ሎጎ ቴራፒ- ከትርጉም የለሽ እና ከተስፋ መቁረጥ ኑሮ የሚያላቅቅ የስነ-ልቦና ጥበብ (ክፍል አንድ)

Posted on Posted in መነቃቂያ

(በሚስጥረ አደራው)

Logo therapy – Part one
” When I was in the concentration camp, I was confronted with Two people who attempted to commit suicide and i asked them why they want to take their lives, I asked both of them independently. Both of them told me “see doctor I don’t have anything to expect from my life anymore” you know why I asked them? “listen, isn’t it considerably possible that instead life expects something from you?”

ፕሮፌሰር ቪክተር ፍራንኪል የኦውስትሪያ ኑሮሎጂስት እና የስነልቦና አማካሪ ነበሩ። በ1940ዎቹ የናዚ ጦርነት ወቅት በናዚ ቁጥጥር ስር ውለው በአስፈሪዎቹ የናዚ ኮንሰንትሬሽን ካምፖች ውስጥ ለሶስት አመታት የግፍ ጊዜያቶችን አሳልፈዋል። የሚወዷትን ሚስታቸው፤ እናት እና አባታቸውን ያጡት በነዚህ እስር ቤቶች ውስጥ ነበር። በነዚህ የሰቀቀን ጊዜያቶች፤ ረሃብን፤ በሽታን፤ ስቃይና ግፍን ከበቂ በላይ ተመልክተዋል። እንደሳቸው የናዚ እጣፋንታ ከደረሰባቸው ሚሊየን እስረኞች በተለየ መልኩ ግን ቪክተር ዛሬም ድረስ ስማቸው ይነሳል። በነዛ የስቃይ ጊዜያቶች ውስጥ ሆኖ የመኖርን ትርጉም ለመመርመር የጣሩ፤ የጣሩ ብቻም ሳይሆን የስነ-ልቦና ጥበብ ላይ ተጽዕኖ ማድረግ የቻሉ ሰው ነበሩ።

ቪክተር ከ 1945 እ.ኤ.አ በኋላ ማለትም ከእስር ነጻ ሲወጡ፤ ወደ ኦስትሪያ በመመለስ በእስር ጊዜያቶች ያዩትን እና ያስተዋሉትን ከስነ ልቦና ምርምር ጋር በማዋሃድ አዲስ ምዕራፍ ለመፍጠር ችለዋል፤ ቪክተር ምርምር ካደረጉባቸውና ለአለም ካበረከቷቸው ስራዎች ዋነኛው Logo therapy ይባላል። በዚህ በክፍል አንድ ጽሁፍ ውስጥ በጥቂቱ ይህንን የስነልቦና ዘርፍ እንዳስሳለን

ሎጎቴራፒ ምንድን ነው?

ከቪክተር ፍራንክሊን ተቋም (Victor Frankl Institute of logo therapy) ያገኘሁት ጽሁፍ እንዲህ ይላል
” Victor Frankl’s Logo therapy is based on the premise that the human person is motivated by a “will to meaning” an inner pull to find a meaning in life.”

