ሶስቱ አለሞች

Posted on Posted in አፈንጋጭ ሃሳቦች

circle of influence

በሚስጥረ አደራው

የምን ሶስት አለም አመጣሽ ትሉኝ ይሆናል?

ሶስቱ አለሞች ከውልደት በፊት፤ በምድር ላይና ከሞት በኋላ የምንኖርባቸው አለሞች አይደሉም። ሶስቱም አለሞች በህይወት እያለን የምንኖርባቸው አለሞች ናቸው። በእያንዳንዱ አለም ውስጥ የተለያየ  ኑሮ፤ የተለያዩ ስሜቶች፤ ይንጸባረቃሉ። አለሞቻችን መለያየታቸው መልካም ነገር ሆኖ ሳለ፤ ያንዱን አለም ኑሮ ከሌላው አለም ጋር ከደባለቅነው ግን ችግር ይፈጠራል። አንደኛው አለም ላይ መሆን የሚገባቸው ሰዎች እና ሁኔታዎች ሌላኛው አለም ላይ ከተገኙ ሰላም ይጠፋል።

እኔ ሶስት አለሞች ብዬ የሰየምኳቸው ሶስቱ ነጥቦች ስቴፈን ኮቬይ “የውጤታማ ሰዎች፤ ሰባቱ ባህሪያት” በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ ያሰፈራቸውን ሶስት ነጥቦች ነው። ሶስቱን አለሞች የተለያዩ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ዋነኛው ነገር እኛ እያንዳንዱን አለም ለመቆጣጠር ያለን ስልጣን ነው። ስቴቨን ኮቬይ የሰው ልጅ ሶስት ተጽዕኖ ክልሎች አሉት ይላል

-በቀጥታ ልንቆጣጠራቸው የምንችላቸው ነገሮች ያሉበት ክልል- (Direct control– Problems involving our own behavior.)

-በተዘዋዋሪ ልንቆጣጠራቸው የምንችላቸው ነገሮች ያሉበት ክልል-( Indirect Control– Problems involving other people’s behavior.)

-ልንቆጣጠራቸው የማንችላቸው ነገሮች ያሉበት ናቸው-( No Control– Problems we can do nothing about, Such as our past or Situational realities.)

እኒህን የተጽዕኖ ክልሎች እንደ አለም ብንቆጥራቸው ይበልጥ ምንነታቸውንና ፋይዳቸውን ለመረዳት ያስችለናል። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ሶስቱን ክልሎች እንደሚከተለው ሰይሜያቸዋለው። የመጀመሪያውን ክልል ማለትም በቀጥታ ልንቆጣጠራቸው የምንችላቸው ነገሮች የሚገኙበትን ክልል “ጠባቡ አለም”፤ በተዘዋዋሪ ልንቆጣጠራቸው የምንችላቸው ነገሮች ያሉበትን ሁለተኛውን ክልል “መካከለኛው አለም”። የመጨረሻውን ክልልና ልንቆጣጠራቸው የማንችላቸው ነገሮች ያሉበትን ክልል “ሰፊው አለም” ብዬዋለው።

ጠባቡ አለም  – በዚህ ክልል ውስጥ እኛን ጨምሮ በጣም ጥቂት ሰዎች የሚኖሩበት አለም ነው። በዚህ አለም ውስጥ ሁሉም ነገሮች በራሳችን ቁጥጥር ውስጥ ናቸው። ያልወደድነውን ነገር የመለወጥ አቅሙ አለን፤ ስሜታችንን የማስተካካል ስልጣኑ አለን። ማንም ያላፈቃዳችን ኑሮዋችንን ሊያዘው እና እንደፈለገው ሊያደርገው አይችልም። የዚህ አለም መጥፋትም ሆነ መልማት በራሳችን ይወሰናል፤ ባልን ባህሪ እና ማንነት ማለት ነው።ይህ አለም ጠባብ ይሁን እንጂ የህይወታችን ምሶሶ ነው። ሁሌም ነቅተን ልንጠብቀው እንዲሁም ልንቆጣጠረው ይገባናል። ምክንያቱም የእኛ በነገሮች ላይ ያለንን ተጽዕኖ  የሚያንጸባርቅ ስለሆነ።

