ብቸኝነት እንዲሰማን የሚያደርጉን የገዛ ሚስጥሮቻችን ቢሆኑስ?

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

our own secrets በሚስጥረ አደራው

የየለት ኑሮዋችንን  ጸሃይ ይሙቀው ማለት አንችልም። የምናስበውንና የምናደርገውን ለአላፊ አግዳሚው ማውራትም አይገባንም። ነገር ግን በውስጣችን ብዙ ሚስጥሮችን በያዝን ቁጥር፤ ከማን እንደምንሸሽ ባናውቅም ሁሌም እንደሸሸን ነው። ከልብ የሆኑና ስር የሚሰዱ ግንኙነቶችን መመስረት የሚሳነን በውስጣችን ብዙ የተቆለፈባቸው እውነታዎች ሲኖሩ ነው። በኑሮዋችን ውስጥ ለጭንቀት የሚዳርጉን፤ በየሄድንበት እንዲቆረቁሩን የሚያደርጉን በውስጣችን የምንይዛቸው ሚስጥሮች ቢሆኑስ? ይዘነው የምንጓዘው በፍርሃት የተቋጠረ እውነታ ቢሆንስ እያንገላታን ያለው? የሰራናቸውን ስህተቶች  ሌሎች እንዳያዩብን ስንል ቢሆንስ ብቸኝነትን የመረጥነው?

በብዛት ለራሳችን ደብቀን የምናኖራቸው ነገሮች ከሌሎች ሰዎች ጆሮ ቢደረሱ ሊያሳፍሩን የሚችሉ፤ የሚያስወቅሱን የሚመስለን ወይንም ስማችን እና ማንነታችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ ብለን የምናስባቸው ድርጊቶቻችን ነው። እኒህ ደብቀን ይዘናቸው የምኖራቸው ሚስጥሮቻችን ሁሌም ገሃድ ቢወጡስ እያልን ስለምንጨነቅ፤ በትልቅ ግንብ ልንከልላቸው እንሞክራለን። ታዲያ ሰዎች ወደዚህ ግንብ በቀረቡ ቁጥር ፍርሃትና በራስ አለመተማማን ይሰማናል። ሁሌም የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማን ስለሚያደርጉን ግልጽ ሆነን ህይወትን ለመጋፈጥ ይከብደናል።

ከላይ በአርስቱ ላይ እንዳልኩት ለመቀበል ቢከድብደንም ብቸኝነት እንዲሰማን ከሚያደርጉን ነገሮች ዋነኛው የራሳችን ሚስጥሮች ናቸው። የራሳችን ሚስጥሮች ስል የደበቅናቸው እውነታዎች። ቋጥረን ያስቀመጥናቸው  ስህተቶቻችን፤ ጸጸቶቻችን፤ የራስ ወቀሳዎቻችን ከሁሉም በላይ ደግሞ ሌሎች ያማያውቋቸው መጥፎ ልምዶቻችን። እነዚህ ነገሮች ሳናውቀው ከሰው መሃል እየጎተቱ የሚያርቁን ነገሮች ናቸው። ካለፈው ስህተታችን ጋር ጥብቅ ግንኙነት ካለን  ሁሌም እንደሸሸን ነው። የሚያሳፍር ስራ ሰርተን ከሆነ፤ ሌሎችን በድለን አልያም በመጥፎ ልምድ ውስጥ ተዘፍቀን ከሆነ፤ ህሊናችን በቀላሉ ከሌሎች ጋር እንድንቀላቀል አይፈቅድልንም።

የሚሰማን አጠተን፤ የሚረዳን ሳላልገኘን ብዙ ነገሮችን በውስጣችን ይዘን የምንገዋለል ጥቂቶች አይደለንም። ለዘመናት ታፍኖ የኖረ ስሜታችን በሰው መሃል ብንሆን እንኳን ብቸኝነት እንዲሰማን ያደርገናል። ንስሃ በእምነታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው፤ ስህተታችንን በመተንፈስ ከራሳችን ጋር እንድንታረቅ ስለሚረዳን ነው።  ነገር ግን እውነታውን ደብቀን በይምሰል  ለመኖር ስንጥር ፤ሚስጥሮቻችን ቅያሜ ሆነው ይጉድናል። የምንቀየመው እራሳችንን ነው፤ የሚያሳፍረን ተባራችንን ለሰው ስለማንነግር እንደቂም ቋጥረን በውስጣችን ይዘነው እንዞራለን።

