በፍቅርና በሐይማኖት ስም…….

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

(በሚስጥረ አደራው)

ለዚህ አጭር ጽሁፍ ሁለት አባባሎችን በአንድ ላይ ልጠቀም እፈልጋለው። እውቁ የመንፈሳዊ መምህር ዳይላ ላማ፤ ስለፍቅር እና ስለ ሐይማኖት በተለያዩ ግዜያት የተናገሯቸውን ድንቅ አባባሎች ነው ልጠቀም የሻትኩት።

“ለምትወደው ሰው የሚበርበትን ክንፍ፤ ተመልሶ የሚመጣበትን ስር፤ ካንተ ጋር የሚቆይበትን ምክንያት ስጠው” ብለዋል። በሌላ ንግግራቸው ደግሞ ስለሀይማኖት እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፤ “የሀይማኖት አላማ እራስህን ለመቆጣጠር እንጂ፤ ሌሎችን ለመውቀስ አይደለም”።

ሁለቱን በተለየያ እርስ ላይ የተነገሩ የሚመስሉ አባባሎችን የመረጥኩበት ምክንያት፤ ሁለቱንም የሚያሳስራቸው ነገር ስላለ ነው፤ ይኸውም ለሌሎች ነጻነትን መስጠት የሚለው ሀሳብ። ዳይላ ላማ ያለምክንያት እኒህን ጥልቅ ንግግሮች አልተናገሩም። እንደኔ ነገር መሰነጣጠቅ ለሚወድ ሰው ከውስጣቸው ብዙ ነገሮች ሊወጡባቸው የሚችሉ ንግግሮች ናቸው።

እዚህ ምድር ላይ በእየለቱ የምናያቸው መጥፎ ክስተቶች በአብዛኛው የሚተገበሩት በመልካም ነገር ስም ነው። በተለይም ደግሞ በፍቅር እና በሃይማኖት ስም ብዙ ጥፋቶች ይከሰታሉ። አንዳንዴ ግራ የሚያጋባ ይሆናል፤ በፍቅር ስም እስከግድያ የሚደርሱ ሰዎች አሉ፤ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅስ እየተጠቀሙ የሚሳደቡ ሰዎች እጅግ ብዙ ናቸው። እዚህ ላይ እኔ ሌላውን ለመውቀስ ፈጽሞ አልሞክርም፤ ግን ድርጊቶቻችንን ቆም ብለን ብናስተውል፤ ምክንያታችን በደንብ ይገባን ይሆናል።

ፍቅር እና ሀይማኖት በነጻነት ይተሳሰራሉ፤ ነጻነት ስል ለሌሎች ደስታ ስንል በመንገዳቸው አለመቆም ማለት ነው። ጸጋዬ ገ/መድህን “ዝም ብለን አብረን ዝም እንበል” በሚለው ግጥሙ ላይ ሁሌም የሚያስደምመኝ ስንኝ አለ…..አብረን ዝም እንበል ፤ በተሰኘው ድንቅ ግጥሙ ላይ እንደአዋሽ ውብ ሆኖ የሚፈስ የፍቅር ታሪክ ይታያል (እርግጥ ነው፤ ስነጽሁፍ ለሁላችንም እንደየ ባህሪያችን እና እንደየ የህይወት ተሞክሯችን የሚሰጠን ትርጉም ቢለያይም፤ ለኔ የሚሰማኝን እንዲህ እገልጻለው)።

“ከሰው መንጋ እንገንጠል

ለአንድ አፍታ እንኳን እንገለል

በእፎይታ ጥላ እንጠለል

ዝም ብለን አብረን ዝም እንበል”

እያለ ገጣሚው የሚወዳትን፤ ከዚህ ከትርምስምሱ አለም እንራቅ እያለ ያባብላታል። አንድም የአዋሽን ውበት ለማየት ሁለትም ሁለቱ ብቻቸውን በዝምታ ለመደማመጥ።

“ለማንም ምንም ሳናዋይ ሳንናገር ሳንጋገር

ከአይንሽ፤ ከልብሽ፤ ከልቤ አዋሽ ማዶ እንብረር”- ሲላት፤ ስለፍቅራችን ሌሎችን ማማከር የለብንም፤ ልብሽ እና ልቤ ከፈቀዱ፤ ሌላ የፍቅራችንን ትክክለኝነት የሚያረጋግጥ ነገር  አያስፈልገንም እያላት ይመስላል።  ይቀጥልና

“አጉል ነው ብለን ሳንፈርድ፤ ድንቅም ነው ሳንል ሳንወድ

ዝም ብለን አብረን ብንወርድ” እዚህ ላይ ደግሞ ዳኝነት በፍቅር ውስጥ ቦታ እንደሌለው ለማመልከት ይመስላል፤ “መጥፎ” ወይም “ጥሩ” ብለን አንድን ነገር አስቀድመን ከዳኘነው፤ እውነታውን ለማየት እድል አናገኝም። ዋናውና ከዚህ ጽሁፍ ጋር የተያያዘው ስንኝ ግን የሚከተለው ነው-