መካከለኛው አለም– ይህ አለም ከመጀመሪያው አለም ሰፋ ያለ ነው። ብዙ ነገሮች ላይ ስልጣን የለንም፤ ወይም በቀጥታ ልንቆጣጠራቸው አንችልም። የሌሎች ሰዎች ባህሪ፤ የአካባቢ ተጽዕኖ ዋነኛ ምሳሌዎች ናቸው። በቀጥታ ልንለውጣቸው ባንችልም፤ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጽዕኖ ልናሳድርባቸው ግን እንችላለን።በዚህ አለም ውስጥ ከመጀመሪያው አለም የበዙ ሰዎች ይገኙበታል። ስሜታችንን ሊለውጡ አቅም ያላቸው የቅርብ ሰዎች በዚህኛው አለም ውስጥ ይገኛሉ። ለምሳሌ ጓደኞቻችን፤ ዘመዶቻችን፤ የቅርብ ሰዎች ድንበሩን አልፈው በዚህ በመካከለኛው አለማችን ሊገቡ ይችላሉ። ነገር ግን ያላፈቃዳችን ወደ ጠባቡ አለም ዘልቀው መሰረታዊ የሆነ ማንነታችን ላይ ተጽዕኖ የማሳደር አቅም የለቸውም።

ሰፊው አለም- ይህ አለም ሰፊ ነው፤ ብዙሃኑን የምናስተናግድበት አለም ነው። በቅርበት የማናቃቸው ሰዎች የሚመላለሱበት ጎዳና ነው። በዚህ አለም ላይ ምንም ስልጣን የለንም። ከዛ በተጨማሪ ከእኛ አቅም በላይ የሆኑ ነገሮች የሚከሰቱበት ሲሆን፤ ልንለውጣቸው የማንቻላቸው ፈተናዎችም የሚበቅሉበት ነው። ያለፈው ታሪካችን እና ስህተታችን በዚህ አለም ውስጥ ካሉ ነገሮች ዋነኛው ነው።

የሶስቱን አለም ልዩነቶች ከተራዳን በኋላ ሙሉውም ምስል እንዴት ልንገነዘበው እንችላለን? ከምስሉ ላይ እንደምትመለከቱት እኛ የቆምነው በጠባቡ አለም ውስጥ ነው። በዙሪያችን ያሉት አለሞች እኛ ወዳለንበት አለም የቀረቡ ከሆነ፤ ህይወታችን ላይ ከገዛ እራሳችን ተጽዕኖ በላይ የሌሎች ሰዎች ተጽዕኖ ይበረታል ማለት ነው። እሱ ብቻም ሳይሆን አቅማችንን እያባከንን ያለነው፤ ከእኛ ቁጥጥር ውጪ በሆኑ ሁኔታዎች ላይ ነው ማለት ነው።

ጠባቡን አለም ወይም የራሳችንን ግዛት ባሰፋን ቁጥር፤ በኑሮዋችን ላይ ይበልጥ ስልጣን እየኖረን ይሄዳል ማለት ነው። ማንነታችን እና ህይወታችን በአካባቢያችን ባሉ ነገሮች እንዳይወሰን ጠባቡን አለም ማስፋት መቻል አለብን። የራሳችንን ግዛት ማተለቅ ከቻልን ስሜቶቻችን በዙሪያችን ባሉ ነገሮች በቀላሉ አይወሰንም። በአንጻሩ ሌሎቹ ሁለት አለሞች ወደኛ እየቀረቡ በመጡ ቁጥር፤ ኑሮዋችን በሌሎች ተጽዕኖ ስር እየወደቀ ነው ማለት ነው።

ከተጽዕኖ ሊያርቀን ወይም የእኛን ግዛት ሊያሰፉ ከሚችሉ ነገሮች ውስጥ ዋነኛ ሃላፊነትን መውሰድ መቻል ነው። ለህይወታችን ሃላፊነት መውሰድ ስንጀምር፤ መለወጥ የምንቻልቸውን ነገሮች እየለወጥን፤ መለወጥ የማችንላቸውን ነገሮች እየተቀበልን፤ አለማችንን ሰፊ ማድረግ እንችላልን። እስቲ እራሳችንን እንጠይቅ? ደስታ እና ሃዘናችን ከእኛ ውጪ በሆኑ ነገሮች ከሆነ የሚወሰነው፤ አለማችን በጣም ጠባብ፤ የሌሎች ተጽዕኖ የበዛበት፤ መካከለኛውና ሰፊው አለም ወደኛ የቀረበ ነው ማለት ነው።

ደግሜ ደጋገሜ በተለያዩ ጽሁፎቼ ተመሳሳይ ሃሳቦችን ማለትም ማንነትን የሚያንጹ፤ ኑሮዋችንን የሚገነቡ ሃሳቦችን የተለያዩ ጸሃፊያን ካቀረቡት ላይ እየቆነጣጠርኩኝ የማቀርበው ይህ እርዕስ ተጠንቶ የማያልቅ በመሆኑም ብቻም ሳይሆን፤ ባህሪያችንን መለወጥ ወይም እራሳችንን መቀየር የምናስብ ከሆነ በአንድ ጀንበር እውን የሚሆን ሳይሆን ከጊዜ ብዛት የሚመጣ በመሆኑም ጭምር ነው።

Do you have any comments?