መፈራረቅ….ሰው የማያመልጠው የተፈጥሮ ህግ

Posted on Posted in ትርጉሞች

የዚህ ሀገር ብርድ እንደ ሀገራችን ብርድ ደግ አይደለም። ሰውን ብቻም ሳይሆን ዛፎቹን ሁሉ እራቁታቸውን የሚያስቀር ጨካኝ ብርድ ነው። ትላንት በቅጠል ተውበው የነበሩት ዛፎች ዛሬ እራቁታቸውን ሳያቸው፤ እንደሰው አይምሮ ቢኖራቸው ምን ይሉ ይሆን ብዬ በምናብ አሰብኩኝ። አመቱን ሙሉ ያበቀሏቸው ቅጠሎች፤ እንደዘበት እረግፈው ማንም ሲረማመድባቸው ሲያዩ ምን ይሰማቸው ይሆን? የብርዱ ከባድነት እንደሰው ተስፋ ያስቆርጣቸው ይሆን? ቅጠሎቻቸውን ሲያረግፍባቸው ከፍቷቸው ከዚህ በኋላ ብሞት ቅጠል አላበቅልም ይሉ ይሆን?

በብርድ ወቅት ዛፎች ብዙ ቅጠሎቻቸውን ያጣሉ፤ ግርማሞገሳቸውን ተነጥቀው እርቃናቸው ይቀራሉ። ሆኖም ግን ተስፋ ቆረጠው ሞታቸውን አይመኙም፤ የበጋ ወቅት እንደሚመጣ እምነት ስላላቸው። እዚህ ላይ ጂም ሮን የተሰኘው ጸሃፊ የተናገረው ንግግር ትዝ አለኝ። “ህይወት የሚፈራረቁትን ወቅቶች ትመስላለች፤ ወቅቱን መቀየር አይቻለንም የምንችለው ግን እራሳችን መቀየር ነው” ብሏል። ክረምቱን መቀየር አይቻለንም፤ አለባበሳችንን ግን ማስተካከል እንችላለን እንደማለት ነው።

መቼም እንደሰወኛ የእኛን ባህሪ አላብሼ በምናብ አሰብኩት እንጂ፤ የትኛውም ዛፍ እንደዚህ አያስብም። ምክንያቱም በተፈጥሮ ላይ እምነት ስላላቸው። ይህ ከባድ ብርድ ሲያልፍ፤ የወደቁት ብሎም የሞቱት ቅጠሎች በአዲስ እንደሚተኩ ስለሚያምኑ። ብርዱን የሚሽር መልካም ወቅት እንደሚመጣ እርግጠኛ ስለሆኑ። “ይህም ያልፋል” የሚል ትልቅ እምነት ስላላቸው መሰለኝ።

የእኛስ ህይወት ከዚህ በምን ይለያል?  የሚገጥሙን ከባድ ችግሮች እንደዚህ የብርድ ወቅት ቢሆኑስ? ክረምቱ በዛፎቹ የፈጸመውን በደል፤ ጊዜ በእኛ ላይ ቢደግመውስ? ብርዱ የዛፎቹን ቅጠል እንዳረገፈባቸው፤እኛ የለፋንባቸውን ነገሮችም ጊዜ ያለርህራሄ ቢቀማንስ?የኮራንበትን  ነገር ሁሉ ከንቱ ቢያደርግብንስ?ለፍተን ያፈራነውን ሀብት፤ ደክመን ያቆየነውን ፍቅር፤ ብዙ መስዋትነት የከፈልንበት ስኬትን በቀላሉ ከጉያችን በቀላሉ ቢነጥቀንስ?

እዚህ ላይ ነው የዛፎቹ  ጥበብ ሊገባን የሚገባው። አለም የምትመራው በማይዛባ የተፈጥሮ ህግ ነው። ምንም ያህል ብንሰለጥን፤ ምንም ያህል በቴክኖሎጂ ብንራቀቅ፤ የተፈጥሮን ህግ በምንም ተዓምር ልንቀይረው አይቻለንም። ቀኑን ማታ፤ ማታውን ቀን ማድረግ አይሆንልም። የትላንትን የዛሬን እና የነገን ቅደም ተከተል ልንቀያይር አቅም የለንም። በገባዖን  የቆመችው ጸሀይ መቼም ደግማ ለእኛ አትቆምም። ሰዓቷን ጠብቃ ትወጣለች፤ ሰዓቷን ጠብቃ ትጠልቃለች እንጂ። ክረምቱንን እና በጋውን ለእኛ እንደሚመቸን አድርገን ልናስተካክላቸው፤ ልናረዝማቸውም ሆነ ልናሰጥራቸው አይቻለንም። አለም ሁሉ የምትመራበት፤ በሰው ጣልቃ ገብነት የማይስተጓገል ህግ ስላለ።