“መቼስ አይሆንም ካልሽ ቅሪ፤

ግዴለም አትገደሪ

ልቦናሽ በመተረብሽ ባሳደረብሽ እደሪ” – የሚለው ውብ ስንኝ

እንግዲህ እንዲህ ያላት፤ ስለአዋሽ ውበት፤ ስለዝምታ ድንቅነት፤ አብረው ቢያሳልፉ መልካም ስለሚሆነው ጊዜ ካወያያት በኋላ ነው። ለእኔ እዚህ ላይ ገጣሚው ስለእውነተኛ ፍቅር እያወራ መሆኑን እንድረዳ አድርጎኛል። “ስለምወድሽ ከእኔ ጋር ወደ አዋሽ መውረድ አለብሽ” አላላትም። “ጨረቃም፤ ሰውም ሳይመሰክሩብን፤ ኮከባችን ሳትቆጥርብን እኛም ሳንቆጥርባት፤ እባክሽ አዋሽ ማዶ ሄደን ጀንበር ትጥለቅብን” እያለ ለምኗታል። ሆኖም ግን “ምንም እንኳን ከኔ ጋር ብትሄጂ ደስ ቢለኝም፤ አይሆንም ካልሽ ቅሪ፤ እኔ ባልኩት ሳይሆን፤ ልቦናሽ ባሳደረብሽ እደሪ” ሲላት። ፍቅሩ እውነተኛ መሆኑን ለማስመስከር ነጻነቷን እየሰጣት ይመስለኛል።

እንግዲህ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ይህንን ሁሉ አስቦ ላይሆን ይችላል የጻፈው። የስነ ጽሁፍ ውበቱ ይህ ነው፤ ለሁላችንም የተለያየ መልክ መያዙ። ከላይ የሰፈረው የዳይላ ላማ አባባል እና የሎሬቱ ግጥም፤ ለምንወዳቸው ሰዎች ነጻነት በመስጠት ፍቅራችን በግል ጥቅማችን ሳይበረዝ  ንጹህ ሆኖ እንዲቀር ማድረግ እንደምንችል የሚያስረዱ ናቸው። ቀላል አይደለም፤ እንደ ሀሳብ መልካም እንደተግባር ደግሞ ከባድ በመሆኑ። ቢሆንም ግን በፍቅር ስም ስህተት እንዳንሰራ ማሳሰቢያ ሊሆኑን ይችላሉ።

ወደ ሀይማኖትም ስንመለስ ተመሳሳይ ነው። (እኔ የምናገረው እራሴን ወክዬ ነው፤ ምክንያቱም እምነት ግላዊ ስለሆነ). የየትኛውም እምነት ተከታይ ብንሆን፤ የሀይማኖታችን የመጨረሻው ማሰሪያ ፍቅር ነው። እኛ ለፈጣሪያችን ያለን ፍቅር ብቻም ሳይሆን እኛ ለመላው የፈጣሪ ልጆች ያለን ፍቅር። ለምሳሌ እንደ እናት ወይም እንደ አባት፤ አንድ ሰው ለእኛ መልካም ሆኖ ለልጆቻችን ጨካኝ ቢሆን ለዛ ሰው ምን አይነት ስሜት ነው የሚኖረን? ለዚህ ነው፤ ከፈጣሪ ጋር የሚያገናኘን ድልድይ ለሌሎች ሰዎች በምናደርገው ነገር የሚወሰነው።

የሚያሳዝን ሆኖ ግን እንደ ፍቅር ሁሉ በሀይማኖት ስምም እጅግ አሰቃቂ ነገሮች ይፈጸማሉ። ለምሳሌ ከጥቂት ጊዜያት በፊት አይሲስ ሰላሳ ኢትዮጵያንን አንገት ሲቀላ፤ ድርጊቱን ይበልጥ አሰቃቂ የሚያደርገው በእምነት ስም መፈጸሙ ነው። ዳይላ ላማ “የሀይማኖት አላማ እራስህን ለመቆጣጠር እንጂ፤ ሌሎችን ለመውቀስ አይደለም” ሲሉ- በእምነት ውስጥ ሌሎችን መዳኘት የእምነታችንን አላማ እንድንስት ያደርገናል ለማለት ነው።

በፍቅር እና በእምነት ስም ስህተቶች ይበዛሉና፤ የምናደርጋቸውን ነገሮች እውነተኛ ምክንያት እራሳችንን በግልጽነት እንጠይቅ።

Do you have any comments?