እንደው ለደቂቃ በጣም ያስቀየማችሁን ሰው በህሊናችሁ ሳሉት። እውነት በደል የደረሰበት ሰው ህመሙን ያውቀዋል።ያ የበደለንን ሰው ስናየው ወይም ስሙን ስንሰማ እንዴት ነው የሚነዝረን? ያ ሰው ያደረገንን እያመላለስን እራስ ምታት እሲኪይዘን ደረስ የምናስበው የበደለንን በደል ከውስጣችን መፋቅ ስለተሳነን ነው። በሰዎች ላይ ቂም ስንይዝ ቢያንስ ያስቀየመንን ሰው እናውቀዋለን። ነገር ግን እንዳስቀየመን እንኳን ሳናውቅ  ጥፋትና ስህተቱ ግን በድብቅ የሚያሰቃየን  አንድ ሌላ ነፍስ በሁላችንም  ውስጥ አለ። ይህን ሰው ቀና ብለን አናየውም፤ አንጋፈጠውም ወይም ለበደል አንነሳስም፤ ነገር ግን የሰራውን ስራ  ይቅር ማለት ስላልቻልን  በደል እና ስህተቱ ልክ ሌሎች ላይ እንደምንይዘው ቂም ይጎዳናል። ይህ እንደተቀየምነው ሳያውቅ የተቀየምነው ሰው የገዛ እራሳች ነው። “ቂም” የምንለው በውስጣችን ሚስጥር አድርገን የምንይዛቸው  ህሊናችንን ግን እንዳያርፍ የሚያደርጉትን እውነታዎች ነው።

በርግጥ ሁሉን ሚስጥራችንን ለሰው እናካፍል ማለት አይቻልም። እውነተኛ ወዳጅ እንዲህ በቀላሉ መች ይገኝና? ነገር ግን ህሊናችንን ከሽሽት የሚያድነው ነገር  ወጣም ወረደ ግልጽነት ነው። ከቻልን ለሌላ ሰው እንተንፍሰው ካልችልን ግን ለራሳችን ግልጽ መሆን መቻል አለብን። ቁስላችንን ወይም የሚያስጨንቁንን ነገሮች በመጠጥና በሱስ ልንደብቃቸው አንችልም። በተለያዩ አጋጣሚዎች ብቅ እያሉ ኑሮዋችንን የሰቀቀን ኑሮ ያደርጉታል ። ግልጽ መሆን ወይም የሚያስጨንቀንን ነገር “መተንፈስ” ዋነኛ ጥቅሙ የጥፋተኝነትን ስሜት ይቀንስልናል። እኛን ያጋጠመን ነገር ወይም የሰራነው ስህተት በሌሎች ሰዎችም ህይወት ላይ ተከስቶ የሚያውቅ ነውና እራሳችንን በተለየ አለም ውስጥ ቆልፈን አናስቀምጠው።

እስቲ ሰው ቢያውቅብን መድረሻ ሊያሳጣን የሚችል ምን ሚስጥር አለን? ይህ ሁላችንንም ካደፈጥንበት ቀና የሚያድርግ ጥያቄ ይመስለኛል። በትዳራችን ወስልተን ይሆናል፤ ሰርቀን፤ ዋሽተን፤ ሰው ጎድተን አልያም መጥፎ ህይወት ውስጥ ተዘፍቀን ይሆናል። ነገር ግን በነዚህ ነገሮች የሚመጣውን የህሊና ሽሽት ሊያስቆመው የሚችለው ብቸኛው መፍትሄ “ግልጽነት” ነው። በተለይ ሃይማኖታችን ለዚህ ትልቅ አስተዋጽዎ አለው “ንስሃ” መግባት ማለት ለኔ መተንፈስ ፤ከሚስጥር ቀንበር ነጻ መውጣት ማለት ነው። ሃይማኖተኛ ካልሆንንም የራሳችን የሆነ የንስሃ መንገድ ሊኖረን ይችላል። ለሰው መንገሩን ከፈራን ለራሳችን ግልጽ ሆነን ስህታችንን እንንገረው፤ ያለፈው አልፏል ነገን በነጻነት ኑር እንበለው። ከራሳችን ጋር ይቅር እንባባል፤ ትላንት የሰራነው ስራ ሚስጥር ሲሆን  የህሊናን ሰላም ይረብሻል። ማንም ሰው ከስህተት የነጻ የለምና፤ በልዩነት ቅጣት እራሳችንን አንቅጣ። እውነታውን እንጋፈጥ፤ ግልጽ እንሁን ለሌሎች ግልጽ መሆን ካልቻልን ለራሳችን ግን እውንታውን እንንገረው። ቢያስን ከድብቅ ጎዳና ያወጣናልና። በፈጣሪ የሚያምን ደግሞ ፈጣሪ የሁሉንም ገበና ሸፋኝ ነውና ከማንም በላይ ሃይል ለሆነው ለአምላኩ ቢተነፍስ ከሰላም ሁሉ የበለጠ ስላምን ያገኛል።

ብዙ ሚስጥሮችን ደብቆ መያዝ ከስነ ልቦና ችግሮችም ጋር ጥብቅ ግንኙነት አለው። ይህንን ጽሁፍ ስጽፍ  አንድ የስነ ልቦና ድረ ገጽ ያወጣውን ጽሁፍ ለመመልከት እድል አግኝቼ ነበር።  “The danger of keeping secrets” (ሊንኩን ሲጫኑ ሙሉውን ጽሁፍ ማንበብ ይችላሉ) በተለይ ምን አይነት ሚስጥሮችን መደበቅ እንደሌለብን ያስረዳል። የብዙ ጭንቀቶች መንስኤም ይህ የህሊና ሽሽት እንደሆነ ይነገራል። እስቲ እንተንፍስ…….

Do you have any comments?