የሎጎቴራፒ መሰረተ ሃሳብ የሰው ልጅ ለህይወቱ የሚሰጠው ትርጉም ካለው ለኑሮው መነቃቃትን ይፈጥርለታል የሚል ነው፤ ይህ ማለት የምንኖርለት ነገር ሲኖረን የሚገጥሙንን ከባድ ፈተናዎች እንኳን መጋፈጥ የሚያስችል ጉልበት ይኖረናል። ፕ/ር ቪክተር በእስር በቆዩባቸው ጊዜያቶች እንዳስተዋሉትና በኋላ ከእስር ወጥተው እንዳስረዱት ከሆነ፤ በእስር ቤት ውስጥ ካሉት እስረኞች ውስጥ፤ በህይወታቸው የሚኖሩለት ነገር ያላቸው ወይንም ከእስር ሲወጡ የሚያድረጉትን ነገር የሚያውቁ (ለማድረግ የሚጓጉ) እስረኞች የመትረፍ እድላቸው ሰፊ ነበር ብለዋል። በምሳሌም ሲያስረዱ፤ ከእሳቸው ጋር ከታሰሩት ሰዎች መካከል አንደኛው ሲበዛ የመጻፍ ፍቅር ነበረው፤ በዛ በመከራ ጊዜ ውስጥ ሆኖ እንኳን የሚያስበው ከእስር ሲወጣ ስለሚያሳትመው መጽሃፍ ነበር። ሌላኛው እስረኛ በበኩሉ ለልጁ የነበረው ፍቅር ካለበት የመከራ ጊዜ አሻግሮ እንዲመለከት አድርጎት ነበር። ፕ/ሩ የራሳቸውንም ታሪክ እንደምሳሌ ሲወስዱ፤ በወቅቱ ለነበረችው እና በናዚ ግፍ ህይወቷን ላጣችው ሚስታቸው የነበራቸው ፍቅር ከዛም በላይ ለመኖር የሚያበቃ ምክንያት ስለነበራቸው፤ ያንን መከራ በጽናፍ ለማለፍ የሚያስችል ጉልበትን አግኝተው ነበር።

ምንም እንኳን ፕ/ር  ቪክተር የሎጎቴራፒን ሃሳብ ያመነጩት ወደ እስር ቤት ከመግባታቸው አስቀድመው ቢሆንም በእስር ቤት በቆዩባቸው ጊዜያቶች ግን ጽንሰ ሃሳቡን አጠንክረውታል። የፕ/ር ቪክተር ተቋም የሎጎቴራፒን ምንነት እና ትርጉም በሚከተሉት ሶስት ነጥቦች ያብራራል

The following list of tenets represents basic principles of Logo therapy
1- Life has meaning under all circumstances, even the most miserable ones.
2- our main motivation for living is our will to find meaning in life
3- We have freedom to find meaning in what we do, and what we experience, or at least in the stand we take when faced with a situation of unchangeable suffering.

ሶስቱን ነጥቦች እንዲህ እንመልከታቸው

1ኛ– ህይወት በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም ትርጉም አላት፤ ለጊዜው ከባድ በሚመስሉን ጊዜያቶችም ጭምር- ፕ/ሩ በተለያዩ ጥናቶች እንዳስረዱት ሰዎች ለመኖር ምክንያት ሲኖራቸው ህይወታቸው በማንኛውም ማዕበል ውስጥ ቢሆን እንኳን ትርጉም ይኖረዋል። ከላይ እንደጠቀስኩት በናዚ የእስር ቤቶች ውስጥ ሆነው እንኳን ስለነገ ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎችን ስናይ ምን ያህል ለመኖር ያላቸው ምክንያት ጽናት እንዳሰጣቸው ነው። ስለዚህ የሎጎ ቴራፒ ዋና መሰረት፤ ለህይወታችን ትርጉም በመስጠት እራሳችን ከተስፋ መቁረጥ አልያም ከትርጉም የለሽ ኑሮ ማላቀቅ ነው። ለወደፊቱ የሚኖረንን ኑሮ በህሊናችን መሳል ስንችል እና ሲያጓጓን አሁን ያለንበትን ፈተና ለማለፍ ጽናት ይኖረናል።

