ዝምታ መልስ ይሆናል?

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

mohammed

“ለዋልኩት ውለታ ይሄነው ወይ ውርሴ?

ልፋቴ ድካሜ ይሄ ነው ወይ ውርሴ?

እንግዲህ ምን ልበል ይህ ከሆነ ቅርሴ

አሃ….ዝምታ ነው መልሴ

ክፉ ደግ አትበል አታውጋ ምላሴ

አሃ ዝምታ ነው መልሴ…….”

ማዳመጫዬን ሰክቼ የማዳምጠው ይህንን ውብ የመሐሙድን የሀዘን ድባብ የተላበሰ ዘፈን ነበር። እውነት ግን ዝምታ ትክክለኛ መልስ ይሆናል? ሰው መልካም ስራ ሰርቶ የማይገባውን ክፍያ ሲያገኝ እንዴት ዝምታ መልስ ይሆናል? በዝምታ ብዙ ነገር አናጣም? ዝምታ ከቃል በላይ ይጮሀል የሚባለው እውነት ነው? ከቃል በላይ ከጮኸ ለምን ሰዎች የዝምታቸውን ዋጋ አያገኙም? ለምን ዝም የሚሉት ለጥያቄያቸው መልስ አያገኙም? ብዙ ዝምታዎች እንደሞኝነት አልተቆጠሩም?

አንዳንዴ ልናሸንፋቸው የማንችል የሚመስሉን ትግሎች ይገጥሙናል። ጩኸታችን አልሰማ የሚልበት ወቅት አለ፤ ድምጻችን ቀዝቃዛ ሆኖ ሳይሆን፤ ሰሚ ጆሮ ስላጣን። ጮኸን ጮኸን ሰሚ ስናጣ፤ ዝምታን ለመምረጥ እንገደዳለን። ዝምታ መልስ የሚሆንባቸው ጊዜያቶች እንዳሉ ባይካድም ፤ ለሁሉም ነገር መልስ ይሆናል ብሎ ማሰብ ግን ሞኝነት ነው።

“ሾተሉ እስኪነቀል የነገር አንካሴ

ዝምታ ነው መልሴ” ይቀጥላል ዘፋኙ……

እዚህ ላይ መሐሙድን በህሊናዬ ልሞግተው ፈለግኩኝ። አየህ መሐሙድ፤ ይህ ምክር ለኛ ለምስኪኖች ተገቢ አይደለም። ሲጀምር ሾተል የሚሰካብን አስቀድመን ዝም ስለምንል ነው። ሾተል የተሰካበት ሰው ካልጮኸ በቀር ማን ይነቅልለታ? ካልጮኸ በቀር ማን ህመሙን ይረዳለታል? ህመሙን ያልተናገረ ሰው እንዴት መድሀኒት ያገኛል? ወይስ ሾተሉ በጊዜው እስኪወድቅ፤ ህመሙ በጊዜ እስኪድን፤ ቁስሉ በጊዜ እስኪጠግን መጠበቅ አለብን? ያ ጊዜ ቢረፍድስ? ስለዚህ

“ሾተሉ እስኪነቀል የነገር አንካሴ

ዝምታ ነው መልሴ” ሳይሆን

“ሾተሉ እስኪነቀል የነገር አንካሴ

ዝም አልልም ከቶ፤ ልጩኸው ለራሴ” ብለህ አዚምልን።

“የእውነት ጸሀይ ወጥታ እስከሚታይ ክሴ

ዝምታ ነው መልሴ”  አሁንም በማዳመጫዬ ዘፈኑ ይቆረቆራል……

ፍርድ በራሷ ጊዜ እንድትመጣ ነጻነት ከሰጠናት፤ ያለመምጣት እድሏ እጅግ ሰፊ ነው። ዝም ካልን ጸሀይ ወጥታ ክሳችን የሚታየው ማን ተናግሮልን ነው? በዝምታ ፍርድ ያገኘ ማን ነው? ክሳችን ተገቢውን ፍርድ እንዲያገኝ ከፈልግን ዝምታን ምርጫ ማድረግ አንችልም። ዝምታ ሁኔታውን በጸጋ እንደመቀበል በሚቆጠርባት በዚህች አለም፤ እንዴት የሚገባንን ፍርድ በዝምታችን ውስጥ እንፈልግ? ጥቁሮች ለዘመናት በባርነት የማቀቁት ልክ እንደዘፈኑ፤ ጸሐይ ወጥታ ክሳቸው እስክትታይ  በዝምታ ተስፋ በማድረጋቸው አይደለም?

“የሰው ልጅ ሆዱን ሲከፋው

ጊዜም እንደሰው ሲገፋው

መሄጃ መውጫ ሲጠፋው

ዝምታ ብቻ ነው ተስፋው“…..መሐሙድ ዘፈኑን ያንቆረቁረዋል

በፍጹም…….ዝምታ ለሰው ተስፋ ሊሆን አይችልም። አንድ ነገር እኮ ተስፋ የሚሆነው ለውጥ ማምጣት ሲችል ነው፤ ለውጥ መምጣት የሚችለው ደግሞ ዝምታ ሲሰበር ነው። እርግጥ ነው ብዙዎቻችን ከፍቶናል፤ ጊዜ እንደ ሰው ገፍቶናል ፤ምንም እንኳን ተስፋ የምንጥልበት ነገር ብናጣም፤ ዝም ግን አንልም……….በዝምታ ውስጥ ተስፋ የለምና……

ማዳመጫዬን ከጆሮዬ አውጥቼ……ዝምታዬን በጩኸት ሰበርኩት! ዝም አልልም!!!!

(በሚስጥረ አደራው)

One thought on “ዝምታ መልስ ይሆናል?

Do you have any comments?