“ሰጠኝ” እና “አገኘሁ”

Posted on Posted in መነቃቂያ

(በሚስጥረ አደራው)

የድሮ የኢኮኖሚክስ አስተማሪዬ ነበሩ። ስማቸው ለጊዜው ተዘነጋኝ። ነገር ግን ከአመታት በፊት የተናገሩት ነገር ዛሬም ድረስ አይምሮዬ ውስጥ አለ። አንድ  ቀን የመጨረሻውን የሴሚስተሩን ፈተና ከተፈተንን በኋላ ስለ ውጤት ሲመክሩን እንዲህ ነበር ያሉት። “ከተማሪዎች ባህሪ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር፤ ውጤታቸው ጥሩ ሲሆን ማለትም ኤ ሲሆን “ኤ አገኘሁኝ” ይላሉ። በአንጻሩ ውጤታቸው መጥፎ ሲሆን ደግሞ ለምሳሌ ሲ ሲያገኙ ፤”ሲ ሰጠኝ” ነው እንጂ የሚሉት ሲ አገኘሁኝ በፍጹም አይሉም” ሲሉ የተሰማቸውን ነገሩን።

ይህ አባባል ከትምህርት ቤት ውጤት በዘለለ ጥልቅ መልዕክት ያለው ነገር ነው። መምህሩ የተናገሩት በሙሉ አንድ መሰረታዊ እውነታ ላይ ያተኮረ ነው ይኸውም ሰዎች ለውድቀታቸው ሃላፊነትን መውሰድ ፈጽሞ እንደሚከብዳቸው ነው። መልካም ውጤት ስናገኝ በጥረታችን እንዳገኘነው ስናምን፤ መጥፎ ውጤትን ስናገኝ ግን ውድቀታችንን በሌሎች ሰዎች ወይም በሁኔታዎች ማሳበብን እንመርጣለን። ለስኬታችን ሃላፊነትን መውሰድ ከቻለን ለምንድን ነው ለውድቀታችን ሀላፊነት መውሰድ የሚሳነን?

በህይወታችን ሀላፊነትን እንደመውሰድ በዚህ ምድር ላይ እኛን ሊያድነን የሚችል ነገር ያለ አይመስለኝም። ነገሮች ሲስተካከሉ እኛ እንዳስተካከልናቸው ካመንን፤ ነገሮች ሲበላሹም እኛ እንዳበላሸናቸው ማመን መቻል አለብን። ምክንያቱም ለስህተቶቻችን ሀላፊነት መውሰድ ካልቻልን፤ የኑሮዋችንን መሪ የሚጨብጡት ሁሌም ሌሎች ሰዎች ይሆናሉ።

“አገኘሁ” የምንልባቸው ጥቂቶች ነገሮች ይኖሩናል፤ እኛን የማያስወቅሱ እና የሚያስከብሩ መልካም ነገሮች እስከሆኑ ድረስ ብቻ። የሚያሳዘንው ግን “ሰጠኝ” የምንላቸው ነገሮች መብዛታቸው ነው። እኛን የሚያስወቅሱ ነገሮችን በሙሉ “አገኘሁኝ” ብለን በፍጹም ሀላፊነትን አንወስድም። ይልቁንም በህይወታችን የማንፈልጋቸውን ነገሮች በሙሉ ሌሎች እንደሰጡን ማመኑ ይቀለናል። ልክ ተማሪዎችን ሲ ሲያገኙ፤ “ሲ አገኘሁኝ” ከማለት ይልቅ  “ሲ ሰጠኝ” ማለት እንደሚቀናቸው ሁሉ።

በ”ሰጠኝ” እና “በአገኘሁ” መካከል ትልቅ የብስለት ልዩነት አለ። ይህ የብስለት መለክያ  “ሀላፊነት መውሰድ” ይባላል። ለህይወታችን ሀላፊነትን ስንውስድ፤ ስኬታችንንም ሆነ ውድቀታችንን “አገኘሁኝ” ነው እንጂ “ተሰጠኝ” አንልም። ሀላፊነት የሚጎደልን ሰው ስንሆን ደግሞ መልካም መልካሙን “አገኘሁኝ”፤ መጥፎ መጥፎውን ደግሞ “ተሰጠኝ” በማለት ከሃላፊነት የሸሸ ኑሮ እንኖራለን።

“ሰጠኝ” ሳይሆን “አገኘሁ” ማለት ይልመድብን።

2 thoughts on ““ሰጠኝ” እና “አገኘሁ”

Do you have any comments?