2ኛ– ዋና የህይወታችን መነቃቂያ ለህይወታችን ትርጉም መፈለግ ነው- ብዙ ሰዎች ለጭንቀት ወይንም ለትርጉም አልባ ኑሮ የሚዳረጉት በህይወታቸው የሚያነቃቃቸው ነገር ስለሌላቸው ነው። በየቀኑ የምናደርገው ነገር ለእኛ ትርጉም ካልሰጠን ህይወት ድግግሞሽ ከመሆን የዘለለ ትርጉም አይኖራትም። ለዚህ ነው ፕ/ር ቪክተር ሰዎች በሎጎ ቴራፒ ወይንም ለህይወታቸው ትርጉም በመፈለግ ያንቀላፋውን ኑሮዋቸውን ማንቃት እንደሚችሉ የሚያስረዱት። ከላይ በምሳሌ የጠቀሷቸው ሰዎች እራሳቸውን ጨምሮ እንዲሚያመላክቱት፤ ለሆነ ነገር ፍቅር ሲኖረን ትልቅ መነቃቃት በህይወታችን ይፈጠራል። “ፍቅር” ከፍተኛ መነቃቃትን እንድሚያመጣም ፕ/ሩ በመጽሃፋቸው አስረድተዋል። ለምሳሌ አንዱ እስረኛ ለልጁ የነበረው ፍቅር፤ ሌላው እስረኛ ለመጽሐፍ የነበረው ፍቅር፤ ፕ/ሩ እራሳቸው ለሚስታቸው የነበራቸው ፍቅር፤ ያፈቀሩት ነገር ይለያይ እንጂ፤ ለሶስቱም በአስቸጋሪው የሰቆቃ ጊዜ እንኳን የመኖርን ጉልበት ሰጥቷቸዋል። ሰዎች ለሚወዱት ነገር መስዋት ለመክፈል ፈቃደኛ የሚሆኑትም በዚሁ ምክንያት ነው።

3ኛ– የመጨረሻው ነጥብ ሰዎች በህይወታቸው በሚያደርጉት ነገር፤ ወይም በሚኖራቸው ልምድ ለህይወታቸው ትርጉም የሚሰጣቸውን ነገር የመፈለግ ነጻነት አላቸው። ይሄ እንኳን ባይቻል ችግር እና መከራ ሲገጥማቸው ሁኔታው የማይቀየር ከሆነ ለችግሩ የሚኖራቸውን አመለካከት የመወሰን ነጻነት አላቸው የሚል ነው። ፕ/ር ቪክተር ይህንን ነጥብ በምሳሌ ሲያስረዱ

“እርግጥ ነው ሰዎች በሁሉም ነገሮች ላይ ነጻነት ሊኖራቸው አይችልም፤ ከእኛ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ነገሮች መፈጠራቸው ስለማይቀር ። ነገር ግን ለነገሮች የሚኖረን አመለካካት ለህይወታችን የሚኖረንን ትርጉም ይወስነዋል። ለምሳሌ አንድ የ17 አመት ልጅ የጻፈልኝ ደብዳቤ ይህንን በደንብ ያስረዳል፤ ይህ ልጅ የደረሰበት የመኪና አደጋ ከአንገቱ በታች መንቀሳቀስ እንዳይችል አደርጎታል፤ በደብዳቤው ግን እንዲህ ነበር ያለው “ምንም እንኳን አደጋው አንገቴን ቢሰብረውም፤ “እኔነቴን” ግን አልሰባበረውም” ሲል የደረሰበትን ክፉ እጣ በራሱ አመለካከት እንዴት እንደቀየረው ተናግሯል።”  እንግዲህ ሁኔታዎችን የምናይበት መንገድ ለህይወት የሚኖረንን  ትርጉም ምን ያህል እንደሚቀርጸው ያስረዳል። ልንለውጣቸው የማንችላቸውን ነገሮችን የምናቀላቸው አመለካከታችንን በመቀየር ብቻ ነው እንደማለት ነው።

(በክፍል ሁለት በዚሁ የስነ-ልቦና ጥበብ እራሳችንን እንዴት ማከም እንደምንችልና እንዴት ትርጉም ያለው ኑሮን መምራት እንደምንችል እንመለከታለን)

One thought on “ሎጎ ቴራፒ- ከትርጉም የለሽ እና ከተስፋ መቁረጥ ኑሮ የሚያላቅቅ የስነ-ልቦና ጥበብ (ክፍል አንድ)

Do you have any comments?