ግልጽነትና ሀበሻነት

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

በሚስጥረ አደራው

ዘነበ ወላ የስብሃት ገብረግዚያብሄርን የህይወት ታሪክ ባሰፈረበት መጽሃፉ ስብሃት በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ እንደነበር ጽፎዋል።”መጽሃፍ ቅዱስን ሀበሻ ቢሆን ኖሮ የጻፈው፤ ዳዊት የኦርዮንን ሚስት ተመኘ የሚለውን አይጽፈውም ነበር፤ ከቤርሳቤህ ጋር ተኛ የሚለውንም ያወጣው ነበር” ይህንን እንግዲህ የተናገረው እውቁ ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚያብሄር እንደሆነ ጸሀፊው ዘነበ ወላ ይናገራል። ይህንን ያለበት ምክንያትም የሚኖርበት የሀበሻ ማህበረሰብ ለመዳሰስ የሚፈራቸው ነገሮች መብዛታቸውን ለማስረዳት ነው። ግልጽነት በእኛ ማህበረሰብ ምን ያህል ያልተለመደ ነገር እንደሆነ እንዲገባን ስላሰበ ይመስለኛል፤ ታላቁን ዳዊት እንደምሳሌ ለመጠቀም የተገደደው።

እኛ ሀበሾች ጉድን አደባብሶ በማለፍ፤ ነገርን ሸፋፍኖ በመተው በጣም የተካንን ነን። ግልጽነት እንደማህበረሰብ የጎደለን እንደግለሰብ ደግሞ እጅግ የራቀን ጥበብ ነው። በብዛት የሚያሳፍሩን ነገሮች በሌሎች ማህበረሰቦች ዘንድ የማያሳፍሩ ነገሮች መሆናቸው ደግሞ እራሳችንን ጥያቄ እንድንጠይቅ ያስገድደናል። እድል ኖሮት ከሌላ ማህበረሰብ ጋር መኖር የቻለ ሰው አስተዳደጋችን ምን ያህል ግልጽነትን እንዳላስተማረን በቀላሉ መረዳት ይችላል።

ስለራሳችን በግልጽነት አለማውራትንና ለሰዎች በግልጽነት የተሰማንን አለመግለጽን እንደባህል የወረስነው ነገር ይመስላል። ይህንን ስንል ሁሉም ሀበሻ እንዲህ ነው ብለን ለመፈረድ ሳይሆን፤ አስተዳደጋችን ግልጽነትን በቅጡ እንደማያስተምረን ለመግለጽ ያህል ነው። እኛ ከወላጆቻን ጋር ያለን ግንኙነት በብዛት በግልጽነት ላይ የተመሰረተ አይደለም በፍርሃት ላይ እንጂ፤ ከምንናገረው ነገር የምንፈራቸው ነገሮች በእጅጉ ይበዛሉ። እኛ ከማህበረሰቡ ጋር ያለን ግልኙነትም እንደዛው። ሰው ምን ይለኛል እያልን በጓዳችን የምንደብቃቸው ሚስጥሮች በጣም ብዙ ናቸው። ምክንያቱም ሌሎች በአደባባይ ሲናግሯቸው ስለማንሰማ ነውር ይመስሉናል።

የእኛ ግልጽ አለመሆን ልኩን ከማለፉ የተነሳ፤ አንዳንድ የሚደርሱብን በደሎችን እናኳን አደባባይ አውጥተን ፍርድ እንደማግኘት በፍርሃት ደብቀናቸው እንኖራለን። ሰው በግልጽነት የደረሰበትን እንዳይናገር የማህበረሰብ ይሉኝታ ፍርድ እንዳያገኝ ሲያደርገው ማየት ያሳዝናል። ለምሳሌ በቀደም በአንድ የኢትዮጵያ ሬድዮ ፕሮግራም ላይ አንዲት ሴት አሳዛኝ ታሪኳን ስትናገር ሰምቼ ስለ ግልጽነት ያለንን አመለካከት ይበልጥ እንድጠይቅ ነው ያደረገኝ። ይህቺ ሴት አንድ ዘመዷ አስገድዶ ይደፍራታል፤ ግልጽነትን ያላስተማሯትን ቤተሰቦቿን በመፍራት ግን ችግሯን ሳታክፍላቸው ለብቻዋ መብሰክሰን መረጠች። ታዲያ ይህንን እንድታደርግ ያስገደዳት ከወላጆቿ ጋር ያላት የግልጽነት መጠን ነው።

እውነት ነው ግልጽነት ልክ አለው፤ ሰው የልቡን ሁሉ ዘርግፎ ለሰው መናገር አይችልም፤ ግልጽ መሆን የሚችለውም እራሱን እስከማይረብሽው ድረስ መሆን አለበት። ነገር ግን ነገሮችን ሁሉ እየሸፋፈኑ በምን ይሉኛል መኖር ተገቢ አይደለም። የተሰማንን መናገር መልመዱ ለግል ህይወታችን ብቻ ሳይሆን እንደማህበረሰብም ሆነ እንደሀገር የተሻለ ደረጃ ሊያደርሰን የሚችል ባህል ነው። ችግሮችም እኮ መፈታት የሚችሉት ግልጽ መሆን ስንጀምር ነው።

መወቀስ ያለበትን መውቀስ፤ መነገር ያለበት መናገር፤ አደባባይ መውጣት ያለበትን ነገር አደባባይ ማውጣት መቻል አለብን። ነገሮችን እየሸፋፈን መኖሩ እስካሁን የጠቀመን አይመስልም። ሌሎች ቢሰሙት ደስ የሚላቸውን ብቻ እየተናገሩ ማለፍ ማየት የምንፈልገውን ልወጥ እንዳናይ ያደርገናል።

እርግጥ ግልጽነት ከባድ ነው፤ የተሰማንን ስንናገር ብዙ ሰዎች ሊከፉብን ይችላሉ፤ በተለይ ስህተትን መናገር ባልተለመደበት ማህበረሰብ እውነታውን አውጥቶ መናገር ቀላል አይደለም። ግን ቀስ እያልን መጀመሪያ ከራሳችን እንጀምር፤ ቀጥሎ ወደ ቤትሰባችን እንሂድ፤ ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር በግልጽ መነጋገር እንልመድ፤ ልጆቻችን እየፈሩን ነገሮችን ከሚደብቁንና  ቆይተን ከምንጸጸት ግልጽነትን እናስተምራቸውና ከስህተት እንታደጋቸው። ቀጥሎ ወደ ማህበረሰብ እንሂድ  በውጭው ሀገር ደስ የሚል አንድ አባባል አላቸው በየመስሪያቤቱም የሚጠቀሙበት “see something say something” ይላሉ። ያያችሁትን ከመናገር ወደኋላ አትበሉ እንደማለት ነው። እንደማህበረሰብ ወይም ኮሚኒቲ ግልጽነት የለወጥ መሰረት ነው፤ ለምሳሌ ሚዲያዮቻችን እና ጋዜጠኞቻችን ግልጽነት ቢኖራቸው ማህበረሰቡን ምን ያህል ማገልገል ይችሉ እንደነበር መገመቱ አይከብድም።

በግልጽነት መነጋግርን ቀስ እያልን እንልመድ፤ ነገሮችን እየሸፋፈኑ ማልፍ የምንፈልገውን ለውጥ አያመጣልንምና። ምን ይሉኛል የሚለው ባህል ልኩን እንዳያፍ እና በፍርሃት እንዳያጥረን እናስብበት።

 

Do you have any comments?