልከት ነው።የጦር መሳሪያውም ጦር እና ዳርት እንደሆነ ይታመናል፤ጦሩን በሰው ልብ ውስጥ ሲሰካም ሰዎች በፍቅር ይወድቃሉ።ይህም ከላይ ወዳነሳሁት ጥያቄ ይመልሰኛል

በፍቅር “መውደቅ” ለእውነተኛ ፍቅር ትክክለኛ ስያሜ ነው? ከዛ ይልቅ በፍቅር “መነሳት” የሚለው አባባል ይበልጥ ጽኑ ፍቅርን አይገልጸውም? አምላክ ለሰው ልጅ ያሳየው ፍቅር “አጋፔ” የሚሉት ፍቅር ነው ይላሉ። በዚህ ፍቅር እኛ ከወደቅንበት ተነሳን እንጂ አልወደቅንም። በተራ ነገሮች ለሚጠናወቱን ስሜቶች “በፍቅር ወደቅን” ብንል አይገርምም፤ ከልብ ስናፈቅር ግን “በፍቅር ተነሳን” ይበልጥ የሚጥም ቃል ይመስለኛል።

አርጀንቲናዊው ጸህፊ ፓውሎ ኮዌሎ፤ ጽኑ የሆነውን እውነተኛ ፍቅር እንዲህ ሲል ይገልጸዋል

“Agape is total love. It is the love that consumes the person who experiences it. Whoever knows and experiences agape learns that nothing else in the world is important — just love.”

ይህ አይነቱ ፍቅር አይጥልም፤ ይልቁንም ከፍቅር ሌላ የሚበልጥብን ምንም ነገር እንደሌለ ስለሚያሳምነን ጸንቶ ያቆመናል እንጂ። እናም ምናልባት በፍቅር እንደወደቅን የምናስብ ከሆነ፤ ፍቅራችን የትኛው ይሆን? ብለን መጠየቁ አይከፋም። በእውነተኛ ፍቅር ብዙ ተዓምሮች ሲፈጸሙ አይተናል፤ ታዲያ ይህ ሰዎች በፍቅር ስለወደቁ ሳያሆን…….ስዎች በፍቅር ብርታት ስላገኙ ነው።

እንዲህ አይነቱን ፍቅር ያድለን…….የሚያስወድቅ ሳይሆን…..የሚያቀናን ጽኑ ፍቅር። የምትወዱትን ላገኛችሁ ፍቅራችሁን ያጽናላችሁ፤ በፍለጋ ላይ ላላችሁ ከምትወዱት ያጋጥማችሁ የዛሬ ምኞቴ ነው።

5 thoughts on “በፍቅር “መውደቅ” ወይስ “መነሳት”

  1. mistr am really sorry for being late to comment on the love issue you have mentioned and l think you know I am biggest fan of yours and keep the good work. l have always gained something excellent, and please just send me the title of any lesson giving book my dear. See you

  2. ፍቅር <– all three are the 6th letters in the alphabet…hmmmmh just a different angle to view and "angle view" is everything in my daily life.

Do you have any comments?