ይህ የተፈጥሮ ህግ ትሏቅን አለም ብቻም ሳይሆን፤ ትንሹን የእኛንም ህይወት ይመራል። ችግሩ እኛ ከተፈጥሮ ህግ ተስማምተን መኖሩ  ያዳግተናል።ከላይ መነሻ ወደሆነኝ ሀሳብ ስመለስ፤ ነገሮች ከባድ ሲሆኑብን እና እኛ እንዳሰብናቸው መሆን ካልቻሉ፤ ከጊዜ ጋር ሙግት እንገጥማለን። ሁሉም በጊዜ እንደሚሆን መቀበል ይከብደናል። እንደዛፎቹ ቅጠሎቻችንን ባጣን ጊዜ መልሰን እንደምናገኛቸው ማመን ያቅተናል። ብርዱ አልፎ ደስ የሚል ሙቀት እንደሚመጣ ማመን አንችልበትም። ስንወድቅ ተመልሰን እንደምንነሳ ለራሳችን መንገር ያቅተናል። ምክንያቱም የዛፎቹን ያህል እምነት ስለሌለን።

አመቱን ሙሉ የሚቆይ በጋ የለም፤ አመቱን ሙሉ የሚቆይም ክረምትም የለም። ጊዜያቸውን ጠብቀው ይመጣሉ፤ ጊዜያቸውን ጠብቀው ይሄዳሉ። ሰውም እንደሌላው የተፈጥሮ ተጋሪ ከዚህ የወቅት መፈራረቅ አያመልጥም። ልዩነቱ የእኛ ክረምት ከብርድ የዘለለ ነው። ገላችን ብቻም ሳይሆን ውስጣችንም የሚቀዘቅዝበት ወቅት አለ። የብቸኝነት ብርድ፤ የሽንፈት ብርድ፤ የተስፋ መቁረጥ ብርድ ይጎበኙናል። ለዘላለም ሳይሆን፤ በወቅታቸው ሊጎበኙን ነው የሚመጡት። ወቅቱ ሲያልፍ ደግሞ የደስታ ወቅት ሊጎበኘን ይመጣል፤ እሱም ጊዜው ሲደርስ ጥሎን ይሄዳል። ምክንያቱም መፈራረቅ የተፈጥሮ ህግ ስለሆነ ልናመልጠው አንችልም።

ከውልደታችን እስከሞታችን ደስተኛ ብቻ ሆነን ልንኖር አይቻለንም። ወይም ደግሞ በመከራ ብቻ የተሞላ ህይወት ሊኖረን አይችልም። ደስታና መከራ፤ ማግኘት እና ማጣት፤ ማሸነፍ እና መሸነፍ ……እየተፈራረቁ የሚጎበኙን ወቅቶቻችን ናቸው። ደካሞች ከሆንን አንዱን ብቻ ልያዝ ብለን ከተፈጥሮ እንሟገታለን። ለምሳሌ ቅጠሎቹ የረገፈበት ዛፍ ተስፋ ቆርጦ ለመውደቅ ቢሞክር  ሞኝ አያሰኘውም? የምንሰጠው መልስ ምንድን ነው “ክረምቱ እኮ ብዙ አይቆይም” ብለን ማጽናናትችን አይቀርም። የእኛም ህይወት ከዚህ በፍጹም አይለይም።

ምንም አይነት ችግር ላይ ብንሆንም፤ ሊያልፍ እንጂ እስከፍጻሜው ሊሰነብት አልመጣብንምና፤ በትዕግስት ወቅቱን እንለፈው። ቅዝቃዜው አልፎ መልካሙ ወቅት እንደሚመጣ እምነት ይኑረን። ዛሬ ያጣነውን ነገ እንደምናገኝ እንወቅ። ዛሬ የኮራንበትን ነገ ልናጣው እንደምንችል እንገምት። ዋናው መልዕክት ወቅቱን መቀየር ካልቻልን እራሳችንን በመቀየር ከባድ ወቅቶችን በትዕግስት እንለፋቸው ነው።

(በሚስጥረ አደራው)

Do you have any comments?